Sunday, August 11, 2019

ፖለቲከኞች ከመጠማመድ ወደ መደማመጥ ተሸጋገሩ!

(Aug 11, (ሪፖርተር))--ከ40 ዓመታት በፊት ኢሕአፓና መኢሶን በመስመር ልዩነት ምክንያት ደም አፋሳሽ ጠላትነት ውስጥ ሲገቡ፣ የቃላት አጠቃቀማቸው ጭምር አንዱን ከሌላው መለያ እንደነበር ብዙ ተብሎበታል፡፡ እነዚህ የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም ይከተሉ የነበሩ ድርጅቶች ንፋስ ሊያስገባ በማይችል ልዩነት ጠላትነት ከመፍጠራቸውም በላይ፣ ለአንድ ትውልድ ጦስ የሆነ መከራ እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል፡፡

አንዱ ከደርግ ጋር በነበረው ከመጠን ያለፈ ወዳጅነት፣ ሌላው ደግሞ በፈጠረው ከመጠን ያለፈ ጠላትነት ሳቢያ በቀይና በነጭ ሽብሮች አገሪቱ ማቅ መልበሷ አይዘነጋም፡፡ የዚህ ሁሉ ጥፋት ዋነኛ ምክንያት ልዩነትን አጥብቦ ለመነጋገር ፈቃደኝነት በመጥፋቱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ፈቃደኝነት ካለ በሁሉም ነገሮች ላይ ለመነጋገር የማያዳግት ሆኖ ሳለ፣ በግለሰቦች ፀብ ወይም ትዕቢት ምክንያት ያ ሁሉ ኪሳራ ደረሰ፡፡ የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች በመምከናቸው የታሰበው ሁሉ ሳይሳካ እንዳይሆኑ ሆኖ ቀረ፡፡ አንድ ትውልድ ለሞት፣ ለእስር፣ ለሥቃይና ለስደት ተዳረገ፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግም ከዚያ ስህተት መማር ባለመቻሉ የደረሱት ሰቆቃዎች ይታወቃሉ፡፡ አሁንም ከዚያ መሰሉ አሳዛኝ ክስተት ለመማር ፈቃደኛነቱ አይታይም፡፡

ከ100 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳሉ በሚነገርበት በዚህ ጊዜ ለሕዝብ የሚቀርቡ አማራጭ ሐሳቦችን ከመስማት ይልቅ፣ በረባ ባልረባው መካሰስና መወቃቀስ የተለመደ ሆኗል፡፡ በዓላማ የሚመሳሰሉት እየተዋሀዱ ጠንክረው ለመውጣት ሳይሆን፣ መደራጀት መብት ነው በሚል ሰበብ ቁጥር ማብዛት ላይ የሚያተኩሩ ይልቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንዴት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትሸጋገር ከማለት ይልቅ፣ ጭራሽ ወደኋላ የሚጎትታትን አጀንዳ ማራገብ ተለምዷል፡፡

የምርጫ ሕጉ ተሻሽሎ ለውይይት ሲቀርብ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ያለበት አገር ውስጥ፣ ለምን አሥር ሺሕ መሥራች አባላት አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት እንጠየቃለን የሚል ክርክር ይሰማል፡፡ አንድ አገር አቀፍ ወይም ክልላዊ ፓርቲ መመሥረት የሚያስፈልገው እኮ፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ሥልጣን ለመያዝ ነው፡፡ የሥልጣኑ ምንጭ የሆነው ሕዝብ ድምፅ የሚገኘውም ተፎካካሪዎችን በሁሉም ዘርፎች በልጦ በመገኘት ነው፡፡ ካሁን ቀደም እንደነበረው የጠንካሮች አጃቢ መሆን በሕዝብ ዘንድ ሞገስ አያስገኝም፡፡ ፖለቲከኞችም መገንዘብ ያለባቸው ይህንኑ ነው፡፡ በቅጡ ተነጋግረው ጠንካራ ሆነው መውጣት የሚችሉት ጠንካራ፣ አሳታፊና ዘለቄታዊነት ያለው ሕግ ሲኖር ነው፡፡

የአገሪቱ ኋላቀር የፖለቲካ ምኅዳር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት አጀንዳ ባላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገጽታው መለወጥ አለበት፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲለወጥ ደግሞ፣ የጨዋታው ሕግ በአግባቡ ሥራ ላይ ሊውል ይገባል፡፡ የጨዋታው ሕግ ምን ይላል? ልዩነትን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት መላበስ፣ ልዩነት አብሮ ለመሥራት አያመችም ከሚል ቅዠት ውስጥ መውጣት፣ ያልተገደበ የሕዝብ ውይይትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር ማድረግ፣ ዝምታን አስፍኖ አሉባልታንና ሹክሹክታን የሚያባዛ የተወጠረ አየርን ማስተንፈስ፣ ዴሞክራሲያዊነት ማለት በመብቶችና በልዩነቶች ውስጥ አብሮ ለመኖር መቻል ማለት መሆኑን፣ ይኼንንም መሠረት ለማስያዝ በመረባረብ ችግሮች ወይም አለመግባባቶች ሲከሰቱ፣ በሰላማዊ መንገድ መፍታትና ውጤቱንም መቀበል የጨዋታው ሕግ አካል ናቸው፡፡

ጥያቄዎች ወይም ልዩነቶች የአመፅ መንገድ ውስጥ ሳይገቡ የሚስተናገዱበት፣ ጥፋቶች ወይም ሕገወጥነቶች የትግል ወይም የመብት ሽፋን ሳያገኙ የሚጋለጡበት፣ በዚህ ወይም በዚያ ፓርቲ መስመር በትክክል የመመራት ጉዳይ፣ የዚህ ወይም ያዚያን ወገን አቋም የማክበር፣ ከሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ በሰላማዊ ክርክር የመርታትና ሰፊ ተቀባይነት የማግኘት፣ ይኼንንም በሕዝብ ወይም በወኪሎች ነፃ ድምፅ ማረጋገጥ የጨዋታው ሕግ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ በጨዋታው ሕግ ማፈር አይቻልም፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሚሳተፉ ኃይሎች የብዙዎች ችግር የጨዋታውን ሕግ አለማወቅ ወይም ሆን ብሎ ማበላሸት ነው፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት በፊት የሥልጣን ጉጉት ስለሚቀድም፣ በሥልጡን መንገድ ለመጓዝ ብዙዎች ይቸግራቸዋል፡፡ አባላትንና ደጋፊዎችን ንቃተ ህሊናቸውን አጎልብቶ የጠራ ዓላማ ከማስያዝ ይልቅ፣ ሰላማዊውን ድባብ በማደፍረስ ሁከትና ግጭት መቀስቀስ ይቀላቸዋል፡፡ ፖለቲከኞች ይህ አልበቃ ብሏቸው በራሳቸው ድክመት ምክንያት በመብት ተሟጋችነት ስም የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶች ተቀጽላ ሆነዋል፡፡ ጉልበታቸውን በተለያዩ መንገዶች ለማሳያት ወደ ኋላ የማይሉት አክቲቪስቶች በሚቆፍሩላቸው ቦዮች የሚነጉዱ ፖለቲከኞች፣ ፓርቲዎቻቸውን መርህ አልባ እያደረጉ ነው፡፡

የፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ እንዲህ ዓይነቶቹ ሲበዙ እንኳንስ በሰከነ መንገድ ለመነጋገር ቀርቶ፣ የቃላት ጦርነቱ ወደ ጠመንጃ ላለመቀየሩ ማስተማመኛ የለም፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ እፍርታሞች ሲበዙበት ደግሞ እንኳንስ ለመነጋገር በዓይን ለመተያየት ይቸግራል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ሲደረስ ደግሞ እንደ እነ ኢሕአፓና መኢሶን ዓይነቱ ጠላትነት አይቀሬ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ይህ ዓይነቱ አክሳሪ መንገድ በፍፁም አይገባውም፡፡ ሕዝብ እየጠየቀ ያለው የፖለቲካ ልዩነቶችና አለመግባባቶች፣ ንትርኮች፣ ቅያሜዎችና ኩርፊያዎች፣ ለዘመናት ያስቸገሩ ቂምና ጥላቻዎች ወደ ግጭት የሚሄዱበት ዕድል እንዲወገድ ነው፡፡ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና መሰባሰብ እየሰፉ እንዲሄዱ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ውክልና የላቸውም፡፡ የሕዝብ ውክልና የሚገኘው ከድምፅ ሳጥን ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ድምፅ ለማግኘት ደግሞ የጨዋታ ሕጉን በአግባቡ መጫወት የግድ ይሆናል፡፡

ከሕገወጥነት በመራቅ ለሕግ የበላይነት መገዛት፣ የጉልበቱን መንገድ በመተው በውይይት ማመን፣ ከትርኪምርኪ ነገሮች ውስጥ በመውጣት የመራጩን ሕዝብ ልብ የሚያማልሉ አጀንዳዎች ማስተዋወቅ፣ የዴሞክራሲን መሠረታዊ ዓምዶች ማክበር፣ ለዘመኑ የሚመጥን ዕውቀትና ክህሎት መጨበጥ፣ አባላትንና ደጋፊዎችን በሥነ ምግባር ማስገዛት፣ ጥራት ያላቸው ሐሳቦች ማመንጨትና የመሳሰሉት የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ መለያ ሊሆኑ ይገባሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ አጓጉል ድርጊቶች እንኳን አደባባይ ሊያስወጡ ለህልውናም አይረቡም፡፡ ፖለቲከኞች ከመጠማመድ ወጥተው መደማመጥ ሲጀምሩ በዚህ ዓይነቱ የላቀ ደረጃ ላይ ለመገኘት አይቸግራቸውም!
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment