Saturday, January 12, 2013

በግብረሰዶም ጥቃት የተጠናቀቀው የድህነት ማሸነፊያ አማራጭ

(Jan 12,  2013, Reporter)--የ25 ዓመቱ ወጣት በፍርሃት ተሸብቦ ቢሯችን ድረስ ሊያነጋግረን የመጣው በሱ የደረሰው በደል በሌሎች ላይ እንዳይደርስና በሱ ታሪክ ሌሎች እንዲማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገው ወጣት ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት የወደቀበት እናቱን በሞት ካጣ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ ነበር፡፡

ጡረተኛ አባቱን ማገዝ ታናናሾቹን ማስተማርና መንከባከብ፣ በየወሩ 500 ብር የቤት ኪራይ መክፈል የሱ ኃላፊነት ነው፡፡ በመላላክ፣ በመደለል፣ የዕለት ተዕለት ሥራዎችን በመሥራት የወደቀበትን ኃላፊነት ከመወጣት ባለፈም በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ በግል ኮሌጅ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍ 2ኛ ዓመት ደርሷል፡፡

ቀለብ ለመቻል፣ የትምህርት ቤት ወጪን ለመክፈልና የቤት ኪራይና ፍላጎቱን ለማሟላት ኑሮ ሸክም የሆነበት ወጣት ከውጭ ለሚመጡ ሰዎች ቢላላክ፣ ጉዳይ ቢያስፈፅምና ቢያግዝ ደህና ገንዘብ ሊያገኝ እንደሚችል የነገረችው በወሎ ሰፈር አካባቢ ያገኛት ወጣት ነበረች፡፡ ከወጣቷ የተነገረው ከውጭ ለሚመጡ ሰዎች ቢላላክና ሥራ ቢያግዝ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚያስገኝ ነበር፡፡ ከውጭ ከመጡ ሰዎች ጋር መሥራቱና ጠቀም ያለ ገንዘብ ማግኘቱ ያጓጓው ወጣት በወጣቷ አማካይነት ሥራውን ጀመረ፡፡

“ከስዊድን የመጣ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ያገናኘችኝ ወጣት፣ ሌሎች ሴቶችና ከስዊድን መጣ የተባልኩት ኢትዮጵያዊ አብረው ነው የሚኖሩት፡፡ አብረው ያሉት ሴቶች ቤተሰቦቹ እንደሆኑ ያገናኘችኝ ወጣት ነግራኛለች፡፡ እኔም ለኢትዮጵያዊው መላላክ ጀመርኩ፡፡”

ወጣቱ ከስዊድን ለመጣው አሠሪው ሱፐር ማርኬት ይላካል፤ በሄደበት አብሮ ይሄዳል፡፡ በመጀመሪያዎቹ የሥራዎቹ ቀናት ላገለገለበትም 600 ዶላር ተቀብሏል፡፡

ገንዘቡን እንደተቀበለም ለቤት ኪራይ የአምስት ወር ቅድሚያ መክፈሉን፤ ቀሪውን ገንዘብ ማስቀመጡን ይናገራል፡፡ ለ15 ቀናት ያህል በሥራ ካገዘው በኋላ ግን ወጣቱ ያልጠበቀው ሁኔታ ገጠመው፡፡ “አሠሪዬን ያገኘሁት በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ለ15 ቀናት ያህል ካገለገልኩ በኋላ አንድ ቀን ዕቃ እንግዛ ብሎኝ ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ ሄደናል፡፡ እኔ ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት አካባቢ ሆኜ እንድጠብቀው ነግሮኝ ዕቃ ገዝቶ መጣ፡፡ ወደ ቤትም ሄድን፡፡ ማታ ወደ ቤቴ ልሄድ ስል የሚያጨሰው ነገር እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ እኔም ጭሱ በአፍንጫዬ ሲገባ በግንባሬ አድርጎ ወደማጅራቴ እስኪሄድ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ የሆነውን አላስታውስም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ለሦስት ተከታታይ ቀናት ገጥመውኛል፡፡”

ወጣቱ እንደነገረን ግብረሰዶም እንደተፈፀመበት ያወቀው ዘግይቶ ነው፡፡ “መጸዳጃ ቤት ስገባ መቀመጫዬ አካባቢ ያመኝ ነበር፡፡ ምን ሆኜ ነው እያልኩ ከራሴ ጋር እመክራለሁ እንጂ ለሰው አላወራሁም፡፡ ግብረሰዶም ተፈፅሞብኝ ይሆናል ብዬም አልጠረጠርኩም፡፡”

ሕመሙ የበዛበት ወጣት ከራሱ ቤተሰብ ጋር ወደሚኖርበት ቤት አቅንቶ ዕረፍት ቢያደርግም የሚሰማው ሕመም አላስቀምጥ አለው፡፡ “መፀዳጃ ቤት ስቀመጥ ደም የቀላቀለ ቆሻሻ ይወጣኝ ጀመር፡፡ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ግብረሰዶም እንደተፈፀመብኝ የገባኝ የወጣውን ቆሻሻ ሳይ ነበር፡፡” ወደ ሕክምና ለመሄድ ሞራሉ ያልነበረው ወጣት ያቀናው አሠሪው የተከራየበት ቤት ነበር፡፡ ሆኖም ተከራዩ ወደ ስዊድን ተመልሷል ተባለ፡፡ ያገናኘችው ሴትም ሆነች ቤተሰቦች የተባሉት በስፍራው አልነበሩም፡፡ ያገናኘችውን ሴት ስልክ በተደጋጋሚ ቢሞክርም ስልኩ አገልግሎት የማይሰጥ መሆኑን ተረዳ፡፡  “ክስ ለመመሥረት አስቤ ነበር፡፡ ያም ሆኖም ማንንም ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ተሳጨሁ፡፡ ድህነትን ለማሸነፍ ብዬ ሕይወቴን አበላሸሁ፡፡”

ወጣቱ እንዳለን 2005 ዓ.ም. ከገባ ጀምሮ ሪፖርተር ጋዜጣ ቢሮ እስከመጣበት ያለፈው ሁለት ሳምንት ድረስ ከቤቱ አልወጣም፡፡ አልጋው ላይ ተኝቶ የሚያስበው ራሱን ስለማጥፋት ነበር፡፡ ሆኖም አባቱንና ታናሾቹን ጥሎ ሞተ ማለት እነሱን በቁም መግደል ስለሆነበት በኃላፊነትና ራስን በማጥፋት፤ የግብረሰዶም ሰለባ በመሆንና በእምነቱ መካከል ባሉ የሐሳብ ፍጭቶች ውስጥ በመዋዠቅ ሦስት ወራት ያህል አጥፍቷል፡፡ ትምህርቱንም አቋርጧል፡፡ ሥራ መሥራትም አቁሟል፡፡

አባቱም ሆነ ታናናሾቹ የባሕሪውን መቀየር ቢገነዘቡም ከቤት አለመውጣቱ ቢያስጨንቃቸውም ምን ሆነህ ነው? ብለው ቢጠይቁትም ዝምታን መምረጡን ይናገራል፡፡ እሱ ቤት በመዋሉም የሱ ተከታይ ከትምህርት ቤት መልስ እንጨት ቤት ለመሥራት ተገዷል፡፡ ገሚሱ ኃላፊነትም ወደታናሹ ተላልፏል፡፡

ከቤት ወጥቶ ትምህርቱን መቀጠል ወይም ሥራ መሥራት ያልፈለገበትን ምክንያት በተመለከተ “መንገደኛው ሁሉ የሚያየው እኔን ነው፡፡ መንገድ ላይ መሄድ አልቻልኩም” በማለት ሕዝብ ሁሉ በራሱ የሚያውቅ የሚመስልበትን ሥጋት ገልጿል፡፡

ሪፖርተር በመጣበት ጊዜ ራስን ማጥፋት መፍትሔ ወይም አማራጭ አለመሆኑን የተገነዘበው ወጣት የምክር አገልግሎት የሚያገኝበት ሁኔታ ተመቻችቶለታል፡፡ 
Source: Reporter

Related topics:
የግብረሰዶም ነገር
የግብረሰዶማውያኑ ስብሰባ የፈጠረው ትኩሳት
ግብረሰዶማዊነትን ለማውገዝ የተጠራው የሃይማኖት ...
ኢትዮጵያ ግብረሰዶምንና አራማጆቹ ምዕራባዊያንን አወገዘች
Ethiopia to be represented at Mr Gay World ...
Ethiopia gay meet creates buzz on Facebook

No comments:

Post a Comment