Sunday, April 07, 2013

ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ጋር ይጫወታሉ

(Apr 06, 2013, (አዲስ አበባ, ኢትዮጵያ))--አፍሪካ ኀብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል በማስመልከት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ( ዋሊያዎቹ ) ከግብጽ አቻው ( ፈርዖኖቹ ) ጋር በአዲስ አበባ ስቴዲየም የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ግንቦት 17 ቀን 2005.ም የሚደረገው ይህ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላሉበት ጨዋታዎች ዝግጅት ጠቀሜታ እንዳለውም ተገልጿል።


የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ኅብረት ምስረታ50ኛ ዓመት በዓልን በማስመልከት የአህጉሪቱ የቀድሞ ኮከብ ተጫዋቾች ተሰባስበው እንዲጫወቱ የአፍሪካን እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን ( ካፍን) ጠይቋል። ይሁንና ተጫዋቾቹ በተለያየ አካባቢዎች ስለሚኖሩ እነርሱን ማሰባሰብ አስቸጋሪ መሆኑ ታውቋል። ስለዚህ የኮንፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ «የካፍ መስራች አገሮች ጨዋታውን እንዲያካሂዱ» የሚል የመፍትሔ ሐሳብ አቅርቧል።

የካፍ መስራች ከሆኑት «ከኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን መካከል ማን ከማን ይጫወትየሚለውን አገሮቹን አወያይተው እንዲለዩ ለኮንፌዴሬሽኑ ዋና ጸሐፊ ኃላፊነት መስጠቱን አስታውሰው፤ ጨዋታው የሚካሄደው ኢትዮጵያ ውስጥ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለጨዋታው ቅድሚያ ተመራጭ ልትሆን መቻሏን አቶ ሳህሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጨዋታው አስተናጋጅነቷ መመረጧን ተከትሎ ከማን ጋር መጫወት እንደምትፈልግ ከዋና ጸሐፊው ለፌዴሬሽኑ በቀረበለት የምርጫ ጥያቄ መሠረት፤ «ጨዋታው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መለኪያነት ጠቃሚ ስለሚሆንና ለጨዋታው ድምቀት ሲባል የግብጽን ብሔራዊ ቡድን መርጠናል » ብለዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር በተደጋጋሚ መጫወቱ ይታወሳል።

« የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ሲባል ግን ዋናው ብሔራዊ ቡድን መሆን አለበት። ካልሆነ ግን እኛም እንደማንስማማበት በገለጽነው መሠረት ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ግንቦት 17 ቀን 2005 .ም አዲስ አበባ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ » ሲሉ አቶ ሳህሉ ገልጸዋል። ዋሊያዎቹ ለጨዋታው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና የቴክኒክ ኮሚቴው እንዲያውቁት መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የአፍሪካ ኀብረትን 50ዓመት ክብረ በዓል ለማክበር አዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት መሪዎች አዲስ አበባ ስቴዲየም ተገኝተው ጨዋታውን እንደሚመለከቱ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤«ጊዜው ሲቃረብ ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽንና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ልዩ ዝግጅት ይደረጋል» ብለዋል።

ዋሊያዎቹ ከፈርዖኖቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ከበዓል ማድመቂያነት ባለፈ ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች አቋሙን ለመፈተሽና ለማስተካከል ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም አቶ ሳህሉ አስረድተዋል።

«ፕሪሚየር ሊጉን በሰኔ ወር ማጠናቀቅ እንፈልጋለን» ያሉት አቶ ሳህሉ ፤ ሰኔ ወር ላይ ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ከቦትስዋናና ከደቡብ አፍሪካ ጋር እንደሚደረግ ተናግረዋል። እንዲሁም በአፍሪካ አገሮች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ( የቻን ) ውድድር ከሩዋንዳ ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ ስለሚደረግና ያለው ጊዜ የተጣበበ ስለሚሆን ከግብጽ ጋር የሚካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ ከኀብረቱ የምስረታ በዓል ባለፈ የቡድኑን አቋም ለመፈተሽና ተጫዋቾች የኢንተርናሽናል ጨዋታ ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዋሊያዎቹ ከግብጽ ጋር በሚያደርጉት የወዳጅነት ጨዋታ የካፍ አመራር አባላት ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ፤ ጨዋታው የአገሪቱን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ከመርዳቱም በላይ በእግር ኳሱ ያለውን መነቃቃት ይበልጥ ለማበረታታት እንደሚረዳም አብራርተዋል፡፡

ብራዚል ለምታዘጋጀው እ..2014 የዓለም ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ ማጣሪያውን በማድረግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደቡብ አፍሪካ፣ ቦስትዋናና መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ በሚገኙበት ምድብ ሦስት መደልደሉ ይታወሳል።ቡድኑ እስካሁን ባደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በአንዱ አቻ ተለያይቶ በሰበሰበው ሰባት ነጥብ ምድቡን በመምራት ላይ ይገኛል።

ዋሊያዎቹ በሜዳቸው ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክና ከቦትስዋና ጋር ያደረጉትን ጨዋታዎች ሁለት ለዜሮና አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ፤ ከሜዳቸው ውጪ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ያደረጉትን ብቸኛ ጨዋታ አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

የግብጽ ብሔራዊ ቡድን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አቋሙ እየቀነሰ ቢመጣም በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ደረጃ ከፍተኛ ነው። ስለሆነም በሁለቱ ሀገራት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ጨዋታው ዋሊያዎቹ ወቅታዊ አቋማቸውን ለመፈተሽ እንደሚያስችላቸው አያጠያይቅም። 
አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment