Monday, September 08, 2014

የዓውዳመት ገበያና ገበያተኛው

 ሆብለን መጣን ሆ ብለን እማማ አሉ ብለን

ሆ ብለን መጣን ሆ ብለን አባባ አሉ ብለን

አበባየሆሽ ለምለም አበባየሆሽ ለምለም......

(Sep 08, 2014, ( አዲስ አበባ)--እንዲህ በሚወደደውና በማይሰለቸው የልጃገረዶች የአበባየሆሽ ጨዋታ እንኳን አደረሳችሁ፡፡ እንኳን አደረሰን እንላለን፡፡ የዘመን መለወጫ ወይም አዲስ ዓመት ከእነስሙ አዲስ ተስፋ አዲስ መንፈስ አለው፡፡በክረምቱ ተራርቆ የከረመው ወዳጅ ከወዳጁ፣ ዘመድ ከዘመዱ ተገናኝቶ ቤት ያፈራውን የዓውዳመት ዝግጅት አብሮ እየተቋደሰ በደስታ ያሳልፋል፡፡ ዓውዳመቱ ከገበያው ግርግር የሚጀምር በመሆኑ ገበያው በራሱ ልዩ ድባብ አለው፡፡ ገዥና ሻጭ በስፋት የሚታደሙበት በመሆኑ ብዙዎች እንደልዩ ትእይንት ያዩታል፡፡ ከሀገር ርቀው የሚገኙ ወገኖች ከሚናፍቋቸው ዓውዳመቶች አንዱ የዘመን መለወጫ የገበያ ግርግር እንደሆነ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ብዙዎችም ወደ ሀገራቸው መምጣት የሚፈልጉት በዓውዳመት ነው፡፡

ቄጤማው፣ አርቲው፣ ጠጅሳሩ፣ የወግርት እጣኑ፣ የፈድሻ በቆሎው፣ ማሽላው፣ እስከእርድ እንስሳቱ በአዘቦቱም የሚቀርቡ ቢሆኑም በዓውዳመት ገበያ ግን ሁሉም ዓይኑን ከፍቶ የሚያያቸው በመሆኑ ቀልብን ይስባሉ፡፡ ታዲያ እንዲህ የሚያስደስቱትን ያህል ግብይቱ ደግሞ የብዙዎችን ኪስ ይፈታተናል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሚጎዘጎዘው ሳር ዋጋ እንኳን አይቀ መስም፡፡ በአዘቦቱ ዋጋ ያላወጣው ቄጤማ በበዓሉ መካካስ አለበት የተባለ ያህል በእስር በእስር ተሸንሽኖ ይቸበቸባል፡፡ በእንስሳት እርድ የሚከበር በዓል በመሆኑም ለነጋዴው ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ገዥው በተባለው ዋጋ ይገበያያል በሚል እሳቤ የሚያዋጣውን ሳይሆን የሚያገኘውን ከፍተኛ ትርፍ አስቦ ነው እንስሳቱን ለገበያ የሚያቀርበው፡፡

«የገበያ ግርግር ለምን ያመቻል» እንደሚባለው ደግሞ አጋጣሚውን ለመጠቀም በገበያና ገበያተኛው መካከል ሆነው ገበያውን የሚሰቅሉት ደላሎችም ለሸማቾች ሌላ ፈተናዎች ናቸው፡፡ በተለይ ከሙከቱና የሰንጋው ገበያ አካባቢ የማይጠፉት ደላሎች ከነጋዴው ቀድመው ገዥውን በመያዝ ያዋክቡታል፡፡« ነቄ» ካልሆኑ ከእውነተኛው ነጋዴ ጋር በአግባቡ ሳይተዋወቁ ሊገበያዩ ሁሉ ይችላሉ፡፡ መኪና ይዘው በዓውዳመት ገበያ ከተገኙማ የሚያግባባዎት ደላላ ይበዛል፡፡ አደናጋሪ ደላላው ግን ሰውንም ሆነ ተሽከር ካሪውን በመለየት ነው የሚገልጸው።

ለገበያ ቅኝት በወጣሁባቸው የመገበያያ ስፍራዎች ነው እንዲህ ያለው ትእይንት ያጋጠመኝ፡፡ ለሥራ የነበርኩበት መኪና መለያ አራት ቁጥር ስለነበር ደላላው በገበያ ክርክራችን ብዙም ሊገፋ አልፈለገም ነበር፡፡እንደገዥ ሆኜ የአንድ ሙክት ዋጋን በጠየኩት ጊዜ ሙክቱ ከሚሸጥበት የአንድ ሺ ብር ብልጫ ተደም ሮባት ነው የተጠራልኝ፡፡ ጠበቅ ስልበት «ድሮም ባላራት ቁጥር ሆነሽ» ብሎኝ ነበር ካጠገቤ የሄደው፡፡ ደላላው ከሄደ በኋላ ከባለቤቱ ጋር ስናወራ ደላሎች በገበያቸው ላይ ያላቸውን ሚና ነበር ያጫወተኝ፡፡ የሚገርመው ነጋዴው ደላላውን ዞር አድርጎ በራሱ መወሰን አለመቻሉ ነው፡፡ በገበያ ቅኝቴ አነስተኛው የበግ ዋጋ 1500ብር ከፍተኛው ደግሞ ከ3ሺ500 እስከ 4ሺ500ብር ነበር፡፡

እስካሁን ባለው ተሞከሮ በዓሉ የቀናት ጊዜ ሲቀረው ዋጋው ይጨምራል፡፡ የበግ ዋጋው ከአካባቢ አካባቢ ይለያያል፡፡ ነጋዴዎቹ ለገበያ የሚያቀርቧቸው የእርድ እንስሳት ከአራቱም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች የገቡ ናቸው፡፡ ተፈላጊነታቸው እንደዋጋቸው ይለያያል፡፡ በውድ የሚሸጡት በብዙዎች ተፈላጊ የሆኑት ብቻ ሳይሆኑ ነጋዴውም ጥሩ ናቸው ብሎ ያመነባቸው ናቸው፡፡ ጥሩ ነዶ ወይም ሥጋ ያላቸው፣ ስጋቸው ጣፋጭ የሆነ ተብለው ተለይተው ለገዥው ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡

ወደ ሰንጋ ተራው ሲሄዱም አስደንጋጭ ዋጋ ይሰማሉ፡፡ ለአንድ በሬ የሚጠራውን ዋጋ ሲሰሙ ጆሮዎትን ይጠራጠራሉ፡፡ ከ12ሺ በታች በሬ አይታሰብም፡፡ በሬ አልነው እንጂ ለዓይን የሚገባ በሬ አይደለም በዚህ ዋጋ የሚጠራው፡፡ ለዓይንም ለእጅም ሞላ ያለው 30ሺ ብርና ከዚያ በላይ ነው፡፡ ብድግ አድርገው በእጅዎ ሲመዝኑት የወፍ ያህል የሚቀለው የዶሮ ዋጋም አነስተኛው አንድ መቶ ብር ነው፡፡ወደ ማጣፈጫው ስንሄድም ቅቤ፣ ሽንኩርት ተራም አምርተን እንዲሁ የተለያየ ዋጋ ነው ያገኘነው፡፡ የበዓል ዋነኛ ምግብ ቅቤም እንደሚመጣበት አካባቢ ዋጋው ይለያያል፡፡ ከፍተኛውን ዋጋ የያዘው የሸኖ ቅቤ ነው፡፡ በኪሎ ከ180 እስከ 190 ብር ነው የሚሸጠው፡፡ የበሳል ቅቤና የለጋ ቅቤ ዋጋም እንዲሁ ይለያያል፡፡ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ግን ከ10 ብር የበለጠ አይደለም፡፡ ( እዚህ ላይ ትክክለኛና ባዕድ ነገር ያልነካው ቅቤ ማግኘቱ ሌላው ፈተና ነው።)

ሽንኩርትም ሁለት ዓይነት ዋጋ ነው ያለው፡፡ «የሀበሻና የፈረጅ»ተብለው ተለይተዋል፡፡ የሀበሻው በመጠኑ አነስተኛ ሲሆን የፈረንጁ ከፍተኛ ነው፡፡ ታዲያ ዋጋቸው የተገላቢጦሽ ነው፡፡ አነስተኛው ወይም ትንንሹ ሽንኩርት በኪሎ እስከ 15 ብር ዋጋ ሲኖረው ትልልቁ እንደጥራቱ 10ብርና ከዚያ በታች እየተሸጠ ነው፡፡ትንንሹ ሽንኩርት አቅርቦቱ አነስተኛ በመሆኑ ዋጋው ከፍ እንዳለ ነው አንዳንድ ነጋዴዎችን ጠይቄ የተረዳሁት፡፡የዶሮ ወጥ ያለእንቁላል የሚታሰብ ባለመሆኑ በገበያ ዝርዝር ውስጥ ይያዛል፡፡ የአንድ እንቁላል ዋጋ 3ብር ነው፡፡ አንዳንድ ድርጅቶች ግን በ10እና በ20ሣንቲም ቅናሽ ይሸጣሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ግብይት በሚካሄድባቸው የሾላ ገበያ፣ በመኖሪያ አካባቢዎች ሰፋ ባሉ ገበያዎች እና በአትክልት ተራ ተዘዋውሬ ገበያውን እንደቃኘሁት ሰፊ የሆነ የዋጋ ልዩነት አላጋጠመኝም፡፡ከአንዳንድ ሸማቾች የሰማሁት አስተያየት ግን ወደመኖሪያቤት ቀረብ ብለው የሚነግዱት መቅረባቸውን እንደጥቅም በማየት ዋጋቸውን በትንሹም ቢሆን እንዲስተካከል ያደርጋሉ። ለገዙት ዕቃ መጓጓዣ ለታክሲ የሚያወጡት ወጪ እና የሸክሙን አድካሚነት በማመዛዘን ከአካባቢያቸው መግዛትን የሚመርጡም አጋጥመውኛል፡፡

ዋና የተባሉትን የዓውዳመት ገበያ ቅኝቴን ስጨርስ አንድ ነገር በአእምሮዬ መጣ፡፡ ዛሬ እስከ ሺ ብሮች በሚደርስ ዋጋ በሚከናወን ግብይትና ከዛሬ አራት አስርት ዓመታት በፊት በሳንቲም ሳይቀር የሚገዙ የበዓልና የዓውዳመት ማክበሪያ ቁሳቁስ ልዩ ግምት መሰጠቱ አኗኗርን ያላመዛዘነ ሆነብኝ። በሳንቲም ግብይት ሲደረግ በነበረበት ዘመን አምስት ሳንቲም እንኳን ከፍተኛ ዋጋ ነበራት፡፡ መገመት ቢያዳግትም ያኔ በአምስት ሳንቲም የሚገዛውን ዛሬ 50ብርና ከዚያ በላይ ልናወጣበት እንችላለን፡፡ ቁምነገሩ ግን ያን ጊዜ እዚህ ግባ የማይባል ገቢ የለውም የተባለው ሰው እንኳን ቤቱ ዓውዳመት ዓውዳመት እንዲል በአቅሙ ይዘጋጃል፡፡ አሁን አሁን ግን ምንም ያህል ሁለንተናዊ ለውጥ እየመጣ ቢሆንም ከኖረው ልማድ ጋር የሚመጣጠን ወጪ ማውጣት ብዙዎችን እየከበደ ነው።

የዓውዳመት ገበያ ለአንዳንዱ ከምግብ ዝግጅትም ያልፋል፡፡የቤት ዕቃ የሚገዙም አሉ፡፡ ከሚገዙት ዕቃዎች ቢላዋ፣ ድስት፣ መክተፊያ እና ጭልፋዎች ይገኙባቸዋል፡፡ የእነዚህ ቁሶች ዘመን ሲቀየር በአዲስ መለወጥ ሁሌም ይገርመኛል፡፡ ሰዎች አዲስ ዓመትን በአዲስ ተስፋ ለመቀበል ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ሊሆን ይችላል በለውጥ ላይ ትኩረት ያደረጉት ብሎ ማየትም በጎ አሳቢነት ይመስለኛል፡፡ አሮጌውን ሸኝቶ በአዲስ ለመቀበል ቤትም ልብስም ይጸዳል፡፡አዲስ ዓመት ሰዎች ያለፈ ዓመት ስኬታቸውን፣ ድክመታቸውን ቆም ብለው ለማየትና በአዲስ ተነቃቅተው የወደፊት ኑሮአቸውን ለመምራት የሚችሉበትን እድልም ይሰጣቸዋል፡፡ለዚህም ነው «በአዲሱ ዓመት ምን አቀድክ ወይም አቀድሽ» የምንባለው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በአስተሳሰብና በተግባር መሻሻልና መቀየር አስፈላጊና ተገቢ ይመስለ ኛል።

የዘመን መለወጫ በዓልን ከሌሎች በዓላት ለየት የሚያደርገው ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ መሆኑ ነው፡፡ከዓውዳመቱ ዝግጅት በተጨማሪ ለልጆች ማስደሰቻ አልባሳት ይገዛል፡፡ የትምህርት ቤት ክፍያ የደብተር ግዥው ሌላም ወጪ ይደረጋል፡፡ ሁሉም የማይቀር በመሆኑ ሰዎች ላላስፈላጊ ብድር ሲዳረጉ ይስተዋላል እና እንደ ጎረቤት ሳይሆን እንደራስ ቤት እያሰቡ በዓሉን መቀበል የቀጣይ ኑሮን ለመታደግም ያስችላል። የገበያ አማራጮችን መጠቀምም ብልህነት ነው፡፡ ለምሳሌም በተመጣጣኝ ዋጋ የተዘጋጁ የእርድ እንስሳን የሚያቀርቡ ተቋማትን በመጠቀም ጊዜንና ወጪን መቀነስ ይቻላል፡፡ ሙክት በጋራ ገዝተው በመካፈል ወጪን የመቀነስ ዘዴ የሚጠቀሙ አንዳንድ ሰዎችም ልምዳቸውን አካፍለውኛል፡፡ዛሬ ከልፋት ለመዳንም አማራጮቹ እየበዙ ነው፡፡ አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች ዶሮ ገዝተው እዚያው ገበያ አስገን ጥለው ስጋዋን ይዘው መግባት ተጀምሯል፡፡ ይህ አገልግሎት መኖሪያቤታቸው ለእርድ ለማይመች ሰዎች መልካም አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡ የሚባርክ ሰው ለሌለውም ችግር ያቃልላል፡፡

በአጠቃላይ ዓውዳመትን በየአቅማችን እያከበርን መጪውን አዲስ ዓመት በደስታ በአብሮነትና በሰላም ማክበር ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያለው የሌለውን እያሰበና እየተረዳዳ በኢትዮጵያዊ ኩሩ ባህላችን መሠረት በዓልን ማክበር ይገባናል። ያስፈልጋ ልም። መልካም አዲስ ዓመት ይሁንላችሁ !
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment