Saturday, July 14, 2018

እናመሰግናለን !

(July 14,(ርዕሰ አንቀፅ ))--ገንዘብ ለሰጠ ገንዘብ ይመለሳል፤ ከሀብቱ ላካፈለም ቆይተው ካፈሩት ሀብት መልሰው ይሰጡታል። አንዳንዴ ግን ከምስጋና ውጪ ምንም ሊሰጠው የሚችል ስጦታ፣ ሊውሉለት የሚችሉት ውለታ የሚታጣለት ሰው ይመጣል። ይሄኔም አንድ ቃል ብቻ ሁሉን የሚሸከም ይመስለናል፤ እናመሰግናለን !

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አሕመድ ገና ከመግቢያቸው ማመስገን መሰልጠን መሆኑን አሳይተውናልና፤ እኛም እናመሰግናቸዋለን። በአካል ስላሳዩን፣ በመንፈስም ስላስገኙልን ከፍታ እናመሰግናለን። ላስጨበጡን ተስፋ፣ ለሰጡን መፅናናት እናመሰግናለን። እውን ስላደረጉት ህልማችን እናመሰግናለን፣ ከመደመር ስለደመሩን፣ ከመከፋፈል ስላተረፉን እናመሰግናለን።

አገር የሚያህል ፍቅርን ስላየንባቸው፣ ከወንድም ከእህቶቻችን ስላገናኙን፣ ለመርከቢቱም መዳን ምክንያት ስለሆኑ እናመሰግናለን!
እርሳቸው፣ ከጎናቸው የነበሩና ያሉ አመራሮችን ሁሉ እናመሰግናለን፤ እነዚህ የእኛ አሸናፊዎች ናቸው።

እንደምን ቢባል፤ እኛ ልናደርግ ያልቻልነውን አድርገዋል፣ ከከፋ ጥፋትም አትርፈውናል። በእኚህ ሰው ብዙ የኖሩ ህልሞቻችን እውን እየሆኑ ነው። ተዓምር እንዳየ ሰው የሚሆነውን በመደነቅ እናያለን፤ ህልምና እውነታችን ደስ በሚል መልኩ ተቀላቅለዋል።
«ወይ ጉድ!»

ማለት ብቻ ተርፎናል። በዚህ መካከል ከእኛ የሚጠበቀውን አብሮ መቆምና ያንንም በሥራ መግለጽ ሊዘነጋ እንደማይገባ ግን ልብ ይሏል! ታድያ ወደነገሬ ስገባ በሃሳባችን የሚመላለስ፤ ከአሸናፊዎቻችን አንደበት ባይወጣም እኛ ግን ተገልጦ ያገኘነው ብዙ ምክር አለ፤ ስለዛም ሁሉ እናመሰግናለን። እንዲህ ነው፤

አንድ ሰው እልፍ ሊያክል እንደሚችል አሳይተውናልና እናመሰግናለን
ሳውቅና ስሰማ «እስቲ ብቻሽን ምን ታመጪያለሽ? ለብቻ መጮህ ምን ዋጋ አለው?» የሚለው ቃል ተለምዷል፤ ታምኖበታልም። አንድ ሰው ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ስለማይመስለን ችላ ያልነው ስንት ነገር አለ? «እኔ ብናገር ባልናገር! እኔ ብል ባልል! እኔ ብሄድ ብቀር!...» ወዘተረፈ እንላለን፤ ግን አንድ ሰው ዋጋ አለው፤ አንድ ሰው ለውጥ ያመጣል።

አንድ ሰው ነኝና ለውጥ አላመጣም አትበል። አንድ ሰው ነኝና አጃቢ ከሌለኝ ሰው አይሰማኝም አትበል። አጃቢ ሃሳብህን ተከትሎ ይመጣል። አገር የሚያክል ሃሳብ ከያዝክ ብቻህን አይደለህም። እያንዳንዱ የምትሟገትለት ሰው በአንተ ውስጥ አለ። ስለዚህ አስተዋይ ከሆንክ፤ አንተ እንደምታስበው አንድ ሰው አይደለህም። አንድ ሰው እልፍ ሲያክል እያየህ?

በጊዜ ላይ መሰልጠን እንደሚቻል አሳይተውናልና እናመሰግናለን
«አሁን መቼ ልጨርሰው ነው? ጊዜው ይበቃኝ ይሆን? ሃያ ምናምን ዓመት ምን አላት? ይህን ለመሆን ሃምሳ ዓመትም የሚበቃ አይመስለኝም…» ወዘተ ሲባል ሰምተን፤ እኛም ብለን እናውቃለን። ጊዜ መንገደኛ ነዋ! በዘመን ጥሪ እንከፋፍለው እንጂ ጊዜ እንደ ወራጅ ውሃ ፈሰስ እያለ ይሄዳል።

ለካ አጭር የሚባል ጊዜ የለም፤ ጊዜ አያንስም። ምን ያህል ተጠቅመናል ነው ጥያቄው። ጊዜን ስታከብረው ያከብርሀል። ለምሳሌ ሦስት ወር አገር ይሠራበታል፤ በሦስት ወር ታሪክ ይገለበጣል፤ በሦስት ወር የሰርተፍኬት ስልጠና ብቻ ይመስለናል የሚያልቀው? ሰው ኅብረትና አንድነትን ይማራል። በጊዜ ውስጥ ታሪክ አይቀየርም፤ ታሪክማ እንዳለ እየተመዘገበ ነው የሚያልፈው። አዲስ ምዕራፍ ግን ይከፈታል። አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ደግሞ አሁን ያለችው እስትንፋስህ በቂ ናት፤ ብዙ ዘመን አያስፈልግም።

ጊዜ አለህ፤ ጊዜው መኖሩ ብቻ ሳይሆን በቂ ነው። ስትሠራና ትልልቅ ህልም ሲኖርህ ጊዜን ትበልጠዋለህ። ከሰዎች አእምሮ በላይ የምትሆነው ጊዜህን ስትጠቀም ነው። የምትፈልገው ለውጥ አውቀህ ካላዘገየኸው በቀር ረጅም ጊዜን ለመጠበቅ አይታገስም። ሦስት ወር ለአንተ ወይም ለሁላችን ለእኛ ምን ያህል ናት? ትንሽ? እንግዲያው በሦስት ወር አገር ተቀይሯል፣ መልክ ታይቷል፣ ዳመና ተገፍፎ የተስፋ መሰረት ተጥሏል።

በፍቅር የማይቻል ነገር እንደሌለ አስታውሰውናልና እናመሰግናለን
«በምን አቅሜ» ብዙዎቻችን እንላለን። የሰው ልጅ በራሱ ሳይሆን በተላበሳቸው ጸጋዎች ምክንያት ትልቅ አቅም አለው። ወላጆቻቸው በፍቺ ተለያይተው፣ እህትና ወንድም በጥቅም ተባልተው፣ ጎረቤታሞች በነገር ተጣልተው...ሁሉም ነገር የተዘጋ ዶሴ መስሎ የተቀመጠበት ቤት በርካታ ነው። ተመልካችም በፍርሃት አልያም በግዴለሽነት ዝም ብሎ ቆይቶ ይሆናል።

ሰው ያደረገውና መልሶ ሊለውጠው የማይችል ነገር የለም። የተዘጋውን ሁሉ በፍቅር መክፈት ይቻላል። የሰው ልጅ ከተላበሰውና ትልቅ አቅም ከሚሰጠው ጸጋ ፍቅር ኃያሉ ነው። ፍቅር የደነደነ የሚመስልን ልብ ያራራል፣ የጨነቀውን ያለዝባል፣ አገርን አንድ አድርጎ የተዘጋን በር ያስከፍታል።

እናም ‹‹ፍቅር የለም›› አትበል። መኖሩ ምን እንደሚመስል ካወቅህ በአቅምህ ፍቅርን አሳይ። ሁሉም አምርሮ ቢጠላላ ወይም ግዴለሽ ቢሆን አልያም ቢፈራ፤ አንተ ግን እንደምትችል እመን። በዚህ ጊዜ በፍቅር የማይቻል ነገር የለም ብሎ አለማመን እንዴት ይቻላል?

አሸናፊነት ምን እንደሆነ አሳይተውናልና እናመሰግናለን
«ሲያበሳጩ» ብለህ ተናደህ የምትተወው ነገር ብዙ ነው። ሃሳባቸውና ድርጊታቸው ልክ እንዳይደለ ስታውቅ፣ አንድ ሰው ነኝና የሚሰማኝ አይኖርም ብለህ ተስፋ ስትቆርጥ ሁሉን ትተህ ትቀመጣለህ። ትቃወማለህ፣ በተቃራኒ ወገን ትቆማለህ፣ የገዛ ወዳጆችህ ቢሆኑ እንኳ ሃሳባቸው ካልጣመህ ትርቃቸዋለህ። በተቃራኒ ወገን ትቆምና ትሟገታለህ።

ብልህ ስትሆን ደስ ያላለህን ጉዳይ ተቃዋሚ ሳይሆን ቀያሪ ትሆናለህ። አስተሳሰባቸው ጠምሟል ያልካቸውን በርቀት ሆነህ በጥላቻ አታያቸውም፤ ትቀርብና የምትፈልገውን እናም መሆን ያለበትን፣ የዘነጉትን ቀለም ታስይዛቸዋለህ። ማሸነፍ የሚቻለው ከላይ ስለሆኑ አይደለም፤ አንድ አባት እንዳወሱት፤ ሙሴ የተገኘው ከፈርኦን ቤት ነው። ወሳኙ ያለህበት ቦታ አይደለም፣ እንዲኖርህ የመረጥከው አስተሳሰብ ነው።

እውነተኛ አሸናፊዎች ደግሞ በድላቸውና በዋንጫቸው ብቻ ሳይሆን እንዲሁ የሚያስተላልፉት ብዙ መልዕክት አለ። ውስጠ ወይራ እንደምንለው ንግግር ወይም ሀሳብ ውጤታቸው ብዙ ምክር ያዘለ ነው። የደረሱበት ብቻ ሳይሆን የሄዱበት መንገድም ያስተምራል። ጉዳዩ አስተውሎ መመልከትን ብቻ ይጠይቃል።

እነዚህ አሸናፊዎች የምናውቀውን እውነት ገለባብጠው ሌላ እውነት ሹክ ይሉናል። እጅ እንደሌላቸው ዓይናችን እያየ ስዕል ይስላሉ፣ እንጨትን ከሚስማር አዋድደው በእግራቸው ወንበር ይሠራሉ። ዓይናማ ባይሆኑም ለዓይናሞችም መብት ተሟግተው ይረታሉ፤ ልጆች ቢሆኑም ከአዋቂ ይልቃሉ።

ሁላችንንም ባለስልጣን ስላደረጉን እናመሰግናለን
ሰው አንድ አመልካች ጣቱን ወደሌላ ሰው ሲቀስር ሦስቱ ወደራሱ ነው የሚያመለክተው ይባላል። ቀላል ነገር አይደለም ለካ! ገልብጣችሁ እዩት። እንኳን በሀሜት በፍቅርም ቢሆን አንዷ ጣታችን ወደ ሌላ ስታመለክት፤ ሦስቱ የቀሩ ጣቶች በፍቅር ነው ወደ እኛ የሚያመለክቱት።

ስማችን አልተጠራም፣ በክብር እንግድነት አንጋበዝም፣ በዘነጡ መኪናዎች ተሳፍረን በአጀብ አንንቀሳቀስም፣ ከገበታው ቀድመን አናነሳም፣ በተቀመጥንበት መድረክ «ክብርት...ክቡር» አንባልም። ግን አንድ ሰው የሚያመጣውን ለውጥ አይተን፣ ጊዜ በቀመሩ ውስጥ ተዋናይ እንጂ እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል ተረድተን፣ ሁላችን ባለስልጣን ነን/ሆነናል።

ስልጣን የሰጡን በአደራ ነው። አደራቸው ቀላል ነው፤ መደመር ብቻ። ሰው እንዴት ተዋደድ፣ አንድነትን አስቀድም፣ ፍቅርን አስበልጥ፣ ይቅርታን እወቅበት ሲባል ይከብደዋል? አገርህን በቀና ልቦና፣ በእኔነት መንፈስ አገልግል ሲባል ፊቱን ያጠቁራል? በፍፁም! የሰጡን አደራ ከተሸከሙት ያነሰ ነው። ከባዱን ሸክማችንን ተሸክመው፣ የማንደፈረውን ደፍረው አሳይተውናልና ቀላሉን ነገር ማድረግ ደግሞ ሊከብደን አይገባም።

ፈጣሪ የሰውን ልጅ ሲፈጥር ፍቅሩን የገለጠው ሁሉን አሟልቶ ሰጥቶ ነው፤ ለምሳሌ ገነት የተባለ ውብ ስፍራ ከነሙሉ ክብሩና ውበቱ ለመጀመሪያው ሰው ተሰጥቶት ነበር። ከሰው ደግሞ የተጠበቀው አንድ ነገር ብቻ ነበር፤ በተራው ለፈጣሪው አክብሮት እና ፍቅሩን እንዲገልጽ አንዲት ትዕዛዝን ማክበር ብቻ፤ አንዲት ቅጠልን አለመንካት፤ ያውም የሞት ፍሬ በመሆኗ።

«ወይ አዳም!» የምንልበት ዘመን አልፎ አሁን «ወይ እኔ» ላይ ደርሰን የለ? የምንፈልገው ሁሉ ከሆነልን ዘንዳ አመስግነን የሚፈለግብንን ልናደርግ ይገባል። ፍቅርን ማጠንከር፣ አንድ ሰው ነን ብለን ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን እውነትን ይዘን መሟገት፣ መሸሽ ሳይሆን መጋፈጥ፣ ይህንንም ሁሉ በፍቅር ማድረግ። የእነዚህ ድምር የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ ከሌሎች የምንጠብቅ ሳይሆን እኛው የምንሠራት ያደርገናል። ይህን መንገድ ያስጀመሩንን ግን...አሁንም እናመሰግናለን። ሰላም!
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ሊድያ ተስፋዬ)
 Home

No comments:

Post a Comment