Saturday, February 24, 2018

ለአዋጁ ተግባራዊነት ኃላፊነታችንን እንወጣ

(Feb 24, (ኢትዮጵያ ))--ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ ነው። የህዝብን ሰላምና ደህንነት የሚጥስና ለአደጋ የሚያጋልጥ ብሎም የህዝቦችን በአንድነት አብሮ የመኖር እሴት የሚንዱ ረብሻዎች በአንዳንድ ሥፍራዎች በመከሰት ላይ ናቸው። የመንግሥትንና የግሉን ዘርፍ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል፤ የህግ የበላይነትን የሚያዳክም፤ በምትኩ ደግሞ በኃይል የታገዘ ሁከትና ብጥብጥ እንዲሁም ሥርዓት አልበኝነት እየነገሰ ነው።

ይህን አለመረጋጋት ተከትሎም የንጹሀን ዜጎች ህይወት እየጠፋ ነው። ብሔርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችና የህዝቦች መፈናቀል እየደረሰ እንደሆነም ይታወቃል። በዚህ ሳቢያም የአገራችን ኢኮኖሚ እየተጎዳ፣ ንብረት እየወደመ፣ የህዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት እየታወከ፤ እንዲሁም ችግሩ እየተስፋፋና እየተራዘመ መሄዱን መንግሥት ተገንዝቧል።

በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት የሕግ ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግላቸው በተለያዩ መድረኮች ጥያቄ በማቅረብ ላይ ናቸው። በሕገ መንግሥቱና በሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ የተጋረጠውን ይህን አደጋ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት መንግሥት አማራጭ ያለውን መፍትሄ አስቀምጧል።

በመሆኑም ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበታል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ሕገመንግሥቱን እና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን ከአደጋ ለመከላከል በተዘጋጀ የአስቸኳይ ጊዜ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል። በመሆኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከየካቲት 9 ቀን 2010 ዓ. ም ጀምሮ የሚፀና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡

ህገ መንግሥቱ «ልዩ ልዩ ድንጋጌ» በሚለው 11ኛው ምእራፍ አንቀፅ 93ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን እና እንዴት እንደሚታወጅ በግልፅ አስቀምጧል። በቁጥር 1 «ሀ» ላይ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፤ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፤ የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው ይላል።

 በቁጥር 4 (ሀ) ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሰረት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡ በ (ለ) ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሰረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ፣ እስከ ማገድ ሊደርስ እንደሚችል በዝርዝር አስቀምጦታል።

 በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) መሰረት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት። ከላይ በንዑስ አንቀጽ (ሀ) ሥር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የሚታወጅ ከሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ሊሆን እንደሚገባ አስቀምጧል። አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛው ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ እንደሚሻርም ያብራራል።

 ይህን ታሳቢ በማድረግ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ የአዋጁ ማስፈፀሚያ መመሪያዎች ወጥተው ሥራ ላይ ውለዋል። ትናንትን መንግሥት በሰጠው ተጨማሪ ማብራሪያም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላ ሀገሪቱ ለ6 ወራት የሚጸና እንደሚሆን አሳውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከሚከለክላቸው ገደቦች መካከል ይፋ ወይም የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ የአደባባይ ሰልፍ ማድረግ ፣ የጦር መሳሪያና ስለታማ ነገሮችን ይዞ መጓዝ ይጠቀሳሉ፡፡ ያለፍርድ ቤት መበርበር፣ ለፀጥታው መረጋጋት አስጊ መስሎ ከተገኘ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማንኛውም አይነት የመገናኛ ዘዴዎች ሊቋረጡ ይችላሉ። የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስትና የአፈፃጸም መምሪያ ቦርድ ተቋቁሟል። እንደ ሁኔታው ታይቶ የሰዓት እላፊ ገደብ ማስቀመጥና ሌሎች ድንጋጌዎች ይኖሩታል። በ15 ቀናት ውስጥ ለተከበረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

 ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ህገ መንግሥታዊ መርሆዎችን ባከበረ መልኩ ለህብረተሰቡና ለሀገር ደህንነት ሲባል የታወጀ መሆኑን መረዳት ይገባል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍልም ለተግባራዊነቱ ተባባሪ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም ከምንም ነገር በላይ ለሀገርና ለህዝብ ደህንነት ቅድሚያ መስጠት የሰለጠነ አስተሳሰብ መሆኑን መረዳት ይገባናልና። በመሆኑም ለአዋጁ ተግባራዊነት ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት ይኖርብናል።
(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

No comments:

Post a Comment