Thursday, December 13, 2012

በሁለት ቀናት ልዩነት ሦስት ጊዜ ቀብሯ የተፈጸመው ወላድ ጉዳይ እያነጋገረ ነው

(Dec 12, 2012, Reporter)-- የመጀመርያ ልጇን በቀዶ ሕክምና ከተገላገለች በኋላ ደም ፈሷት ሕይወቷ ያለፈው የ27 ዓመት ወጣት የቀብር ሥርዓቷ ባለፈው ቅዳሜ፣ እሑድና ከትናንት በስቲያ ሰኞ የመፈጸሙ ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡ ሟች ቤተልሔም ሰለሞን ልጅ ወልዳ ለመሳም ዘጠኝ ወራትን ስትጠብቅና የእርግዝናዋንም ሁኔታ ስትከታተል ቆይታ የመውለጃዋ ዕለት በመድረሱ፣ ጎፋ ማዞሪያ ወደሚገኘው ሮያል የጽንስና የማኅፀን ሕክምና ከፍተኛ ክሊኒክ የሄደችው ኅዳር 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ነበር፡፡

ክትትል ስታደርግበት የነበረው ክሊኒክ ተቀብሎአት ወደ ማዋለጃ ክፍል ካስገባት በኋላ የምጥ መርፌ ቢወጋትም፣ በዕለቱ ልትወልድ አለመቻሏንና ወደ ቤቷ መመለሷን ወላጅ እናቷ ወይዘሮ በለጡ አበበና ባለቤቷ አቶ ፍስሐ እሸቴ ገልጸዋል፡፡

ቤተሰቦቿ እንደሚሉት፣ ቤተልሔም ምጧ እየተፋፋመ በመምጣቱ ኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ተመልሳ ወደ ክሊኒኩ ትሄዳለች፡፡ የክሊኒኩ ሐኪሞች ተቀብለዋት ወደ ማዋለጃ ክፍል ካስገቧት ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ ቤተሰቦቿ ተጠርተው “እንኳን ደስ ያላችሁ፤ በሰላም ተገላግላለችና የሕፃኗን ማቀፊያ አምጡ፤” ይባላሉ፡፡ በክሊኒኩ የተገኙት እናቷና ባለቤቷ ደስታቸውን በእልልታና እርስ በርስ በመሳሳም ገልጸው ለጥቂት ደቂቃዎች እንደቆዩ፣ ቤተልሔም “እናቴን፣ ባለቤቴንና ልጄን አሳዩኝ፤” ብላለች ተባሉና ሁሉም ገቡ፡፡

ቤተልሔም ከማደንዘዣ ነቅታ በደንብ እንዳነጋገረቻቸው ተናግረው፣ “ጠብቁ አሁን ትወጣለች” በመባላቸው ሕፃኗን ይዘው ከነበረችበት ክፍል ወጥተው መጠባበቅ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ ሐኪሞቹ “ትንሽ ቆዩና ባለቤቷን ጠሩት” የሚሉት የቤተልሔም እናት፣ እሳቸው ግራ ገብቷቸው በመጠባበቅ ላይ እያሉ፣ ባለቤቷ መኪናቸውን ይዘው ሲወጡ መመልከታቸውንና በዚያው መቅረታቸውን ተናግረዋል፡፡

ልጃቸው ምን እንደሆነች ያላወቁትና ግራ ተጋብተው ሲንቆራጠጡ ለነበሩት የቤተልሔም እናት፣ አንዲት ነርስና ዶክተር መጥተው የባለቤቷን ስልክ ሲጠይቋቸው፣ “ምነው ልጄ ምን ሆነች?” ሲሏቸው፣ “ደም ስላነሳት ደም እንዲሰጥ ነው” እንዳሏቸው ተናግረዋል፡፡

የቤተልሔም ባለቤትና ጓደኞች ደም ቢሰጡም እየደከመች ስለመጣችባቸው ያዋለዷት ዶክተር ሪፈር ጽፈው በመስጠት ኦክስጂን የተገጠመለት አምቡላንስ እንዲያመጡ ይነግሯቸዋል፡፡ ደክማለች በተባለችው ልጃቸው የተጨናነቁት ቤተሰቦች፣ ሩጫቸውን ወደ ተክለሃይማኖት ሆስፒታል እንዳደረጉ ይናገራሉ፡፡ የተጻፈውን ሪፈር ወረቀት የተመለከቱት የተክለሃይማኖት ሆስፒታል ሐኪም፣ “ብዙ ደም ስለፈሰሳት አንሠራም፤ ኃላፊነት አንወስድም፤” ሲሏቸው እግራቸው ሥር ቢወድቁም ሌላ ምላሽ ሊሰጧቸው እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡

ግራ የተጋቡት ቤተሰቦች ጉዟቸውን ሜክሲኮ ገነት ሆቴል አካባቢ ወደሚገኘው ላንድማርክ ሆስፒታል በማድረጋቸው፣ የታዘዙትን ኦክስጂን የጫነ አምቡላንስ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የሆስፒታሉ ሠራተኞች፣ “እናንተ እዚህ ጠብቁን፤ እኛ ይዘናት እንመጣለን፤” ብለው ቤተልሔም ወደተኛችበት ሮያል የጽንስና የማኅፀን ሕክምና ከፍተኛ ክሊኒክ በማምራት ይዘዋት መምጣታቸውን እናቷ ወይዘሮ በለጡ ተናግረዋል፡፡ የቤተሰቦቿ መሯሯጥና እሷን ለማትረፍ ያደረጉት ጥረት ውጤት ሳያገኝ ቤተልሔም ላንድማርክ ስትደርስ ማረፏን እናቷና ባለቤቷ አስረድተዋል፡፡

ይኼ ሁሉ የሆነው ኅዳር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. ሙሉቀን እስከ ምሽት ድረስ በመሆኑ፣ የቤተልሔም አስከሬን ላንድማርክ ሆስፒታል እንዲያድር ይደረግና ቤተሰቦቿ በቀዶ ሕክምና የተወለደችውን ሕፃን ታቅፈው ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡

“ማንኛውም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም” የሚለው መሪ ቃል ባልሠራበት ሁኔታ ደም ፈሷት ሕይወቷን መታደግ ሳይቻል በመቅረቱ ቤተልሔም ሕይወቷ ማለፉንም አስረድተዋል፡፡ ቤተሰቦቿና ወዳጅ ዘመዶቿ በተገኙበት የቀብር ሥርዓቷ ገርጂ በሚገኘው ደብረገነት ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት መፈጸሙን ቤተሰቦቿ አረጋግጠዋል፡፡

የቀብር ሥርዓቷን ፈጽመው በሐዘን እየተብሰለሰሉ የዋሉትና ያደሩት የቤተልሔም ቤተሰቦች፣ በማግሥቱ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. የተነገራቸውን ማመን አቅቷቸው ወደ ቀብር ቦታዋ ተሯሩጠው ይሄዳሉ፡፡

ቤተሰቦቿ የቀብር ቦታው ሲደርሱ የቤተልሔም አስከሬን ከተቀበረበት ጉድጓድ ወጥቶ ዳር ላይ በፊቱ ተደፍቶ ማየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አስከሬን ጉድጓድ ውስጥ ከገባ በኋላ በባዞላ ድንጋይ ጉድጓዱ ተደፍኖ በላዩ ላይ በሲሚንቶ ይለሰናል፡፡ ከዚያም በላይ አፈር ይለብሳል፡፡ ይኼንን ሁሉ አልፎ እንዴት ሊፈጸም እንደቻለ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሊቀ ማዕምራን ጽጌ ከበረ ምላሽ እንዲሰጡ በሪፖርተር ተጠይቀው ነበር፡፡

አስተዳዳሪው እንደነገሩን፣ ሟች የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በመሆኗ ሥርዓተ ፍትኃት ተፈጽሞላት ኅዳር 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት የቀብር ሥርዓቷ ተከናውኗል፡፡ በዚያኑ ቀን ለእሑድ አጥቢያ እሳቸው ቅዳሴ ላይ እያሉ የቤተ ክርስቲያኑ ጥበቃዎች አስከሬን ከጉድጓድ ወጥቶ መገኘቱን ነግረዋቸዋል፡፡

ጥበቃዎቹ እንደነገሯቸው አስከሬን ከተቀበረበት ወጥቶ በመገኘቱ ለፖሊስ ተደውሎለት መጥቷል፡፡ የሟች ቤተሰቦችም መጥተዋል፡፡ ውጭ ላይ የተገኘው አስከሬን የተገነዘበት ጨርቅም የለም፡፡ አስከሬኑ ልብስ ባለመልበሱ ምክንያት ነጠላ ተሸፍኖ አባዲና እስኪመጣ ቢጠበቅም ሊመጣ ባለመቻሉ፣ ፖሊስና የሟች ቤተሰቦች ተመካክረውና ተስማምተው ለሁለተኛ ጊዜ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ አምስት ሰዓት አካባቢ በድጋሚ ቀብሩ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

አስተዳዳሪው ያዩትን እንደተናገሩት፣ አስከሬኑ የወጣው ባንድ በኩል አንድ ባዞላ ድንጋይ ተፈንቅሎና በጠባብ ቀዳዳ ውስጥ ሲሆን፣ ቀብር የተፈጸመበት ሳጥንም ጉድጓዱ ውስጥ መሆኑንና አስከሬኑ በማበጡ ምክንያት እንዴት በዚያ ቀዳዳ ውስጥ እንደወጣ ተዓምር እንደሆነባቸው ነው፡፡

አስተዳዳሪው እንደገለጹት ሁሉ የሟች ቤተሰቦች ያዩትን ተናግረዋል፡፡ በሲሚንቶ የተደፈነ መቃብርን ደም ፈሷት የሞተች፣ ከ12 ሰዓታት በላይ ታፍና የቆየችና አቅም የሌላት ወላድ፣ ቀጭን ሰው በማያስወጣ ቀዳዳ እንዴት እንደወጣች፣ አፈሩ ሳይነሳና ከአንድ ባዞላ በስተቀር ሌላው ሳይነካ አስከሬን ወጥቶ በደረቱ ተደፍቶ መገኘቱ ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡

የሟች ቤተልሔም አስከሬን ጉዳይ በሁለት ጊዜ ቀብር ሳያበቃ ከተቀበረ ከሰዓታት በኋላ “ጩኸት ይሰማል፤ ሳጥን እየተንኳኳ ነው፤” በማለት ፖሊሶች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎችና ሕዝቡ አካባቢውን አጥለቅልቆት እንደገና መጠራታቸውን ቤተሰቦቿ ገልጸዋል፡፡ እነሱ ሲደርሱ “ሆን ብለው ከነነፍሷ ቀብረዋት ነው፤ አምልኮ ቢኖር ነው፤ ስትጮህ ሰምተናታል፤ ውኃ ስጡኝ ስትል ነበር፣ ወዘተ” ከሚል ሹክሹክታና ትርምስ በስተቀር የቀብር ቦታው እንዳልተከፈተ መመልከታቸውን ቤተሰቦቿ ተናግረዋል፡፡

ፖሊሶች የሟች ቤተሰቦችን “እኛም ምንም የሰማነውና ያየነው ነገር የለም፤ ፈቃደኛ ከሆናችሁ ይቆፈርና ይውጣ፤” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው፣ “የተሰበሰበው ሰው የተለያየ ነገር ሲል እየሰማን እንዴት አይሆንም እንላለን? ይቆፈርና ይውጣ፤” በማለት መፍቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡

አስከሬኑ በፖሊስ ተቆፍሮ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ሳጥኑ ሲከፈትና አባዲና ሲመረምረው መሞቷ መረጋገጡን፣ ነገር ግን ሰውነቷ ፎርማሊን የተወጋ ቢሆንም፣ መተጣጠፍና መዘረጋጋት እንደሚችል የገለጹት ቤተሰቦቿ፣ ሕይወቷ ለማለፉ የመጨረሻ ማረጋገጫ ለማግኘት አስከሬኑ ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ገብቶ እንዲመረመር ከተደረገ በኋላ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ታኅሣሥ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ለመጨረሻ ጊዜ ቀብሯ መፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡

ልጃቸው በሕክምና ጉድለት ደሟ ፈሶ መሞቷ አንሶ አስከሬኗ ሲንገላታ መክረሙ የበለጠ መሪር ሐዘን እንደሆነባቸው የገለጹት እናቷ፣ አንድ ልጃቸው መሆኗንና እሳቸውም ሆኑ ልጃቸው ከማንም ጋር ፀብም ሆነ ቅያሜ የሌላቸው በመሆኑ የልጃቸውን አስከሬን ከጉድጓድ ያወጣውን ማወቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት “ሰምተናል፣ አይተናል፤” በማለት ሕዝቡንና ሐዘንተኞችን ሲያሸብሩ የነበሩትን በደንብ እንዲመረምርና ያለውን እውነት እንዲገልጽላቸውም ጠይቀዋል፡፡

የባለቤታቸውን የአስከሬን ምርመራ ውጤትና በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ተጠርጣሪ ሰዎች የምርመራ ውጤት አንድ ላይ ለቤተሰብና ለሕዝቡ ፖሊስ ይፋ እንዲያደርግ አቶ ፍሰሐ እሸቴ ጠይቀዋል፡፡

ፖሊስ ስለደረሰበትና ስለተደረገው ነገር ሁሉ ማብራርያ እንዲሰጥ በሪፖርተር ጥያቄ ቀርቦለት፣ የአስከሬኑ ምርመራ ውጤት ገና እንዳልደረሰ ገልጾ፣ ሕዝብንና ቤተሰብን በተደጋጋሚ ሲያሸብሩ የነበሩትን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና በምርመራ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በምርመራ ላይ በመሆኑም ተጨማሪ ማብራርያ መስጠት እንደማይችል ገልጿል፡፡
Source: Reporter

9 comments:

Anonymous said...

እግዚያብሄር ነብስሸን በገነት ያኑር፡፡ ለእናቷና ለቤተሰቦቿ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡



Anonymous said...

betam yemiyasazn agatami new!!!! amlak ymuachuan nebs begenet yanur!!!!

Anonymous said...

Deve
Betam Yasazinal.

Anonymous said...

Betam new yemiyasaznew. . . . . . . "GOD KEEP HER SOUL IN TO HEAVEN"

Anonymous said...

touching!! RIP.

Anonymous said...

in the ERA of zero tolerance to mother am sorry to hear this!!!!!!

Anonymous said...

ሰው አንዴ ከሞተ በ|ላ ሊነሳ የሚችለው በጌታ ምጽኣት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን የእግዚአብሄርን ህልውና ከሰዎች ለማስተማር ሲፈልግ አንዳንድ ተአምራትን ሊሰራ ይችላል፡፡ በሰወች ይህ ድርጊት ከተሰራ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡

Unknown said...

egezabeher nebsuan yimar

wyne8945 said...

it seemed so fictional!!

Post a Comment