Saturday, April 23, 2011

ሕዝበ ክርስቲያኑ ትንሳኤን በዓል ሲያከብር መልካም ስራን ለሰው ልጆች ሁሉ በመስራት ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

(አዲስ አበባ, ሚያዝያ 15 ቀን 2003, አዲስ አበባ, ENA) - ሕዝበ ክርስቲያኑ የትንሳኤን በዓል ሲያከብር ፍፁም ክብርና የዘላለም ህይወት የሚያስገኘውን መልካም ስራ ለወገኖቹና ለሰው ልጆች ሁሉ በመስራት ሊሆን እንደሚገባ ብፁወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አስታወቁ።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የ2003 የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት ቃለ ቡራኬ ምዕመናን በዓሉን ሲያከብሩ ረዳት የሌላቸውን አቅመ ደካሞችና ችግረኞች፣ አረጋውያንን፣ የሚበላና የሚቀመስ ላጡ ህሙማን፣ አሳዳጊ ያጡ ሕጻናትንና የኤድስ ሕሙማንን መርዳትና ማፅናናት አለባቸው፡፡

በተጨማሪም ህዝበ ክርስቲያኑ ሌት ተቀን ሰርቶ አገሩን፣ ወገኑንና ራሱን ማበልፀግ በእግዚአብሄር ዘንድ የተወደደ መሆኑን ሁላችንም መረዳት ይኖርብናል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የተያያዘችውን መልካም ሥራ መነሳሳትና የልማት መስፋፋት ትንሳኤ በሁሉም አቅጣጫ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የእግዚአብሄር ፍላጎት መሆኑን ህዝቡ ሊገነዘበው እንደሚገባ ገልፀዋል።

የትንኤ በዓል ምስጢር በትክክል ተረድተናል ማለት የሚቻለው ያሳለፍናቸውን የድህነት፣ የድንቁርና የስንፍና ዘመናትን በልማትና በስራ ለመለወጥ ከልብ በመነሳት እንደሆነ አቡነ ጳውሎስ ተናግረዋል።

ትንሳኤ ማለት በነፍስም በስጋም መታደስ ማለት ነውና በመንፈስም፣ በሥራም ፣ በሃይማኖትም በርትተን እየሠራን በልማት ጎዳና የአገራችንን እድገት ዕውን ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠርን እኛ የእግዚአብሄርን አሠራር በመከተል ዓለማችንን ውብና ማራኪና ለሰው ልጅም ምቹ መኖሪያ ትሆን ዘንድ እንድናበጃት እግዚአብሄር አዞናል ብለዋል።

በተለይ በዓለም ላይ የሚታይ የተመሰቃቀለ የሰው ልጆች አኗኗር ከፈጠሩ ምክንያቶች አንዱ ለሰላምና ለሥራ ትኩረት ያለመስጠት ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል።

ሰላም ለራስ ደህንነት፣ ለአገር ዕድገትና ልማት አስፈላጊ በመሆኑ ሁሉም ኅብረተሰብ እርቅና ሰላምን መፈለግና መከተል እንደሚጠበቅበትም አቡነ ጳውሎስ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም በዓሉ የተባረከና የተቀደሰ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የስምምነት ያድርግልን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁ አቡነ ብርሃነየሱስ በበኩላቸው እንደገለጹት በፋሲካ በአል ብዙ የሚደሰቱ እንዳሉ ሁሉ ብዙዎች በችግር እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል።

በተለይ የታመሙትን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናትን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችንና አቅመ ደካሞች ስላሉ ሁላችንም በተቻለ መጠን በክርስቲያናዊ መንፈስ ልንረዳቸውና በዓሉን በጋራ ልናከብር ይገባል ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ መንግስት ሥራ ለሌላቸው ወገኖች ትኩረት ሰጥቶ በተለያዩ የሙያ መስኮች በማሰልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ የያዘው ዕቅድ የሁሉንም ህብረተሰብ የስራ መነሳሰት ከመፍጠሩም በላይ የሥራ ባህል እንዲለመድ ያደረገ መሆኑን አቡነ ብርሃነየሱስ ተናግረዋል።

በአገራችን እየተተገበረ ያለው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የእግዚአብሄር እርዳታ ተጨምሮበት ውጤታማ እንዲሆን እንፀልያለን ብለዋል።

በመጨረሻም በአባይ ወንዝ ላይ ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሁላችንም ተሳትፎ ተገንብቶ የህብረትና የአንድነት ቅርስ እንዲሆን እንመኛለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዋቅስዩም ኢዶሳ በበኩላቸው በዓሉን ክርስቶስ ራሱን ለእኛ ሰጥቶ እንዳደነን ሁሉ እኛም ለወገኖቻችን ያለንን በማካፈል በዓሉን ማክበር ይጠበቅብናል ።

መልካም ስራን የሚሰሩ የትንሳኤ መጀመሪያ የሆነውን ክርስቶስን መስለው መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ ብለዋል።

በፋሲካ በአል በችግርና በህመም፣ በስቃይና በጎዳና የሚኖሩ እንዲሁም በኤች አይ ቪ ህመም ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ህፃናት ብሎም ሰብሳቢና ጧሪ አረጋውያንና አረጋውያት ስላሉ ሁላችንም በተቻለ መጠን በክርስቲያናዊ መንፈስ ልንረዳቸውና በዓሉ በጋራ ልናከብር ይገባል ብለዋል።
Source: Ethiopian News Agency

Epiphany celebrated colorfully 

No comments:

Post a Comment