Saturday, July 14, 2018

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ - እንኳን ደህና መጡ !

(July 14,(ርዕሰ አንቀፅ ))--የኢትዮ- ኤርትራ ያለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የጥላቻ ዘመናት በፍቅርና በይቅርታ የተቀየረበት፤ ከመጥፎ የታሪክ ምዕራፍ ወደ አዲስ የተስፋ፣ የፍቅር እና አብሮ የማደግ ምዕራፍ የተሸጋገርንበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ይሄ ደግሞ የሁለቱ አገራት መሪዎች ባደረጉት ስምምነት ተረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት ቃልኪዳን ከገቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያውያንን ጆሮና ቀልብ ከሳበው መካከል አንዱ ከኤርትራ ጋር ያለውን «ሞት አልባ ጦርነት» ማቆምና ወደ ሰላም ማምጣት መሆኑን ያበሰሩበት ነው። «አለመግባባቱ እንዲያበቃ ከልብ እንሠራለን» ሲሉ አስደማሚ ንግግር አድርገዋል።

በዚህ ታሪካዊ ዕለት በህዝብ እንደራሴዎቹ ፊት ቆመው የተናገሩት በብዙዎች ዘንድ ከባድና አስደንጋጭም ነበር። ይሄ ቀና ሀሳብ ተሳክቶ እናትና ልጅ ፣ ባልና ሚስት፣ እህትና ወንድም በአጭር ጊዜ ይገናኛሉ ብሎ ያሰበ ግን አልነበረም። ያም ሆኖ ግን ከእዚች እለትና ሰዓት ጀምሮ ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይስ አፈወርቂ (ወዲ አፎም) የሚመጣው ምላሽ በጉጉት የሚጠበቅ ነበር።

የኤርትራው ፕሬዚዳንትም ከህዝባቸው ጋር በተሰባሰቡበት የሰማዕታት መታሰቢያ በዓል ላይ ለሰላም ያላቸውን ዝግጁነት ገለጹ። ወደ አዲስ አበባም አንድ ልዑክ በቅርቡ እንደሚልኩ አስታወቁ። በቃላቸውም መሰረት ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ለሰላም ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋገጡ። ይሄ ቀን ለኢትዮጵያውያኑም ሆነ ለኤርትራውያን ጥቁሩ መጋረጃ የተቀደደበት ዕለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የልዑካን ቡድኑን አየር መንገድ ድረስ በመሄድ ማንም ባልጠበቀውና ባልገመተው መልኩ ደማቅ አቀባበል አድርገው ለሰላም፣ ለፍቅር እና ለይቅርታ ያላቸውን ዝግጁነት በአደባባይ አረጋገጡ። ከዛም አለፍ ብለውም ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ደብዳቤ በመፃፍ ጭምር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለሰላምና ለፍቅር ያላቸውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት አስታወቁ።
ጸብ ለማንም የማይጠቅም ይልቁንም ሁለቱንም ሀገሮችና ህዝቦች ለድህነት የዳረገና የሚዳርግ ነው። ስለዚህ አሁን ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ህዝቦች የሚያስፈልገን መጋጨት ሳይሆን በሰላም፣ በይቅርታ እና በፍቅር ተባብረው፣ ተረዳድተውና ተስማምተው በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስክ መሥራት እና ለውጥ ማምጣት ነው።

የደምና የስጋ ትስስር ያለው የኢትዮ - ኤርትራ ህዝብ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ለ20 ዓመታት ተለያይቶ ቆይቷል። ኤምባሲውም ተዘግቷል። አሁን ኤምባሲው ሊከፈት ዝግጅት እየተደረገ ነው። የአየር በረራ ከሰሞኑ እንደሚጀምር ተነግሯል። የኪነጥበብ ባለሙያዎችም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የሚያድሱና የሚያነቃቁ ዝግጅቶችን እያደረጉ ናቸው። ይሄ ሰፊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚፈጥር፤ የተለያየውን፣ የተበታተነውን ቤተሰብ የሚያገናኝና ወደነበረው ቤተሰባዊ ፍቅሩ የሚመልስ እርምጃ ነው።

ለዚህ ለውጥ እና ውጤት የሁለቱ አገራት መሪዎች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል። በኢትዮ ኤርትራ የገባው የሰላም አየር ከሁለቱ አገራት አልፎም ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም የሚኖረው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። አሁን የጸብ ግንብ ፈርሶ አገናኝ የሆነ የፍቅር ድልድይ የተገነባበት ወቅት ላይ ደርሰናል ። የተበጠሰውን የፍቅር ገመድ ዳግም የመለሰ ነው። የጥላቻ ድንበር ፈርሶ የፍቅር ድልድይ ተሰርቷል። ህዝቡም የሰላም አየር መተንፈስ ችሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባደረጉላቸው ግብዣ መሰረት ለሁለት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ ወደ አገራችን መምጣታቸው በሁለቱ መንግሥታትና ህዝቦች መካከል ያለውን መተማመን፣ መተባበርን ይበልጥ የሚያጠናክር እና የሚያረጋግጥም ነው። በቀጣይም የሚሰሩት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሥራዎች ይበልጥ ሰላምን የሚያረጋግጥ፣ ዘላቂ የሆነ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን የሚያጠናክር መሆን አለበት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ወደ አስመራ በአቀናበት ወቅት የነበረው አቀባበል እጅግ ያማረ ነበር። የህዝቡ አቀባበልና በወቅቱ ያሳየው የነበረው እንባ በማንባት የታገዘ የደስታ ስሜት አንድ ህዝብ አንድ ስነልቡና በሁለት አገራት ተከፍሎ መቆየቱን መስክሯል። ፍቅራቸው ከውስጥ የመነጨ መሆኑን ብዙ ማሳያዎች ነበሩ። ይሄ አቀባበል በራሱ ትልቅ ይቅር ባይነትን የሚያሳይ ነው፤ አንድ ህዝቦች መሆናችንን ወደፊትም አንድ ሆነን እንደምንቀጥል ማሳያ ፍንጭ ነው። ኤርትራውያን ጨዋ ህዝቦች መሆናቸውን በተለያየ መልኩ አሳይተዋል። የተራቡት ፍቅር መሆኑንም አስመስክረዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም መንግሥታትና ህዝብን ያስደመመ መልካም ምላሽ አግኝታለች። በዚህም የሰላምና የፍቅር መንገድ ከፍታለች። በመሆኑም ዛሬ ፕሬዚዳንት ኢሳይስ አፈወርቂ ወደ አገራችን ሲመጡ ወደ ሁለተኛዋ አገርዎ ኢትዮጵያ እንኳን ደህና መጡ ብለን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ልንቀበላቸው ይገባል። ኢትዮጵያውያን እንኳን የሚያውቀውን የማያውቀውን እንግዳ ተቀባይ አገር ነውና በዛሬው አቀባበልም ሆነ በቆይታ ጊዜያቸው ቤተሰባዊ ፍቅራችንን እንለግሳቸው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ርዕሰ አንቀፅ)

No comments:

Post a Comment