Sunday, April 07, 2013

የመለስ ፋውንዴሽን ተመሠረተ

(Apr 06, 2013, (አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ))--የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በታጋይነትና በአመራር ዘመናቸው በአገር፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያከናወኗቸውን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ለመዘከር፤ አስተሳሰባቸውንና አስተምህሮ ለማስቀጠልና ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚረዳው «መለስ ፋውንዴሽን» ተመሰረተ፡፡ ፋውንዴሽኑን የሚመሩ የቦርድ አባላት ምርጫም ተካሂዷል፡፡



ትናንት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተካሄደው መስራች ጉባዔ የአቶ መለስን ህልፈተ ሕይወት ተከትሎ ራዕያቸውን ለማስቀጠልና አስተማሪ ሰብዕናቸውን ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል በስማቸው ፋውንዴሽን እንዲቋቋም በተወሰነው መሰረት አስፈላጊው ዝግጅት በተሟላ መልኩ መጠናቀቁ በጠቅላላ ጉባዔው ታምኖበትና ውይይት ተደርጎበት «መለስ ፋውንዴሽን» በይፋ ተመስርቷል፡፡ 

ፋውንዴሽኑን ለመመስረት በተቋቋመው «የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሌጋሲ ኮሚቴ» አማካኝነት የሚያስፈልገው የዝግጅት ሥራ ባለፉት ሰባት ወራት ሲከናወን መቆየቱን የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አዲሱ ለገሰ ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው የአቶ መለስን የትግል አስተዋፅኦና ምጡቅ ሰብዕና ዋነኛ የሥራው መነሻ በማድረግ የተጣለበትን ኃላፊነት በመወጣት ለፋውንዴሽኑ ምስረታ መድረሱን አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የመለስ ፋውንዴሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ ህግ በማዘጋጀት ለበላይ አካል በማቅረብ እንዲመከርበትና እንዲፀድቅ አድርጓል፡፡ ከዚህም በተጓዳኝ ለፋውንዴሽኑ ምስረታ የሚረዱ ልዩ ልዩ የአሰራር ማኑዋሎችና መስራች ጉባዔውን ለመጥራት የሚያስችሉ ተግባራት በኮሚቴው ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡

በጉባዔው እንደተገለፀው «የመለስ ፋውንዴሽን» አቶ መለስ ለአገራቸው፣ ለአፍሪካና ለዓለም ላበረከቱት ታላቅና ድንቅ አስተዋጽኦ መነሻ የሆኑትን እምነቶች፣ ፍልስፍናዎችና ጉልህ ሥራዎቻቸው በአግባቡ ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ የአስተሳሰብ ግንባታ ግብዓት ሆነው የሚያገለግሉበትን ሚና ይጫወታል፡፡ 

በአቶ መለስ አስተምህሮ ዙሪያ የጥናትና ምርምር ማዕከል ለማቋቋምና ለመደገፍ፣ ነፃ የትምህርት ዕድል ለመስጠት፤ የአቶ መለስ ጽሑፎችን መድብል ለማዘጋጀትና ለማቅረብ፣ ቤተ መጻሕፍትና የአረንጓዴ ልማት አካባቢ መፍጠሪያ ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአገልግሎት ማዕከል ማቋቋምና መሰል ተግባራትን ያከናውናል፡፡ 

ጉባዔው መለስ ፋውንዴሽንን ለማቋቋም የፀደቀውን አዋጅ መሠረት ባደረገ መልኩ ፋውንዴሽኑን የሚመሩ የቦርድ አባላትን መርጧል፡፡ በእዚህም መሠረት በቦርዱ ከሚካተተቱ አራት የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች በተጨማሪ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ ዶክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም፣ አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ ወይዘሮ አስቴር ማሞ፣ አቶ አብዲ ዑመር መሃመድ፣ አቶ አህመድ ናስርን መርጧል፡፡

ወይዘሮ አዜብ መስፍን የቦርዱ ፕሬዚዳንት፤ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ቦርዱን ለመምራት ተመርጠዋል፡፡ የፋውንዴሽኑ የሥራ ዕቅድ ለጉባዔው ቀርቦ ፀድቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment