Friday, September 16, 2011

ቀነኒሳ በብራስልስ የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ10ሺህ ሜትር ሩጫ አሸነፈ

(መስከረም 6 ቀን 2004 (አዲስ አበባ, ኢዜአ)--አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ትናንት በቤልጂዬም ዋና ከተማ ብራስልስ በተጠናቀቀው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 10ሺህ ሜትር ሩጫ አሸነፈ።

ኢማነ መርጊያ ለሁለተኛ ዓመት በአምስት ሺህ ሜትር የዳይመንድ ሊግ ውድድር የዓመቱ ምርጥ ተሸላሚ ሆኗል።

ኢዜአ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ እንዳስታወቀው ለሁለት ዓመታት ያህል በሕመም ምክንያት ከውድድር ርቆ የቆየው ቀነኒሳ 26 ደቂቃ 43ነጥብ 16 ሰከንድ ርቀቱን በመግባት አሸንፏል።

ቀነኒሳ የገባበት ሰዓት በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመት በእንግሊዛዊው መሐመድ ፋራህ ከተመዘገበው የሦስት ነጥብ 41 ሰከንድ ብልጫ አለው።

ታዋቂው አትሌት በንጉሥ ባዩዲዩን ስታዲዬም የታደመውን 40ሺህ ታዳሚዎች ባስደመመ መልኩ ኬንያዊ ሉካስ ሮታችን የመጨረሻውን ዙር ትቶት በመሮጥ በቀዳሚነት ውድድሩን አጠናቋል።

ቀነኒሳ በኮሪያዋ ዴጉ ከተማ በየተካሄደውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሕመም ምክንያት ውድድሩን አቋርጦ ወደ አገሩ መመለሱን ኢዜአ አስታውሷል።

በተመሳሳይ ሁኔታ ሁለተኛ ዓመቱን ትናንት ባጠናቀቀው የዳይመንድ ሊግ ውድድር አትሌት ኢማነ መርጋ በአምስት ሺህ ሜትር ሩጫ ምርጥ አትሌት ሆኖ ለመሸለም በቅቷል።

ኢማነ የተሸለመው በሊጉ በተደረጉት ውድድሮች ባጠራቀመው 15ነጥብ በማግኘት በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት በውድድሩ ከተሳተፉ ምርጥ አትሌቶች አንዱ በመሆኑ ነው።

ኢማነ ባለፈውና በያዝነው የአውሮፓውያን ዓመታት በተደረጉት የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ካሸነፉ አራት ወንድ አትሌቶች ውስጥ መግባቱንም የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር መረጃን ዋቢ አድርጎ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት   


No comments:

Post a Comment