• ከዳያስፖራው ጋር ሰፋፊ ውይይቶችን ለማካሄድ ተዘጋጅቷል
በውድነህ ዘነበ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን (ዳያስፖራ) ወጥ በሆነ መንገድ ማስተናገድ ያስችላል ያለውን አዲስ ፖሊሲ አረቀቀ፡፡ ሚኒስቴሩ ከዚህ ረቂቅ በተጨማሪ አገሪቱ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በምትመራበት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ በሚቀጥለው ሳምንት ጥር 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየት አቅዷል፡፡በውድነህ ዘነበ
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳዮች ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ መብራት በየነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚኒስቴሩ ለበዓል ወደ አዲስ አበባ ከመጡ 500 ከሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመመካከር ቀን መቁረጡን ገልጸዋል፡፡
ውይይቱ ትኩረት የሚያደርገው ዳያስፖራውን በሚመለከት በተረቀቀው ፖሊሲና በአምስት ዓመት ዕቅዱ ዙሪያ መሆኑን፣ በእነዚህ አጀንዳዎች ላይ ዳያስፖራው ሚናውን እንዲገነዘብና ተጨማሪ አስተያየቶቹን እንዲሰጥ ለማድረግ መሆኑን ወይዘሮ መብራት አስረድተዋል፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸው ውስጥ ኢንቨስት ቢያደርጉ የሚያገኙዋቸው የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በተለያዩ አዋጆች ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ ይሁንና ዳያስፖራው በአገሪቱ ልማት ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ሊያሳድር የሚችለው መልካም ተፅዕኖ ተለይቶ እንዲታወቅ ለማድረግና ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሚያገኛቸው ማበረታቻዎችና ጥቅማ ጥቅሞች ዙሪያ ወጥ የሆነ ፖሊሲ ማስቀመጥ ያስፈልጋል በሚል፣ ሚኒስቴሩ ጥናት ሲያካሂድ መቆየቱን አክለው ገልጸዋል፡፡
የሌሎች አገሮች ልምድ ተካቶበት ተዘጋጀ የተባለው ረቂቅ ፖሊሲ ለመጀመሪያ ጊዜ በሸራተን አዲስ ሆቴል ውይይት እንዲካሄድበት መዘጋጀቱንና ስብሰባውንም የሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ረቂቅ ፖሊሲ በተጨማሪም ከዚህ ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ በሚደረገው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለውይይት ይቀርባል፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ ግዙፉን የአምስት ዓመታት ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስፈልገውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለማግኘት ትኩረት ከተደረገባቸው ምንጮች መካከል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይጠቀሳሉ፡፡
መንግሥት ከእነዚህ ኢትዮጵያውያን ለልማት የሚውል ጠቀም ያለ ገንዘብ ለማግኘት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ሽያጩን ከመጀመሩ በፊት የልማቱን ጥልቀትና ስፋት ማሳወቅ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ስብሰባው እንደተዘጋጀ ታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በሁለቱ አጀንዳዎች ዙሪያ ከዲያስፖራው ጋር የሚያካሂደው ውይይት በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ እንደማይቀርና በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከወራት በኋላ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ሰፋፊ ውይይቶችን ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑም እየተነገረ ነው፡፡
ይህንን ውይይት ለመምራት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴርና የብሔራዊ ባንክ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ተቋማትን የሚመሩ ባለሥልጣናት ቅድሚያውን እንደሚይዙም ታውቋል፡፡
የመሠረተ ልማት ተቋማት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሮች ከሦስት ሳምንት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ በየመሥሪያ ቤቶቻቸው አማካኝነት የተሠሩ ሥራዎችንና ሊሠሩ የታቀዱ ሥራዎችን አጠናቅሮ የያዘ ሰነድ በ10,000 ኮፒ እንዲያዘጋጁ መታዘዛቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡