Saturday, February 24, 2018

ልማትን እየጠየቁ ልማትን የማውደም አፍራሽ አባዜ!

(Feb 24, (ኢትዮጵያ ))--(በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በሀገሪቱ በብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች መስዋእትነት እውን የሆነው ሰላም ፋይዳ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን የልማት ባለውለታ የሆነ ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሰራች ትገኛለች፡፡

በሀገሪቱ የሰፈነው ሰላም ህዝቡ የዘመናት ባላጋራው በሆነው ድህነት ላይ እንዲዘምት ያስቻለው ሲሆን፣ ይህም ርብርብ የኢኮኖሚ እድገቱ ተከታታይ እና ፈጣን እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በድህነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ለመታደግ አስችሏል፡፡እድገቱ በእርግጥም ሰላም ካለ የማይደረስበት እንደሌለ አመልክቷል፡፡ምንም እንኳ ለኢትዮጵያውያን ሰላምን የመጠበቅ ጉዳይ አነጋጋሪ ባይሆንም፣ እነዚህ በሰላም ምርኩዝነት ስኬታማ ተግባር የተከናወነባቸው ወቅቶች የሰላም ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን በሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡

እንደሚታወቀው ሰላም ከሌለ የዜጎች ህይወት ፣አካል ፣ጥሪትና ሀብት የሀገር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ኢትዮጵያውያን ይህን በሚገባ ያውቃሉ፡፡ለዚህም ነው በእጃቸው የገባውን ሰላም ከመጠበቅም አልፈው ዘላቂ ለማድረግ የሚረባረቡት፡፡

የሰላም ፋይዳ ለኢትዮጵያውያን ይህን ያህል ቢሆንም ፣‹‹በጥባጭ ካለ ማን ንጹህ ይጠጣል››እንደሚባለው ፣ ሰላማቸውን የሚገዳደሩ ችግሮች ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል፡፡ በተለይ ከሁለት አመታት ወዲህ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተቀሰቀሱ ግጭቶች፣አለመግባባቶችና ባለቤት በሌላቸው ህገወጥ ሰልፎች ሳቢያ የሀገሪቱ ሰላም ደፍርሶ ቆይቷል፡፡በዚህ የተነሳም የዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ፣ አካል እያጎደለ ፣ ኢንቨስትመንት ለአደጋ እየተጋለጠ ፣ የህዝብ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እየተስተጓጎለ ይገኛል፡፡

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በተለያዩ መስኮች ለውጦችን ብታስመዘግብም ዕድገቱ ገና አልተቋጨምና ገና ያልተመለሱ በርካታ የህብረተሰቡ ጥያቄዎች እንዳሉ ለማንም ገልጽ ነው፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ጥያቄዎቹን በተለያዩ መንገዶች እያቀረበ ሲሆን፣ ይህን የህዝቡን ጥያቄ ተገን ያደረጉ ጸረ ልማቶች የጥፋት ተልዕኳቸውን ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፤ ይህ ባይሆንማ የልማት ያለህ እየተባለ ልማት አይወድምም ነበር፡፡

መንግስት እነዚህን ሀይሎች ወደጎን በመተው የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚረባረብ ሲያረጋግጥ ቆይቷል፡፡ይሁንና የድርጊቱን አሳሳቢነት በማጤን ችግሩ ህገመንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን በመረዳትም በመደበኛው ህግ የማስከበር ስርአት ብቻ መፍትሄ እንደማያገኝ በማጤን ባለፈው አመት መጀመሪያ ላይ የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከ ማውጣት ደርሷል፤ ለወራት የዘለቀው ይህ አዋጅ ችግሩ በመደበኛው የህግ ማስከበር መንገድ ሊያዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰም ደረጃ በደረጃ መነሳቱ ይታወሳል፤

ብዙም ሳይቆይ ችግሩ እያንሰራራ በመምጣቱም መንግስት ብሄራዊ የደህንነት ምክር ቤት በመመስረት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እያገረሸ የነበረውን የደህንነት ስጋት ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ይሁንና አሁንም የህዝብን ቅሬታ ተገን ባደረጉ ሀይሎች ግጭት፣አለመግባባት ህገወጥ ሰልፎችና አድማዎች አልፎም ተርፎ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በተለያዩ አካባቢዎች እስከ መሰንዘር ከዚህም ጋር ተያይዞ የዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደርሰዋል፡፡

መንግስት ግጭቶቹን እና አለመግባባቶቹን ተገን ያደረጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጉዳይ በጽሞና በመከታተል የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ባለበት በአሁኑ ወቅትም አድማዎቹ እየሰፉና እየተደራጁ መቀጠላቸው ተስተውሏል፡፡
ከዚህ አንጻር መንግስት ህዝቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች ለመፍታት የተለያዩ ተግባሮችን ሲያከናውንና ወደፊት ረጅም ርቀት ተጉዞም ነገሮችን በሰከነ አግባብ ሲመለከት ቆይቷል። ይህም በእነዚህ ወገኖች ዘንድ እንደ የዋህነት እና ተሸናፊነት የተወሰደ መስሏል፡፡

መንግስት ድካሙን ሲያምን ያለምንም መሸፋፈን ይቀበላል፡፡ይህንንም በተለያዩ ግምገማዎቹም እያረጋገጠ ነው፡፡የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ያረጋገጠውም ይህንኑ ነው። የልማቱም የድክመቱም ባለቤቱ እኔ ነኝ ፤አስተካክላለሁ ብሏል፡፡

 የህዝቡን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ የሚያውክ ተግባር እዚህም እዚያም ሲፈጸም አስተውሎ ወዲያውኑ እርምጃ አለመውሰዱ ሆደ ሰፊነቱን ያመለክታል፡፡ በሌላም በኩል ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታው የጎላ ፋይዳ እንዳለው የታመነበትን የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ስራ ለማጎልበትም ይረዳል፡፡

ይሁንና ችግሩ እየገዘፈ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዜጎችንና የሀገርን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ታላቅ ኃላፊነት አለበትና መንግስት ሰላምና መረጋጋቱን ለመጠበቅ ቁርጠኛ አቋም ይዟል፡፡ ይህንንም ሰሞኑን ከወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረዳት ይቻላል፡፡‹‹ሞኝ አውሬ ነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ ሁለቴ የሚወጋ›› እንደሚባለው ከአመት በፊት በተከሰተ ተቃውሞ አይነት ተቃውሞ ሀገሪቷና ህዝቧ እንደገና መጎዳት የለባቸውም፡፡

ከአመት በፊት የደፈረሰው ሰላም በህዝብና በሀገር ላይ ምን ያህል አሉታዊ ተጽእኖ እንዳሳረፈ ይታወቃል፡፡ሀገሪቱ በብዙ ስራ ከውጭ ያስመጣችውና ለውጡን ማጣጣም የጀመረችው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመጠኑም ቢሆን እንደተደናገጠ ፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብትን ለማፍራት በተከናወኑ ስራዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ባለሀብቶች ንብረት እንደወደመ ይታወሳል፡፡
መንግስት ኢንቨስትመንቱ እንዳይጎዳ ሌሎች ወደ ኢንቨስትመንቱ እንዳይሳቡ የሚያደርግ ደንቃራ እንዳይፈጠር በሚል ሰላምና መረጋጋቱን ወደነበረበት ከመመለስ ባሻገር ሀገሪቱ በሌላት ሀብት ለእነዚህ ባለሀብቶች በተለያዩ መንገዶች ካሳ በመክፈል እንዲያንሰራሩ አድርጓል፡፡ይህ መደገም የለበትም፡፡ከዚህ አንጻር መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁንም መውጣቱ ትክክልና ወቅታዊም ነው፡፡

የሀገሪቱን ሀብትና ገጽታ እያጠፉ ፣የልጆቿን ህይወት እየቀጠፉና ጥሪታቸውን እያወደሙ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ማቅረብ የሚጣረሱ ናቸው፡፡በዚህ ድርጊት የተሰለፉ ሀይሎች ራሳቸውን መለስ አድርገው በመመልከት በዴሞክራሲያዊ አግባብ መብታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ አሻፈረኝ ብለው በድርጊታቸው የሚቀጥሉ ከሆነ ፣ድርጊቱ ሀገርንና ህዝቧን በአያሌው ይጎዳልና መንግስት በእዚህ አፍራሽ ተግባር የተሰማሩ ሀይሎችን አሁንም ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ሊቀጣቸው ይገባል። ልማትን እየጠየቁ ልማትን የማውደም አፍራሽ አባዜ መገታት ይኖርበታልና፡፡
(ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት)

No comments:

Post a Comment