Tuesday, September 09, 2014

አዲሱን ዓመት ስንቀበል ማተኮር ያለብን

(Sep 09, 2014, ( አዲስ አበባ))--በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መሠረት ከነገ በስቲያ አዲሱ 2007 ዓመት ይገባል። የረጅም ዘመኗ ባለታሪክ ሀገራችን ያሣለፈችውን ረጅም ውጣ ውረድ፣ ወድቆ መነሣትን ሁሉ አሣልፋ ዛሬ የህዳሴ ጉዞዋን ዳግም አጠናክራ የጀመረችበት የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። መላው የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነትና በአብሮነት ህብረብሄራዊ አንድነታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውም የደረስንበትን መልካም ደረጃ አመላካች ነው። እነዚህና ሌሎች በርካታ በጐ ዕድሎች በተፈጠሩበት ሁኔታ አዲሱን ዓመት ስንቀበል እንደ ሀገር ማተኮር ያለብን ጉዳዮችን መጠቃቀስ የዛሬ የጋዜጣችን መልዕክት ማድረግ ተፈልጓል።


የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ መቀጠል

የምንቀበለው አዲስ ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የማጠናቀቂያ ጊዜ ነው። ስለሆነም በዕቅድ ዘመኑ የተያዙ የመሰረተ ልማቶች ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ ተግባራት እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ ሜጋ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ መፈተሽ፣ ወደ ኋላ የቀሩ ካሉ ምክንያታቸውን በዝርዝር መለየትና በቀሪው ጊዜ የሚጠናቀቁበትን ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። ካለፉት አራት ዓመታት የዕቅዱ አፈፃፀም ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመርና ድክመቶችን በማስወገድ በላቀ ሁኔታ መረባረብም ግድ የሚል ይሆናል።

ከዚሁ ተነጥሎ የማይታየው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግብ የማጠናቀቂያ ሥራዎችንም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በብዙዎቹ መመዘኛዎች የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግባለች እንደተባለች ሁሉ ይህንኑ በሚያረካ አኳኋን ለመደምደም መንግሥትና ሕዝብ ከመቼውም በላይ ተቀናጅተው ለልማቱ ሥራ ትኩረት መስጠት አለባቸው።

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሰሶው ምርጫም ትኩረትን ይሻል

ሀገራችን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተችበት አንድ ማሳያ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ነው። ይህ ዕውነት በብዙዎች ትግልና መስዋዕትነት መገኘቱ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረና ብዙኃኑን እያሳተፈ መጥቷል። በተለይ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው አስኳል የሆኑት የመምረጥና መመረጥ የመረጃ ነፃነትና ሃሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት እንዲሁም የመቃወምና ሠላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶች የሌሎችን መብትና ጥቅም በማይነኩበት አኳኋን በህግና ሥርዓት እንዲመሩ መደረጋቸው ሂደቱን በሰከነና በሠለጠነ አኳኋን ለማሳደግ ያስችላል።

ይህን መልካም አጋጣሚ ግን አንዳንድ ወገኖች በዴሞክራሲ ሥርዓቱ ላይ ገደብ የተጣለ አስመስለው እያቀረቡት ነው። በአንድ በኩል ህጋዊና ህገወጥ አካሄድን ለሚከተሉ የፖለቲካ ኃይሎች ዕድል የሚሰጥ አሠራር የለም። በሌላ በኩል ሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ አማራጮችን በሕግ አግባብ ለሚጠቀሙ ሁሉም ኃይሎች የተመቻቸ ዕድል ተፈጥሯል። እነዚህን ሁኔታዎች በመረዳት የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና የሲቪክ ማህበራት 5ኛው ብሄራዊ ምርጫ በተሳካ አኳኋን እንዲጠናቀቅ የየበኩላቸውን ሚና ከወዲሁ መወጣት አለባቸው። ህዝቡም ፍርድ ሰጪ እንደመሆኑ በሠለጠነና በሰከነ አኳኋን ያዋጣኛል የሚለውን ለመምረጥ መዘጋጀት ይኖርበታል።

የመልካም አስተዳደር መጓደልና ሙስናን አምርሮ መታገል ያስፈልጋል

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘ ዓለምአቀፍ ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከአፍሪካ ሀገሮች ዝቅተኛ ሙስና የተፈፀመባት መሆኗን በጥናት አረጋግጧል። ይሄ ትልቅ የምስራች ነው። ግን ሊያዘናጋን የሚገባ ጉዳይ አይደለም። አሁንም ለመልካም አስተዳደር መጓደል ዋነኛ ምክንያት የሆኑ አነስተኛ ሙስናዎች ( petty corruption) የሚፈፀሙባቸው ተቋማትና የሥራ አካባቢዎች እንዳሉ ሕዝቡ ይናገራል። በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በእውቂያና እከክልኝ ልከክልህ ፍትህ አለመዛባቱን አስተዳደር አለመጓደሉን አፅንኦት ሠጥቶ መከታተልና ማረም ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም። መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጀመረው የልማታዊ መልካም አስተዳደር ሀገር አቀፍ ንቅናቄን አጠናክሮ ህዝቡን ያሳተፈ የማሻሻያ እርምጃዎች መውሰድ አለበት። የአሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነትም ሊዳብር ይገባል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በአዲሱ ዓመት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ ይገባል፣ ያስፈልጋል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያችን የሠላም ምድርነቷ ተጠብቆ እንዲዘልቅ የእንግዳ ተቀባይና ኩሩ ሕዝብ ምድርነቷ እንደተከበረ እንዲቀጥል ብሎም ለዜጎቿ ተስማሚ መኖሪያ እንድትሆን ሕዝብና መንግሥት ትኩረት ማድረግ ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ችግሮችን እየቀረፉ፣ በየዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ግን ዜጎች እርስ በርስ በመረዳዳትና በመደጋገፍ ከራስ በላይ ለሀገርና ለወገን በመሥራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ለዚህም ሁሉም በተሰማራበት ሙያ በሥነ ምግባርና በሀገራዊ ስሜት መንፈስ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። መንግሥትና የመንግሥት አካላትም የተጣለባቸውን ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መንገድ በመፈፀም ሀገራችን ወደ መካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ የምታደርገውን ጉዞ ማፋጠን አለባቸው። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሠላም ያልተለያት ኢትዮጵያን ለማረጋገጥም ይበልጥ መትጋት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !

መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment