Sunday, August 11, 2019

ማፈርስ በራሳችን ነው!

(Aug 11, (ሪፖርተር))--የኢትዮጵያ ስታዲየሞች በሙሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንን (ካፍ) ዝቅተኛውን መሥፈርት ስለማያሟሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑ ዓለም አቀፍ ግጥሚያዎች ወደ ጎረቤት አገር እንደሚሄዱ ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡

ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት የካፍ መሥራች አባል የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ዝቅተኛውን መሥፈርት ማሟላት ባለመቻሏ ስታዲየሞቿ ከዓለም አቀፍ ውድድር ሲታገዱ መስማት ትልቅ ኃፍረት ነው፡፡ ይህ አንገት የሚያስደፋ ኃፍረት ብዙዎችን የሚያሳዝንና የሚያበሳጭ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ቆም ብሎ ዙሪያ ገባውን በማየት ዘርፈ ብዙ አገራዊ ጉዳዮችን መመርመር ያስፈልጋል፡፡

ምክንያቱም በጣም የተበላሹ ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ካፍ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ዝቅተኛውን መሥፈርት አታሟሉም ካለን፣ በተለያዩ ዘርፎችም ከመሥፈርት በታች እንደምንገኝ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ ስታዲየሞች እየገነባን ነን ብለን ስንኮፈስ፣ ከመፀዳጃ ቤት ጀምሮ አስፈላጊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ደረጃቸውን መጠበቅ ካቃተን፣ በብዙ ዘርፎች መሠረታዊ የሆኑ ችግሮች አሉብን ማለት ነው፡፡ ከመኮፈስ ወጥተን በራሳችን እያፈርን ራሳችንን እንመርምር፡፡

በርካታ መንግሥታዊ ተቋማት ለዓመታት ከሚተቹባቸው ጉዳዮች መካከል ዕቅድና አፈጻጸም ይጠቀሳሉ፡፡ ዕቅዶች ሲወጡ የሚፈለገውን ውጤት ለማስገኘት የሚረዱ ክንውኖች በቅደም ተከተል ካለመለየታቸውም በላይ፣ የቁጥጥርና የግምገማ ሥልቶቹ እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ የሚሰማራው የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የማቴሪያል አቅርቦትና አጠቃቀም ከደረጃ በታች ነው፡፡ ለሚያጋጥሙ ችግሮች ምን ዓይነት መፍትሔዎችን ለመጠቀም እንደሚቻል ዝግጅት አይደረግም፡፡

የሌሎች ግብዓቶች አስፈላጊነት ይዘነጋል፡፡ በእነዚህና በመሰል ምክንያቶች አፈጻጸም ከሚፈለገው በታች ወርዶ እንዘጭ ይላል፡፡ በዚህ ዘመን ‹የተለጠጠ ዕቅድ› የሚባል አስገራሚ ነገር መስማት አዲስ አይደለም፡፡ ውጤቱ ግን ‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ› ነው፡፡ በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በተለያዩ አገልግሎቶች አሰጣጥና በመሳሰሉት የሚታየው አስተቃቀድና አፈጻጸም ምን ያህል ሥር የሰደደ ችግር እንዳለ ማሳያ ነው፡፡ የሚፈለገውን የሰው ኃይልና ሀብት ይዞ የበለጠ ማግኘት እየተቻለ፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት መሰቃየት አይኖርም ነበር፡፡ መሥራት እየተቻለ ችግር አይወራም ነበር፡፡ መሥራት የሚችል እጅ ለልመና አይዘረጋም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የ110 ሚሊዮን ሕዝብ መኖርያ አገር እንደሆነች ተደጋግሞ ይነገራል፡፡ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ለአገር ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ በዚህ ላይ እጅግ ለም የሆነ ሰፊ መሬት፣ ከፍተኛ የሆነ የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውኃ ሀብት፣ ለግብርና ተስማሚ የሆኑ የተለያዩ የአየር ፀባዮች፣ ዓይነተ ብዙ ማዕድናት፣ በአፍሪካ ቁጥር አንድ ለመባል የሚችሉ የቱሪዝም መስህቦች፣ ወዘተ ባለቤት የሆነች አገር በዓመት በአማካይ ከስምንት ሚሊዮን የማያንሱ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ይለመንላቸዋል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ በብሔር ግጭት ሳቢያ ሚሊዮኖች ተፈናቅለው የዕርዳታ ጥገኛ ይደረጋሉ፡፡ ሥራ አጥነት፣ ከድህነት ወለል በታች መኖር፣ በመኖሪያ ቤት ዕጦት መሰቃየት፣ በተመጣጠነ ምግብ ዕጦት መቀንጨርና ጎስቋላ የሆነ ሕይወት መግፋት፣ ወዘተ የሚሊዮኖች ዕጣ ፈንታ ናቸው፡፡

ስንዴ፣ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉት እዚህ በስፋት መመረት ሲኖርባቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣባቸው ናቸው፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አንገት ከሚያስደፋ ማጥ ውስጥ በፍጥነት ወጥቶ ተባብሮ መሥራት ሲቻል፣ ድህነት አሁንም የማይበገር የመከራ ቋጥኝ ሆኗል፡፡ በቁጭት በመነሳሳት ከዚህ አሳፋሪ አኗኗር ለመውጣት የሚደረገው ጥረት ደግሞ አስተዛዛቢ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ኃፍረቱ አንገት ያስደፋል፡፡

በሌላ በኩል ከዓመት ዓመት የቁልቁለት ጉዞውን የተያያዘው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር፣ አሁንም ተስፋ ያስቆርጣል እንጂ አበረታች ነገር አይታይበትም፡፡ ፖለቲከኞች ከሚባሉት አብዛኞቹ ለመነጋገር የሚያስችላቸውን መቀራረብ ይፈሩታል፡፡ በግድ የሚያገናኛቸው መድረክ ሲኖርም በግልጽ አይነጋገሩም፡፡ ከሐሜትና ከአሉባልታ የዘለለ የሥልጣኔ ፖለቲካ ውስጣቸው ሊሰርፅ አልቻለም፡፡ ጥንካሬ፣ ትዕግሥትና ፈቃደኝነት ስለሚጎድላቸው በግልጽ ለመነጋገር ወኔው የላቸውም፡፡

ለግማሽ ክፍለ ዘመን በውስጣቸው ያጨቁትን ቂምና ቁርሾ ለማወራረድ እንጂ፣ ከዓመታት ስህተት ተምረው ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዳ ጠጠር ለማቀበል ዝግጁ አይደሉም፡፡ መነጋገርና መደራደር የብልህ ፖለቲከኞች ባህሪ መሆኑን ከመረዳት ይልቅ፣ ተጠላልፈው ለመውደቅ ግን ማንም አይቀድማቸውም፡፡ ሰጥቶ መቀበል በሚባለው መርህ መሠረት የጋራ የሆነ አማካይ ለመፈለግ ሳይሆን፣ አንዱ ሌላውን እንዴት ማጥፋት እንዳለበት ሲያደቡ ካሰቡበት ሳይደርሱ መንገድ ላይ ይቀራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ሰላም እየነሱ ንፁኃንን መከራ ያሳያሉ፡፡ ከመሥፈርት በታች ያላችሁ ፖለቲከኞች ለአገር ጠንቅ ሆናችሁ በኃፍረት አንገታችንን አታስደፉን መባል አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ  የቁልቁለት ጉዞው ይቀጥላል፡፡ ኃፍረቱም እንዲሁ፡፡

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ ይህች ታላቅና ታሪካዊት አገር ግን በዚህ ዘመን በርካታ ችግሮች አሉባት፡፡ አንገቷን ቀና አድርጋ በኩራት መራመድ ያለባት አገር በድህነትና በዴሞክራሲ ዕጦት የምትሰቃየው አንሶ፣ በሁለት እግሯ ቆማ ያቋቋመችው ካፍ ከመሥፈርት በታች ነሽ ሲላት የዘመኑ ትውልድ ካላፈረ ማን ይፈር? ለበርካታ አገሮች በሰላም አስከባሪነት ታላቅ ተጋድሎ ያደረገች ኢትዮጵያ፣ በገዛ ልጆቿ ጥፋት ሰላሟ ደፍርሶ ያለመረጋጋት ምሳሌ ስትሆን ማፈር ያለበት ማን ነው? ለበርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣት የአንበሳውን ድርሻ የተጫወተች አገር፣ በዚህ ዘመን በጠባብ ብሔርተኞች ምክንያት ህልውናዋ አጠያያቂ ሲሆን ማን ይፈር?

በበርካታ ጉዳዮቻችን አገራችንን ለኃፍረት እየዳረግን መቀጠል ይሻለናል? ወይስ ከጥፋታችን ተምረን አገራችንን በአንድነት ማሳደግ? እርስ በርስ በማይረቡ ጉዳዮች እየተናጀስን መበላላት? ወይስ እንደ ሠለጠነ ሰው እየተነጋገርን መተማመን መፍጠር? በዚህ አያያዛችን ከቀጠልን ውርደቱ የበለጠ እንደሚጨምር መጠራጠር አይገባም፡፡ ጣት በመቀሳሰር ጥፋትን ሌላ ላይ ማላከክ ሳይሆን፣ የደረሰብን ኃፍረት የጋራ ጥፋታችን ውጤት መሆኑን በመተማመን ከገባንበት አዘቅት ውስጥ መውጣት ይበጃል፡፡ ማፈር ካለብን በራሳችን እንጂ በሌላ ማላከክ አያዋጣም!
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment