Saturday, February 24, 2018

የምናለማት እንጂ የምናጠፋት አገር ልትኖረን አይገባም

(Feb 23, (ኢትዮጵያ ))--የሃገራችንን የኋላ ጉዞ መለስ ብለን ስንቃኝ በርካታ የጦርነት ታሪኮችን እናገኛለን፡፡ አንዳቸውም የጦርነት ታሪኮች ግን በኢትዮጵያውያን ግፊት የተከሰቱ አልነበሩም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሃገሪቱን ለመበተን ከውስጥና ከውጭ የተነሱትን ኃይሎች ለመመከት የተደረጉ የትግል ውጤቶች ናቸው፡፡

ጀግኖች አባቶቻችንም በተለያዩ ወቅቶች የመጡብንን ወራሪ ኃይሎች በወኔና በቆራጥነት በመመከት ሰላሟ የተረጋገጠና በማንም የውጭ እጅ ያልወደቀች ነፃ ሃገር አውርሰውናል፡፡ ይህችን ነፃና ዳር ድንቧሯ የተከበረ አገር ለዛሬው ትውልድ ለማውረስም የህይወትና የአካል መስዋዕትነትን ከፍለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የውጭ ወራሪ ኃይል ስጋት አልተጋረጠብንም፡፡ በዚህ ዘመን ከፊታችን ተጋርጦ የሚገኘው እያደገ የመጣው የህዝብ ፍላጎት የፈጠራቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ የህዝብ ቅሬታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ጥያቄ በመፍታት ረገድም ነገ ሃገሪቷን የሚረከበው ወጣቱ ትውልድ የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ ይገባል፡፡ ሃገርን የመገንባትም ሆነ የማጥፋት አቅሙ ያለው በዋናነት ወጣቱ ትውልድ ላይ በመሆኑ ወጣቶች በሃገራችን እየተፈጠሩ ያሉ አለመረጋጋቶችን በሰከነና በሠለጠነ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው 71 ከመቶ የሚሆነው የሃገራችን ህዝብ ዕድሜው ከ30 ዓመት በታች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሃገሪቷን የወጣቶች አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይህ ኃይል ደግሞ ሃገርን ለመለወጥ የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለው መገንዘብ አያዳግትም፡፡

በሌላ በኩል ይህ ኃይል በሚፈለገው ልክ ለልማት ካልዋለና የጥፋት መንገድ የሚከተል ከሆነም የሚያስከትለው ጉዳት የዚያኑ ያክል ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም መንግሥት ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይ ወጣቱን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ልዩ ልዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ መተግበሩ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በ2009 በጀት ዓመት ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአስር ቢሊዮን ብር የተዘዋዋሪ ፈንድ በጀት መድቦ ወደ ሥራ መግባቱና በአንዳንድ ቦታዎችም ወጣቶች ተደራጅተው ወደ እንቅስቃሴ በመግባት ውጤታማ መሆናቸው የዚህ ሥራ ፍሬ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

ሆኖም በሁሉም የመንግሥት አስፈፃሚዎች ዘንድ አቅጣጫዎች በአግባቡ ባለመተግበራቸውና የወጣቱን ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ ባለመቻላቸው የቅሬታ ምንጭ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በአንዳንድ የሃገሪቷ አካባቢዎች የግጭት ምንጭ እስከመሆን ደርሰዋል፡፡

ያም ሆኖ ግን መንግሥት እነዚህ ችግሮች መኖራቸውን በማመን ለመፍታት ቁርጠኝቱን አሳይቷል፡፡ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም በቅርቡ ለ17 ቀናት ባካሄደው ጥልቅ ግምገማ በመንግሥትና መንግሥቱን በሚመራው ድርጅት ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን በመገምገም ችግሩን ለማረም እንደሚሠራ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንንም መሰረት በማድረግ ግምገማው እስከታችኛው የአስተዳደር እርከን እንዲወርድ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ እርምጃዎች መወሰድ ጀምረዋል፡፡

ያም ሆኖ ግን በሃገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ሊቆም አልቻለም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም ግጭቱ አላስፈላጊ መልክ በመያዝ የመንግሥትና የህዝብ ንብረትን የማውደም፣ እንዲሁም ዘርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች እየተከተለ መሆኑ ይታወቃል፡፡

መንግሥት ችግሮቹን ባመነበትና ለመፍታትም ጥረት በጀመረበት፤ ችግሩንም ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ትንሽ ጊዜ እንዲሰጠው በጠየቀበት በዚህ ወቅት ብጥብጥን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን መረዳት ይገባል፡፡

ዛሬ ላይ በአገራችን የሚከናወኑ አንዳንድ የልማት ሥራዎች ከተጀመሩበት ፍጥነት በላይ በእጥፍ ካልጨመሩና ፈጥነን ከድህነት ካልወጣን የልማት ጉዞው እንደሚደናቀፍ ይታመናል፡፡ በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች የልማት አውታሮችን ማውደም እድገትን የሚገታና ሃገራችንንም ቀድሞ ወደነበረችበት ድህነት እና ኋላ ቀርነት የሚመልሰን ከመሆኑም ባሻገር ሃገርን የሚበታትን በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

 ኢትዮጵውያን ድህነት አጥፊያችን መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ የእርስ በርስ ግጭትም ድህነትን ከማባባስና አገራችንን ከማውደም ሌላ ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በቅርቡ በአንዳንድ የአፍሪካ እና የአረብ አገራት ከተከሰቱት የእርስ በርስ ግጭቶች ተምረን ከእንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ ልንቆጠብ ይገባናል፡፡ ሊቢያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን፣ ሶርያና ሌሎች የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ የገቡ አገራት የደረሰባቸውን ማየትና ከዚህ ትምህርት መውሰድ ብልህነት ነው፡፡

ስለዚህ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ግጭትና ብጥብጥ እንዲሁም የልማት አውታሮችና ሌሎች ንብረቶችን ማውደም መፍትሔ አለመሆኑን በሰከነ መንፈስ ሊረዳው ይገባል፡፡ አሁን ላይ ዋናው መፍትሔ በሰከነ አዕምሮ ቆም ብሎ ማሰብና በሰከነ አዕምሮ መወያየት፣ ያሉንን ጥቄዎችም በሰላማዊ መንገድ ማቅረብና ላቀረብነውም ጥያቄ ምላሽ ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እኛ ወጣቶች የምናለማት እንጂ የምናጠፋት ሃገር ልትኖረን አይገባም፡፡
(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

No comments:

Post a Comment