Saturday, December 03, 2011

የግብረሰዶም ነገር

(04 December 2011, Reporter)--በአገራችን የግብረሰዶማውያን ጥፋት እየበረታ መጥቷል፤ በማኅበራዊ ሁኔታቸው ለአጥቂዎች የተጋለጡ ወንዶች ሕፃናት ጉዳቱ ሲደርስባቸው፣ ሴቶች ሕፃናት ሲደፈሩ የሚነሣውን የተቃውሞ ጩኸት የሚያህል ቀርቶ የሚያስታውሳቸውም የለም፡፡ ጥፋተኞቹም በቀላሉ ይታለፋሉ፡፡

ሰሞኑን ደግሞ ኢ-ሕጋዊነቱ እየታወቀ ግብረሰዶም ሊሰብኩ ቀጠሮ የያዙ እንዳሉ ሪፖርተር አስነብቦናል፡፡ ሊያወግዙ የተሰባሰቡ አባቶችም ታግደዋል፡፡ በተለያዩ መስኮች ያሉ ሳይጣናዊና የተደበቁ የሳይጣን አምላኪዎች ሴራ ታሪክ የያዘችውና አሳታሚ ከምትጠብቀው መጽሐፋችን የቀነጨብናትን የጉዳዩን አድማስ በማሳየት ሕዝቡ ከሌባ የሚጠነቀቅበትን ንቃት ትፈጥራለች ካልናት ህልም አጨናጋፊዎቹ ፡ የምስጢር ማኅበራት ታሪክ መግቢያ ከምትል መጽሐፋችን የወስደነውን እንድታነቡ እንጋብዛችኋለን፡፡

በ2ኛ ጴጥሮስ 2፣ 7-8 ጻድቅ የሆነው ሎጥ በአመፀኞች ሴሰኛ ድርጊት (ሰዶምና ገሞራ) እየተሳቀቀ እንደኖረ ያስታውሰናል፡፡ ይህን ያነሣነው በሎጥ ዘመን የነበረውን መንፈሳዊ ዝቅጠት ለማስረዳት ሳይሆን አሁን ያለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ተፈጥሯዊ (ባህላዊ) ሕይወት ሥርአት የሚያናጋው የሰዶማውያን እንቅስቃሴን ለማስረዳት ነው፡፡ አሁን የሚታየው የተፈጥሯዊ ሞራል (ሕግጋት) ጥሰት በሎጥ ዘመን ከነበረው ድርጊት ይበልጥ እንደሆነ እንጂ ሊያንስ አይችልም፡፡

ግብረሰዶማዊነት ማለት የአእምሮ እድገት መቃወስ ሲሆን፣ ከተቃራኒ ጾታ ጥብቅና ቋሚ የሆነ ጥምረት ካለመፍጠር፣ ጣራ የነካ ሴሰኝነት፣ ያለ ወላጅ በተለይ ያለ አባት ከማደግ ወዘተ. የሚነሣ ኢ-ግብረገባዊ (ኢ-ሞራላዊ) ድርጊት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ200 እስከ 230 ሚሊዮን ወንዶችና ሴቶች ግብረሰዶማውያን እንዳሉ ይገመታል፡፡ ይህ ተግባር ብራዚልና አርጀንቲና በመሳሰሉት አገሮች ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በብራዚል በቅርቡ በተካሔደው ፕሬዚዳንታዊ ፉክክር ላይ የቀረቡት እጩዎች በጠቅላላ የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን ሕጋዊ የማድረግ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡ በአፍሪካ በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያ እና አሁን ደግሞ ዘመቻቸውን በከፈቱባት ዑጋንዳ ካለው እንቅስቃሴ ውጪ እንደ ላቲን አሜሪካና ምዕራባውያኑ የገነነ እንቅስቃሴ የለም፡፡ አሁን ባለው “ዘመናዊ ማኅበረሰብ” የሚታየው መጠነ ሰፊ ቁሳዊ ፉክክር ምክንያት የግብረሰዶማውያን ሴራ እሚገባውን ክትትል እንዳይሰጠው አድርጓል፡፡

ከተለያዩ አገሮች ልምድ መማር እንደሚቻለው ችግሩ ሥር ሳይሰድ ካልተገደበ መዘዙ ከባድ ይሆናል፡፡ የምስጢር ማኅበራቱ ሰዎችን ለመቆጣጠር ሰብእናቸውን ከማሳጣት በላይ የተሻለ መሣርያ እንደሌለ ስለሚያውቁ በተለያዩ መንገዶች (በመዝናኛ ወይም በተጣመመ የሰብአዊ መብት ክርክር) እያሳበቡ ግብረሰዶማዊነትን የማስፋፋት ሥራቸውን መገደብ አስቸጋሪ ሁኗል፡፡ የዑጋንዳ ፓርላማ የግብረሰዶማዊነት ችግር በሕግ ለመግታት እየተወያየበት ይገኛል፡፡ (ምንም እንኳ የምዕራባውያኑ ሚዲያዎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በማኩረፍ የዑጋንዳ መንግሥት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ቢከፍቱበትም፡፡)

አልፍረድ ኪንሰይ (Alfred Kinsey)
በሮክፌለር ፋውንዴሽን ድጋፍ ይደረግለት የነበረ አልፍረድ ኪንሰይ የተባለ አሜሪካዊ በምርምር ስም የሠራቸው ሥራዎቹ ለዘመናችን የሞራል ውድቀት የበኩሉን አበርክቷል፡፡ አልፍረድ ኪንሰይ በሕይወት ዘመኑ ይመኝ የነበረው ምድራችን በፍላተ-ስሜት የተሞላች “የወሲብ ዩቶፕያ” ሁና ማየት ነበር፡፡ ኪንሰይ የተወለደው ሰኔ 16 ቀን 1886 ዓ.ም. (ጁን 23 ቀን 1894) ኒውጀርሲ ውስጥ በምትገኘው ሆብከን ነበር፡፡ ኪንሰይ በብዙዎች የሥነ ወሲብ (sexology) ሰው በመባል ይታወቃል፡፡ ኪንሰይ “የወሲብ ትምህርት” መስጠት የጀመረው በ1938 በኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ትምህርቶቹ ዘግይቶ ጋብቻ መመሥረት፣ ከጋብቻ በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም፣ ተማሪዎቹ ግብረሰዶም እንዲፈጽሙ የሚገፋፉና የሚያበረታቱ ነበሩ፡፡

ኪንሰይ ከሕፃንነቱ ጀምሮ የጤንነት ችግር ነበረበት፡፡ ገና ሕፃን እያለ የአጥንት መጣመመም (rickets) እና የመገጣጠምያ (ሪህ) በሽታ (rheumatic fever) ተጠቂ የነበረ በመሆኑ በሕይወት ይቀጥላል ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡ የኪንሰይ አባት የመተዲስት አገልጋይ እና በኋላ በስቴቨን ኢንስትቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ፕሮፌሰር ነበር፡፡ የኪንሰይ አባት ኃይለኛና ግትር አገልጋይ የነበረ በመሆኑ ልጁን በፍርሃትና በሰቆቃ ነበር ያሳደገው፡፡ ነፃነቱን ያገኝ የነበረው ከቤቱ ውጪ በየቀኑ በሚያደርጋቸው ረዥም ጉዞዎች ነበር፤ በእነዚህ ጊዜያትም ነበር በጥቃቅን ነፍሳት ፍቅር የተለከፈው፡፡ ሙያውንም በሚመርጥበት ጊዜ የሚወደውን ሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ለማጥናት ሲመርጥ አምባገነን አባቱ ምሕንድስና ካላጠናህ ብለው ስለጨቀጨቁት በወጣትነቱ ከቤተሰቡ ተቆራረጠ፡፡ በ27 ዓመቱ ጋብቻ የፈፀመ ሲሆን የጋብቻ ምሽቱም በሕይወቱ አዲስ ምዕራፍ የከፈተለትን ክሥተት አጋጥሞታል፡፡ ይኸውም ባለቤቱ “ዝግ የሆነ ገለፈት/ክብረ ንጽሕና” (restrain/imperfect hymen) ነበራት፡፡ ይህ ክስተት እልኸኛው ኪንሰይ በወሲብ ዙርያ መመራመር እንዲጀምር አደረገው፡፡

ኪንሰይ በነፍሳት ላይ ያካበተው እውቀቱ በሰዎች ወሲባዊ ባሕርያት ጥናቱ ላይ መጠቀም ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ነው የሚታወቅበት ተማሪዎቹ ወሲብ እንዲፈጽሙ የሚያደርግበት ቅሌቱ የተጀመረው፡፡ ኪንሰይ በግብረሰዶማዊነት ድርጊት የጨቀየው ሚስት ካገባ በኋላ ሲሆን ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር በሙሉ ወሲብ ፈጽሟል፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ከንድፈ ሐሳብ በበለጠ ጥናቱን በተግባር መደገፍ የጀመረው፡፡ ጥናቱን በሚያደርግበት ወቅት ለሙከራ የሚመርጣቸው ሰዎች ሳይንሳዊነቱን ባልጠበቀ መልኩ ማኅበረሰቡን ጠቅላላ የማይወክሉ ወንጀለኞችንና ግብረሰዶማውያንን ነበር፡፡

ይህም የተጣመመ ኢ-ምክንያታዊ የሆነ ተመሳሳይ ጾታ ወሲብ የመፈጸም ፍላጎት አላቸው የሚለውን ድምዳሜውን ሳይንሳዊ የማድረግ ሙከራው አካል ነው፡፡ አሁንም ያሉት ቅጥረኛ “ሳይንቲስቶች” ግብረሰዶማዊነት ተፈጥሯዊ ለመሆኑ በእንስሳትም ይታያል የሚል መከራከርያ እያነሡ ይገኛሉ፡፡ በእርግጥ በእንስሳት ስለመታየቱ ጸሐፊዎቹ ባያውቁም በእንስሳት ስለታየ ሰዎች ማድረጋቸው ተገቢ አያደርገውም፡፡ ምክንያቱም እንስሳት ልጆቻቸውን ሲበሉ ይታያሉና፤ ሰዎችም ልጆቻቸውን መብላት ይችላሉ እንደማለት የተጣመመ ሳይንሳዊ ያልሆነ አመክንዮ ነውና፡፡

የኪንሰይ ምርምሮች በሐሰተኛ ማስረጃ ላይ ስለመመርኮዛቸው ብዙ ሳይንቲስቶች ያጋልጧቸዋል፡፡ ከነዚህም መሃል ጁዲዝ ሪዝማንን (Judith Riesman) መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኪንሰይ ጥያቄ ካደረገላቸው 1 ሺሕ 800 ምልምሎች አብዛኞቹ የከፍተኛ ሴሰኝነት ችግር ያለባቸው ነበሩ፡፡ አንደኛው ስህተቱ እነዚህ የሐሰት ናሙናዎች አጠቃላይ የዓለምን ሕዝብ ይወክላሉ ማለቱ ነው፡፡ በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ ያሳተማቸው መጻሕፍቱ አሁን ለተንሰራፋው ማኅበራዊ ሴሰኝነት ደጋፊ መሠረት የሆኑ ናቸው፡፡ የኪንሰይ ጥናቶች በታይም፣ ላይፍ፣ ሉክ፣ እና ማክኮልስ ከዚያም በፕለይ ቦይ መጽሔቶች ሰፊ ሽፋን በማግኘት የብዙኀንን ልቦና ሰርቀዋል፡፡

ከመጽሔት ሽፋን በተጨማሪም የሮክፌለር ፋውዴሽን ሰፊ ድጋፍ ያደርግለታል፡፡ በሮክፌለር ፋውዴሽን ድጋፍ የ700 ገጽ “Sexual Behavior in the Human Male” የተሰኘውን መጽሐፉን አሳትሞለታል፡፡ ይህ መጽሐፍ በተለመደው ስልታቸው በማስተዋወቅ፣ በስፋት በማስወራት ከፍተኛ ሽያጭ ጣራ ላይ እንዲወጣ አድርገውታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “Sexual Behavior in the Human Female” የሚል አሳትሟል፡፡

ይህ መጽሐፉ ከሕዝብ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስከተለበት ሲሆን፣ ድጋፍ የሚያደርጉለት ስውር እጆች ግን ቤተሰባዊ የማኅበረሰብ መሠረት የማፍረስ እቅዳቸው እንደመሆኑ የሚገታቸው አልተገኘም፡፡ ብዙዎች የሴራ ተመራማሪዎች የኪንሰይን አላማና ሥራ ከጋርዮሻውያን ሴራ ጋር ያገናኙታል፡፡ በ1950ዎቹ በአሜሪካ ቁልፍ ሥልጣን የያዙ ድብቅና ሰርጎገብ ጋርዮሻውያን ላይ ዘመቻውን ከፍቶ የነበረው የምክርቤት አባሉ ሴናተር ጆ ማካርቲ (Joe McCarthy) ስለ ኪንሰይ ምርምር ሲናገር የሥነ ምግባር ጥሰት በማስፈን ጋርዮሻውያን ማምጣት ለሚፈልጉት ሙሉ ቁጥጥር በር ከፋች ናቸው ይላል፡፡

1954 የሮክፌለር ፋውንዴሽን በኪንሰይ ጥናት ዘዴ ላይ ስህተት ስላገኘሁበት ድጋፌን አቁሚያለሁ ያለበት ዓመት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ግድፈቱን መጀመርያውኑ ያውቁት እንደነበር ጥያቄም የለውም፡፡ ይህ የሕዝብ ቁጥጥር በሚለው ምዕራፍ ከተዳሰሰው ጋር የሚሔድ እንቅስቃሴ ነው፡፡

ከሮክፌለር ፋውዴሽን ጋር “ከተቆራረጠ” በኋላ በአካላዊና አእምሯዊ ስቃይ ደስታን የማግኘት ሥነልቦናዊ ሕመም (masochism) ማጥናት ጀመረ፡፡ በዚህን ወቅት ክፉኛ በእንቅልፍ እጦት ይሰቃይ ነበር፡፡ በስተመጨረሻ በ62 ዓመቱ በልብ ሕመም ተጠቅቶ ሕይወቱ አለፈች፡፡ ስለዚህ ሰው እውነተኛ ታሪክ ማወቅ ለሚሹ የጁዲዝ ሬይዝማን (Judith Riesman) ጽሑፍን ማንበብ ይችላሉ፡፡ ከኤድዋርድ አኬላ (Edward E. Eichel) ጋር የጻፉት “Kinsey, Sex and Fraud” ተጠቃሽ ነው፡፡

የግብረሰዶማውያን ጦርነት
በምዕራቡ ዓለም ግብረሰዶማውያን ቁልፍ የመንግሥት ቦታዎችን (አስተዳደራዊ፣ ወታደራዊ፣ ፍርድቤት፣ ስለላ ተቋማትን) በበላይነት ይዘው ይገኛሉ፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በምስጢር ማኅበራቱ ስውር እጅ አማካይነት ነው፡፡ የዛሬ ሃምሳ ዓመት ገደማ ስሙን መጥራት አሳፋሪ የነበረው ከስንት ዘመቻ በኋላ ከግብረሰዶማውያን ጥያቄ አልፎ ማንኛውም ሰው 18 ዓመት ሳይሞላው ጾታው ወንድ ወይም ሴት የሚለው መወሰን የለበትም የሚል ክርክር የግብረሰዶማውያን መብት ተሟጋቾች እያቀነቀኑ ይገኛሉ፡፡

ግብረሰዶማዊነት ከአጭበርባሪው ኪንሰይ በፊት የዕድገት መዛባት ችግር ተደርጎ ይቆጠር የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን እንደ ተፈጥሮ ውጤት እየተነገረ ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ በ1963 የNew York Acadamy of Medicine Committee on Public Health ግብረሰዶማዊነት በሽታ አይደለም ብሎ ቃሉን ያስተላለፈበት ጊዜ ነው፡፡ ድርጅቱ የአቋም ለውጥ ለማድረጉ እንደ ኪንሰይ ያሉ የተጋለጡና የሚደጉሟቸው ያመኑበት “ሳይንሳዊ ግኝት” አሳምኗቸው ሳይሆን፣ አሁንም ከበስተጀርባ የሚሠሩ ኃይሎች ውጤት እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ምንም እንኳ በምስጢር ማኅበራቱ ኃይል ሴራውን የሚቃወሙ ተቋማትን ሰርጎ በመግባት አሊያም በማስፈራራት ቢወጓቸውም፣ እስከአሁን ድረስ ግብረሰዶማዊነት የሥነልቦና ችግር እንጂ ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ የሚያረጋግጡ ተቋማት አሉ፡፡ ከነዚህም አንዱ The Group for the Advancement of Psychiatry ይገኝበታል፡፡ በ1973 ከከፍተኛ ዘመቻ፣ ሰላማዊ ሰልፍና አመፅ በኋላ የአሜሪካ የሥነ ልቦና ሙያተኞች ማኅበር ለመጀመርያ ጊዜ በግብረሰዶም ላይ ያለውን አቋም እንዲቀይር ተደረገ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ማድረግ ያለብን ግብረሰዶማውያንን አይዟችሁ የሚሏቸው ከበስተጀርባ የሚያደራጇቸው፣ የሚያሰለጥኗቸውና የሚያሰማሯቸው ኃይሎች እንዳሉ ነው፡፡ ያለዚህ እንዲህ ጥያቄያቸውን አንዴ ሰብአዊ ሌላ ጊዜ ፖለቲካዊ መልክ እያስያዙ በሕትመትና በመዝናኛ ዘርፍ ዓለምን ማጥለቅለቅ ባልቻሉም ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ግብረ ሰዶማዊ ጥፋትን የሚያመለክቱ ጥቅሶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ  በማውጣት የተቆነጻጸለ፣ የተበጣጠሰ ‹‹ብጡል መጽሐፍ ቅዱስ›› እያሰራጩ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ብዙ ጥቅሶች ከብሉይ ኪዳንና ከሐዲስ ኪዳንም የተቀነሰበት ጎደሎ መጽሐፍ ነው፡፡ ይህን የሚያሳትሙትም ግብረሰዶማውያን ናቸው፡፡

የግብረሰዶማውያን ጥምረት
በ1988 ከዓለም የግብረሰዶማውያን ተቋሞች የተውጣጡ 175 የግብረ ሰዶማውያን መብት ተሟጋቾች ለዋሽንግነተን ዲሲ ቅርብ በሆነችው ቨርጂንያ ግዛት በምትገኘው ዋረንቶን ውስጥ ደማቅ የሆነ “የጦርነት ጉባኤ” / “War Conference” በሚል ስብሰባ ያደረጉበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ውሳኔ መሠረት ሃርቫርድ ውስጥ የተማሩት የማኅበራዊ ሳይንቲስትና የግብረሰዶማውያን መብት ተሟጋች የሆኑ ማርሻል ኪርክ እና ሃንተር ማድሰን አማካይነት “የግብረሰዶማውያን መግለጫ” (Homosexuals Manifesto) እውን ሆነ፡፡

በስብሰባው ከተደመጡትና በመግለጫው ከሰፈሩት ጽሑፎች “…ከዚህ በፊት የነበሩት ያረጁ ዘዴዎች በጥንቃቄ በተቀመሩ የሕዝብ ግንኙነት ፕሮፖጋንዳ በመተካት… ለቀጣዩ የግብረሰዶም አብዮት መድረክ ለምናደርገው ጦርነት በአክራሪ [የተፈጥሮ ሕግን የሚጠብቁ] ተቃዋሚዎች ላይ ፍጹም የሆነ ድል ለመቀዳጀት የሚያስችለን መሠረት መጣል ይሆናል፡፡” የመግለጫው ጸሐፊዎች በመቀጠል “ማንኛውም ዜጋ ከአስር ሰዎች በአንድ ወይም ሁለቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የመፈጸም ፍላጎት መኖሩን የሚክድ … በጠና የታመመ መሆን አለበት፡፡” ይላሉ፡፡ ይህ አይነቱ አፍራሽ አካሔድ በተጋለጡት የአልፍረድ ኪንሰይ ጥናቶች መሠረት ያደረጉ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡

ይህን የግብረሰዶማውያን ጥቃት የሚገልጹ ሦስት ወሳኝ ቃላት ናቸው፡- ማደንዘዝ --Desensitization፣ ማፈን --Jamming እና መቀየር --Convert ይሏቸዋል፡፡ ክሪክና ማዲሰን እንደጻፉት ከሆነ የቃላት ስያሜን በመቀያየርና በማምታታት እቅዳቸው ውስጥ የተካተቱትን ዘመቻዎች እውን ማድረግ ወሳኝ ነው ይላሉ፡፡

በነርሱ ቋንቋ ማደንዘዝ ማለት በተቻለ መጠን ትንሽ ተቃውሞ ሊያሥነሣ በሚችለው ስልት (በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በስደተኞች ጥያቄ፣ የብዝኀ ባህል ጥያቄዎች) ጋር እያስታከኩ የግብረሰዶም ፕሮፓጋንዳ መንዛት ማለት ነው፡፡ ዓላማው ሰዎች በቀጥታ ግብረሰዶማዊ ድርጊትን እንዲቀበሉ ሳይሆን በተዘዋዋሪ አርእስቱን በተደጋጋሚ በማቅረብ ችላ እንዲባልና አስፈላጊው ትኩረት እንዳያገኝ ማድረግ ነው፡፡ ስያሜያቸውም ግብረሰዶም በሚለው ፈንታ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት (ሆሞሴክሽዋል)፣ ተጎጂ ሰለባ በሚለው ምትክ “ጌይ” (ደስተኛ) እያሉ መጥራታቸው ይህንኑ ያንፀባርቃል፡፡

ሁለተኛው ስትራቴጂያቸው ማፈን ነው፡፡ ይህ የዘመቻው ደረጃ  ደግሞ የሚያነጣጥረው የግብረሰዶማውያን አውዳሚና እኩይ ተግባር በሚቃወሙት ላይ ሥነልቦናዊ ሽብር ከመፍጠሩ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡  በመግለጫው በእርግጥ አክራሪው (የተፈጥሮ ሕግጋት አክባሪው) እንዲያምን ማድረግ አይጠበቅብንም፤ በሒደት ለዘብተኞቹ አክራሪውን እንዲንቁት ይደረጋል፤ ዋናው ነገር በየትኛውም መንገድ ተጽዕኗችን እውነት ሆነ ትክክለኛ አመክንዮ ባይከተልም ድል ማድረግ መቻሉ ነው፤” ይላል፡፡ ለማፈን ዋናው መሣርያ “መቻቻል” የሚለው ዘመቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ በተቃራኒ የቆመውን መቻቻል የማያውቅ “Homo hatred” “የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ጠላት” የሚል ስም ይሰጡታል፡፡ ከሃይማኖት በመነሣት የሚጠላቸውን “ሃይማኖታዊ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ጠላት” ይሉታል፡፡ ሌላኛው እንደነሱ የሆነ ግን እንቅስቃሴያቸውን የማይደግፈውን “gay homophobes” ይሉታል፡፡ የመጀመርያ ሁለቱ ልክ የአይሁዶች ሴራን የሚያጋልጥ ፀረሴም እንደሚሉት ሲሆኑ፤ የመጨረሻው ደግሞ አይሁድ ሆኖ የአይሁድ ዘር የበላይነትን የማያምን “ራሱን የሚጠላ አይሁድ” ብለው እንደሚሰይሙት ማለት ነው፡፡

ሦስተኛው የግብረሰዶማውያን ስትራቴጂ መቀየር ነው፡፡ ይህን ቅየራ በማኅበረሰቡ እውን ለማድረግ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ በሚፈጥሩ ነገሮች፣ የሚቃወሙትን በመወንጀልና ተቋማዊ ማኀበራትን በማደራጀት ሲሆን፣ ይህም የመግለጫው ጸሐፊዎች “ተራው አሜሪካዊ ዜጋ ስሜቱ፣ አእምሮውና ፈቃዱን ባቀድነው መሠረት ሥነልቦናዊ ጥቃት በመፈጸም መቀየርን ማምጣት ይሆናል፡፡ ሚዲያውን በመጠቀም ለማኅበረሰቡ ፕሮፓጋንዳ በመቀለብ የሚከናወን ነው፤” በዚህ የቅየራ ስልት መሠረት “አክራሪው የሚያውቃቸው በሙሉ በተለይ ግብረሰዶማዊ ከሆኑት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲመሠርቱ በማድረግ ማሳየት” ይህ ተፈጥሯዊ ሕግ ጠብቆ የሚሔደው ሰው ለዘብተኛ አቋም እንዲኖረው ለማድረግ ነው፡፡

የእንስታውያን ዘመቻ
አፍላጦን/ፕላቶ ሪፐብሊክ በሚለው መጽሐፉ፣ “የተሟላ ተምኔታዊ ዓለም” (proper utopia) ለመፍጠር መሪዎች እንደ አማልክት ፍጹም ሆነው የመቅረብ አስፈላጊነቱን ያስገነዝባል፡፡ ይህም እውን የሚሆነው ቁጥጥርንና ማጭበርበርን በተራቀቀ መልኩ በማንገሥ ነው፡፡ ፕላቶ “ፈላስፋው”፣ “እውነት የተጠማው” ሕዝብን ለማስተዳደር ማጭበርበርን ይመክራል፡፡ በአሁኑ ዘመን በፕላቶ ስሌት በማጭበርበር እየሠሩ ያሉት የእንስታውያን እንቅስቃሴ (feminist movement) እየተባለ የሚታወቀው ነው፡፡ ይህ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለና በተለያዩ ሰበብ አስባቦች የነገሠ እንቅስቃሴ ነው፡፡

እንስታውያን ማለት ከወንድ ጨቋኝነት የተነሣ ካልሆነ በስተቀር በወንዶችና ሴቶች መካከል በተፈጥሮ ባሕርይ ምንም አይነት ልዩነት የለም የሚል ፍልስፍና ነው፡፡ የዚህ ፍልስፍና አስኳል የሆነው የእኩልነት ጥያቄ ተፈጥሯዊ ባሕርያት ማእከል ያደረገ ሳይሆን፣ የቤተሰብን ጽንሰ ሐሳብ ደብዛውን ለማጥፋት በናፍቆት በሚጠብቁት የምስጢር ማኅበራት ፍልስፍና ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ ይህ እንስታዊ አጀንዳ ወንዶች ጨቋኞች ሴቶች ደግሞ የዚህ ሰለባ ናቸው ከሚል አስተሳሰብ ውጪ ሌላ ምንም አይቀበልም፡፡ ይህ የእንስታውን አስተምህሮ ከሁሉም ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ እንስታውያን የአንድ ነገር ትክክለኛነት የሚረጋገጠው አንድ ሰው ያለምንም ገደብ እስከፈለገው ድረስ በመተግበር ነው የሚል አውዳሚ መርሕ ያምናሉ፡፡

ይህ የጭቆና ሰለባ የሚለው የእንስታውያን አመክንዮ እጅግ አማላይና አሳሳች ፈጠራ ነው፡፡ የእንስታውያን እንቅስቃሴ ሁለቱንም ወንዱንም፣ ሴቱንም የሚጎዳ ነው፡፡ ለእንስታውያን በወንድና በሴት መካከል ያለው የሥራ ድርሻ፣ ችሎታ፣ ሥነልቦና ወዘተ. ልዩነቶችን አይቀበሉም፡፡ የሥነሰብ (አንትሮፖሎጂ) ተመራማሪዋ፣ ማርክሲስት እና እንስታዊ የሆነችው ኤሊኖር ሊዮኮክ (Eleanor Leocock) በዚህ አቋማቸው ከሚታወቁት ተጠቃሽ ነች፡፡

ሥነ ማኅበራዊው (ሶሽዮሎጂስቱ) ስቲቨን ጎልድበርግ (Steven Goldberg) ባደረገው ጥናት መሠረት ከአጠቃላይ የሥነ ማኅበራዊ መጻሕፍት ከ38ቱ ውስጥ 36ቱ የሚያተኩሩት የወንድና ሴት ሚና ቅየራ (role-reverse/ role-disorientation) ላይ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ እነዚህ መጻሕፍት በወንድና በሴት መካከል ያሉት ልዩነቶች ተፈጥሯዊ ሳይሆኑ ማኅበረሰቡ ያመጣቸው ተጽዕኖዎች ውጤት ወይም አካባቢያዊ ግፊት የፈጠራቸው ናቸው ይላሉ፡፡ የወንድ ልጅ አባታዊ የመሪነት ሚናና የሴት ልጅ ባልና ልጅን የመንከባከብ ኃላፊነት እሚባል ነገር አይዋጥላቸውም፡፡ ሌላው ዋናው መከራከሪያቸው ኢኮኖሚያዊ አዋጭነትን ያስታከከ ነው፡፡ ሴቶች በተፈጥሯቸው የሚማረኩት በራሱ በሚተማመን፣ ኩሩና ኃያል ወንድ ነው፤ ይህም ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ሚና በግልጽ ያሳያል፡፡ እምነቷን መለገስና መማረክ አንድ ሴት ለአንድ ወንድ መሪነቱን የምታፀድቅበትና የምታፈቅርበት መንገድ ናቸው፡፡ ወንድ በተፈጥሮው መሪነትን ሲሻ በአንፃሩ ሴት ልጅ ፍቅርን ትወክላለች፡፡ ይህ የመሪነትና ፍቅር ልውውጥ የተቃራኒ ጾታ ጋብቻ መሠረት ነው፡፡

እንስታውያን ወንዶችና ሴቶችን አጋር ጥንዶች አድርገው ሳይሆን የሚመለከቱት ሴቶች ለወንድ ልጅ ፍላጎት ተገዢ የሆኑ መገልገያና የወሲብ ማሽን የተደረጉ ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ እንስታውያን ተፈጥሯዊው የወንድና ሴት ግንኙነት የግጭት ሳይሆን የውሕደት መሠረትነቱን በመካድ ማኅበረሰባዊ አጋጣሚዎች ከፈጠራቸው ቀውሶች ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ስቲቨን ጎልድበርግ ምላሽ ሲሰጥ “…ስሕተቱ ያለው ማኅበረሰባዊ ሁናቴ/ አካባቢን (social environment) በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ ያልሆነ፣ በራሱ የቆመ ቀመር (independent variable) አድርገው መመልከታቸው ነው” በማለት ነበር፡፡ ከተፈጥሮ ሕግጋት መጣስ ባሻገር ቅጥረኛ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ካልሆኑ በስተቀር በወንድና ሴት መካከል ያለውን የሥራ፣ የአካላዊ ቅርጽና ባሕርያት፣ የሥነልቦናዊ ባሕርያት የተለያየ መሆን የማይቀበል የለም፡፡ በሌላ አነጋገር እንስታውያን የሆርሞን ሚናን አይቀበሉም፡፡

እዚህ ጋ ቀላል ጥያቄ ለእንስታውያን ቢጠየቅ ውዝግቡን ይፈታዋል፡፡ ሴቶች “ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው” እንዲቀጭጭ ወይም በሕይወት መስክ ያላቸው ሚና እንስታውያን እንደማይቀበሉት አይነት እንዲሆን ያደረገው ማኅበራዊ ሁናቴው ብቻ ከሆነ፤ በአፀያፊና ስህተት ድርጊት ጾታቸውን የሚቀይሩ ሰዎች ለምን በቴስተስትሮጅንና በኦስትሮጅን ሆርሞን በመርፌ መጠቅጠቅ አስፈለጋቸው?

የእንስታውያንና ግብረሰዶማውያን አፀያፊ የማታለያ ተግባሮች አብዛኛውን የዓለም ማኅበረሰብ በተለይም ዘመናዊውና ምሁሩ ሊበራል (ልል) ዘንዳ ተቀባይነትን እያገኙ ነው፡፡

ሌላው የእንስታውያን ጩኸት እስከአሁን የመጣንበት የወንድና የሴት ግንኙነት፣ የሥራ ድርሻ፣ አባታዊነትና እናታዊነት ሒደት የወንዶችን ራስ ወዳድነት ለማርካት ሲባል ሴቶች የወደቁበት መንገድ ነው ይላሉ፡፡ ታዋቂው ስዊዘርላዳዊ ሳይንቲስት ጆን ጃኲ ባቤል በ5 ሺሕ 600 ዓመታት የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ 14 ሺሕ 500 ጦርነቶችን ሲፋለም በዚህም እስከ 3.5 ቢሊዮን ሰዎች እንደሞቱ በጥናቱ ይገምታል፡፡ ይህ አሁን ካለው የዓለም ሕዝብ ግማሹን ያክላል፡፡ ታዲያ ከዚህ ፍልሚያ ከ95% በላይ ሰለባ የሆኑት ወንዶች ናቸው፡፡ ወንዶች በራስ ወዳድነታቸው የፈጠሩት ታሪክ ነው ከተባለ እንዴት እንዲህ ራሳቸውን የሚጎዳ መንገድ ይከተላሉ?

እዚህ ጋ ማስታወስ የምንፈልገው ታሪክ አለ፤ በ2003 በኛ አቆጣጠር በዓለም መገናኛ ብዙኀን ወንድ ልጅ በአሜሪካ ልጅ ተገላገለ የሚል አስደማሚ ዜና ተሰምቶ ሲያስገርመን ነበር፤ ከአርእስተ ዜናው በስተጀርባ ግን ልጅ የተገላገለው ሰው ወንድ ሳይሆን ሴት መሆኗ ይደረስበታል፡፡ በቀዶ ጥገና ጡቶቿን አስወግዳ የወንዴ ሆርሞን እየተወጋች ፂም ፊቷ ላይ ያበቀለች፣ ማሕፀኗን በቀዶ ሕክምና ያላስወገደች ሴት፣ በመርፌ የወንድ የዘር ፍሬ ተቀብላ የፀነሰች ነች፡፡ ግማሽ ታሪክ እየተናገሩ ማወናበድ የፕሮፓጋንዳ ውጊያቸው አካል ነው፡፡ የአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ አቀንቃኞች ብርቅዬ የሆነችው ኦፕራ ዊንፍሬም በኦፕራ ቶክ ሾው ይህችን ሴት አቅርባ ቃለ መጠይቅ በማድረግ የተለመደው የአዲስ ዘመን እንቅስቃሴ አስተዋጽዖዋን አበርክታለች፡፡ የኦፕራ ሾው በአዲስ ዘመን ፍልስፍና የሚመራ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዎቹን አቶ ተክሉ አስኳሉና ግደይ ገብረኪዳን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡፡ ( seeallconcern@yahoo.com ወይም በfacebook: illuminati conspiracy study group))
Source: Reporter

3 comments:

Giday Gebrekidan said...

የላይኛው በሪፖርተር የወጣው ፅሁፋችን ያስደሰተው አንባቢ ስለ አለም አቀፋዊ ሴራዎች ተጨማሪ ማንበብ ከፈለገ የሚከተሉትን ሁለት መጣጥፎች ማንበብ ይችላል፡
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/317-world/4323-2011-12-03-08-42-35.html#disqus_thread (በአለም አቀፍ ፋይናንስ ቀውስ ዙርያ)
http://www.ethiopianreporter.com/component/content/article/303-commentary/2241-2011-06-04-09-58-25.html#disqus_thread (በገንዘብ አቅርቦትና የዋጋ ግዥፈት ዙርያ)
ፅሁፎች ማንበብ ይችላል፡፡ መፅሃፋችንን በማሳተም መተባበር የምትፈልጉ በተጠቀሰው አድራሻችን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

Meron Aberham said...

እግዚአብሔር ምህረቱን ይስጠን። ከእደዚህ አይነት በሽታ ያዉጣን

Anonymous said...

አዲስ ብሎግ በአማርኛ ስለጀመርኩኝ ለበለጠ መረጃ እና ተጨማሪ ፅሁፎችን ለማግኘት ይጎብኙን :
http://antiglobalconspiracy.blogspot.com/

Post a Comment