Tuesday, May 28, 2013

«ኢትዮጵያዊ ነህ አይደለህም? በኢትዮጵያዊነትህስ ታምናለህ አታምንም?» - ለዳያስፖራ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ጥያቄ

(May 28, 2013, (አዲስ አበባ))--እኚህ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ የ500ሺ ዶላር የህዳሴ ግድብ ቦንድ ነው የገዙት። ይህም እስከ አሁን በግል ከተፈጸሙ ድጋፎች ውስጥ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ ተመዝግቧል። በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በተለይም በዱባይ ለ32 ዓመታት የኖሩና እየኖሩም ያሉ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ለአፍሪካ መንግሥታት ትላልቅ የሲቪል ሄሊኮፕተሮችን ከመሸጥ ጀምሮ የህክምና መሳሪያዎችን የማቅረብና ሌሎችንም ትላልቅ ዓለም አቀፍ ንግዶችን በመስራት ላይ ይገኛሉ - አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር።

አቶ ዳዊት ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ መልካም ተግባራቸው በአገር ቤት ላለውና ለመላው ዳያስፖራም ጭምር አርአያ ይሆናልና ሃሳባቸውን በጥቂቱ እንዲያጋሩን ወደድን። ከሰሞኑ በሥራ አጋጣሚ በአገር ቤት በነበሩበት አጭር ጊዜ ውስጥ አግኝተን «ለግድቡ የዳያስፖራው ተሳትፎ እንዴት እየቀጠለ ነው? ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልስ ምን መደረግ አለበት?» በሚሉት ጉዳዮች ላይ አነጋግረናቸዋል። «የዓባይ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ አይደለም - ቁጭቱ የዘመናት ነው። የግድቡ ግንባታ ከእንግዲህ ወደ ኋላ አይቀለበስም።  

ከባዱ ነገር መጀመሩ ነበር፤ አሁን ተጀምሯል» ይላሉ። አባይን ጥቅም ላይ የማዋል ጉዳይ የማይመለከተው ኢትዮጵያዊ የለም። ካለ ግን የኢትዮጵያዊነትን ስም ብቻ የያዘ ባዕድ ለማለት ይቻላል። በርግጥ ፖለቲካዊ ጥቅምንና የግል ፍላጎትን ተንተርሰው ግድቡን በአሉታዊ መልክ የሚያስተጋቡ   ጥቂት የማይባሉ ሰዎች አሉ። ነገር ግን የእነሱን ጎዳና መከተል ከኢትዮጵያዊነት ያስወጣል።

 ዳያስፖራውን በግድቡ ዙሪያ ለማነቃነቅና ለማሳመን «ኢትዮጵያዊ ነህ አይደለህም፤ በኢትዮጵያዊነትህስ ታምናለህ አታምንም?» ብሎ መጠየቅ በቂ ነው። «ኢትዮጵያዊ አይደለሁም፤ በኢትዮጵያዊነቴም አላምንም፤ ኢትዮጵያ ውስጥም ወዳጅ ዘመድ የለኝም» የሚል ካለ እሱን ግድቡን እንዲደግፍ መጠየቅ አያስፈልግም። ይህ ሰው ታዲያ ድጋፉን ባይሰጥም በዓባይ ልማት ዙሪያ መጥፎ ከመናገር መቆጠብ ይኖርበታል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንና የሚኮራውን ድጋፉን እንዲሰጥ መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህ ሰው ያለጥርጥር ድጋፉን ይሰጣል። ትልቁ ቁም ነገር   «ምን ያህል ገንዘብ አዋጥቷል?» የሚለው አይደለም፤ በግድቡ ግንባታ ላይ ተሳትፏልን? የሚለው እንጂ - አቶ ዳዊት ያብራራሉ።

 «በውጭ የሚኖር ብዙ ኢትዮጵያዊ አገር ቤት ላለ ወዳጅ ዘመዱ በየጊዜው የሚልከው ገንዘብ ጊዜያዊ ርዳታ ነው። ለአባይ ልማት የሚያደርገው ድጋፍ ግን ዘላቂ ነው። ምክንያቱም አባይን ገድበን ኤሌክትሪክ  ማመንጨት ስንጀምር ኢንዱስትሪዎች በቂ ኃይል አግኝተው በስፋት ይንቀሳቀሳሉ።

ኢንዱስትሪዎች በስፋት ተንቀሳቀሱ ማለት ደግሞ ሰፊ የሥራ ዕድልና ትልቅ አገራዊ አቅም ተፈጠረ ማለት ነው። በዚህም ዳያስፖራው ገንዘብ እየላከ በቁጥ ቁጥ ሲረዳው የነበረው ወዳጅ ዘመድ ሁሉ ራሱን ችሎ ከተረጅነት እንደሚላቀቅ እሙን ነው» በማለትም የግድቡን ግንባታ መደገፍ የቱን ያክል አገራዊ አጀንዳ ፋይዳ እንዳለው ያስረዳሉ። ይህንን እውነታ በቅጡ በመገንዘባቸውም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ቦንድ ገዝተው ሀብት ወደ አገር ቤት እንዲፈስ ማድረጋቸውንም በመግለጽ ጭምር።
 
አቶ ዳዊት እንደሚሉት ዳያስፖራው በስፋት እንዲሳተፍ ንቅናቄ የመፍጠር ኃላፊነት በቀዳሚነት በኤምባሲዎች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው- የሌሎችም ኃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ። ኤምባሲዎች ይህንን ጉዳይ ግንባር ቀደም አጀንዳቸው አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል። «ነገር ግን 'የቱን ያክል ተንቀሳቅሰዋል? ምን ውጤትስ አስገኙ?' የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ነው። የሆነው ሆኖ ግን መንግሥት የላቀ ድርሻ መወጣት እንዳለበት ይሰማኛል። በአገር ቤትም ሕዝብና መንግሥት በስፋትና ቀጣይነት ባለው መልኩ መንቀሳቀስ አለባቸው። መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይገባዋል።

ግልጽ በሆኑ ሕጎች የሚመራ፥ ከሙስና የጸዳና የሕዝብ ጥቅም የሚቀድምበት መዋቅርና አሰራር ማጠናከር የግድ ነው። ሥራቸውን የሚያከብሩና ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ የሚወጡ ብቁ አመራሮችን በማብዛትና ስልጣንን ሽፋን አድርገው ለግል ጥቅም የሚሮጡ ኃላፊዎችን ለአፍታም ቢሆን ባለመታገስ ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት» ሲሉም ያከላሉ።
   
ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ላይ ትርጉም ባለው መልኩ መንቀሳቀስ የጀመረው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ከባተ ወዲህ ነው። እርግጥ ነው ከዚያ ቀደምም ቢሆን ዳያስፖራው በአገሩ ልማት ላይ በመጠኑም ቢሆን ይሳተፍ እንደነበር አይዘነጋም። በተለይም ወደ አገር ቤት የሚልከው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ የበርካታ ቤተሰቦችን የኑሮ ቀዳዳ ይደፍን ነበር። ይሁንና ቻይና፣ ህንድና እስራኤልን ከመሰሉና ዳያስፖራቸው የአገር ውስጥ ልማቶችን ትርጉም ባለው መልኩ እየደገፈ ከሚገኝባቸው አገራት ተሞክሮ ጋር ሲነጻጻር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከሚሌኒየሙ በፊት ተደንቆ የሚወራለትን ልማታዊ ድጋፍ አድርጓል ብሎ መናገር አይቻልም። ለእዚህ ገና በርካታ የውስጥና የውጭ ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ መዘንጋት የለበትም።

ፕሮፌሰር አባቡ ምንዳ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በተለይ በግድቡ ግንባታ ላይ የዳያስፖራው ድጋፍ አሁን ከታየውም በላይ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱና የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ዙሪያ በሰሜን   አሜሪካ ከዳያስፖራው ጋር ምክክር ሲደረግ ከከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ተሳታፊ ነበሩ። በወቅቱ በዳያስፖራው ዘንድ ከፍተኛ መነሳሳት ስለነበር ወዲያው የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት ታይቷል። ይሁንና ያኔ የማስተዋወቅ እንጂ የድጋፍ ማሰባሰብ ቅድመ ዝግጅት ባለመካሄዱ ገንዘብ የማሰባሰቡ ሥራ በቆንስላዎች ወደፊት እንዲሠራ ነበር አቅጣጫ የተቀመጠው። ይህ በመሆኑም በርካታ ገንዘብ ሳይሰበሰብ እንዲቀር አድርጓል። «ይህ ያልተጠቀምንበት መልካም አጋጣሚ ነው» ይላሉ።  

እርሳቸው እንደሚሉት የዳያስፖራ ማህበሩ ሕጋዊ ህልውና ከማግኘቱ አስቀድሞ ራሱን በሚያስተዋውቅበት ወቅት የማስተባበር ሥራ ያከናውን ነበር። ባለፉት ወራት ግን ራሱን በማጠናከር ሥራዎች ላይ ተጠምዶ ስለነበር ይሀ ነው የሚባል ተጠቃሽ ሥራ አከናውኗል ለማለት አይቻልም።   በአሁኑ ወቅትም ከመንግሥትና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ይህንኑ ሥራውን አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ ነው።

በተለይ ማህበሩ ለመንግሥት ያቀረባቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙ ከሆነ ድጋፉ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ይታመናል። ከእነዚሁ የማህበሩ   ጥያቄዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ዳያስፖራው በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በተለይም በባንክ ኢንቨስትመንት ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ፈቃድ ማግኘት ይገባዋል የሚለው ነው። የቢሮክራሲ እንቅፋቶችና የሙስና ማነቆዎችም ዳያስፖራውን በእጅጉ እየጎዱ ስለሆነ ከፍተኛ ትግል ሊደረግበት ይገባል። ለኢንቨስተር ዳያስፖራ እንደሚሰጠው ልዩ ትኩረት ሁሉ ገንዘብ ሳይሆን እውቀቱን ይዞ ለሚመጣው ምሁር ዳያስፖራም የተለየ ድጋፍ ሊደረግለት ያስፈልጋል። ዳያስፖራው የተሟላ መረጃ የሚያገኝበት የተደራጀ የመረጃ ማዕከል መኖር አለበት።

«ከዳያስፖራው 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማሰባሰብ ማቀዱን መንግሥት አስታውቋል። ይሁንና ከሶስት ወራት በፊት ባለኝ መረጃ እንኳን 16 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር ከዳያስፖራው ተሰብስቧል። ይህ ድጋፍ በቂ ነው ባይባልም በደንብ መንቀሳቀስ ከተቻለ ከዚህ በላይ ድጋፍ ማሰባሰብ ይቻላል። በተለይ የዳያስፖራውን ተነሳሽነትና ንቅናቄ አስተባብሮ ወደ ተግባራዊ ድጋፍ እንዲቀየር የሚያደርግ መዋቅር ያስፈልጋል። ዳያስፖራን በልማት ማሳተፍ በራሱ ከፍተኛ ገንዘብና ጊዜን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ ዳያስፖራው በያለበት የዓለም ጥግ ሁሉ ተዘዋውሮ ማስተባበርን የግድ ይላል። ስለሆነም በተቀናጀና ተከታታይነት ባለው መልኩ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል» በማለትም ያብራራሉ።
   
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ብዛቱ፥ አቅሙና አጠቃላይ መረጃው አልተጠናም። ይሁንና ከ2 እስከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የዓለም ጥጎች እንደሚኖሩ ነው የሚገመተው። አውሮፓና አሜሪካ የኢትዮ ጵያውያኑ ዋነኛ መዳረሻዎች ሲሆኑ፤ በርካታ የዳያሰፖራው አባላትም በእነዚሁ አህጉራት ይኖራል። አሁን አሁን በየዓመቱ ከመቶ ሺዎች የሚልቁ ኢትዮጵያውያን የሚጎርፉባቸው የመካከለኛው ምስራቅ አገራትም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ መዳረሻዎች ዋነኛ ሆነዋል። በአውሮፓና በአሜሪካ ከሚገኘው ዳያስፖራ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ከፍ ያለ የትምህርት ደረጃ ላይ የደረሱ ግለሰቦችን፣ እውቅና ያገኙ ተመራማሪዎችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን፣ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎችንና ሌሎችንም ያቀፈ ነው። የየራሳቸውን ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱና ተቀጣሪ ሆነው የሚሰሩ ባለሙያዎችም በርካታ እንደሆኑ ይነገራል።

 የዳያስፖራውን የህዳሴ ግድብ ቦንድ ሽያጭ የሚከታተለውና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቋቋመው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ሴክሬታሪያት ዳይሬክተር አምባሳደር ሻሜቦ ፊታሞ እንደሚናገሩት፤ ዳያስፖራው በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የራሱን ታሪካዊ አሻራ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ፍላጎት አለው። ግድቡ ብሔራዊ አጀንዳና የጋራ ጉዳይ መሆኑን በቅጡ ተገንዝቧል። ይህንንም በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል። ከራሱ አልፎም በልጁ ስም ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ሲታሰብ ደግሞ ዳያስፖራውን ያስመሰግነዋል። ከንግድ ባንከ የተገኙ መረጃዎችን ጠቅሰው፤ እንደሚገለጹትም    በአሜሪካ የሚኖሩት አብርሃ በዛብህ እና ዘመናይ መንግሥት የተባሉ ጥንዶች የ700ሺ ዶላር እንዲሁም ወልደ ብሩክ ጸጋዬ ንጉሥ እና ብሩክታዊት እዮሀብ የተባሉ የ230ሺ ዶላር ቦንድ ገዝተዋል። ፖርት አውቶኖሚ ኢንተርናሽናል የተባለና በጅቡቲ የሚገኝ ድርጅት ደግሞ የ500ሺ ዶላር  ቦንድ ከመግዛቱም በላይ 500ሺ ዶላር በስጦታ አበርክቷል።

 ትልቁ ጉዳይ መሆን ያለበት ይህንን ድጋፉን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል የተለያዩ አቅጣጫዎችን መቀየስ ነው። በዚህ ረገድ መንግሥት የዳያስፖራውን ድጋፎች የሚያጠናክሩና በአገሩ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች በባበሌትናትና በእኔነት ስሜት እንዲረዳቸው የሚያደርጉ የንቅናቄ፥ የድጋፍና ምቹ ሁኔታ የመፈጠር ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። በተለይ ዳያስፖራውን በመድረስ ረገድ የተኬደው ርቀት አጭር በመሆኑና መንግሥትም ዳያስፖራውን በውል ስላላወቀው በአገር ቤት ስላሉ ተጨባጭ እውነታዎች ጠንቅቆ እንዲገነዘብ ለማድረግ ተከታታይ የግንዛቤ  ማስጨበጫና የምክክር መድረኮች በስፋት ለማካሄድ ውጥን ተቀምጧል።

ይህንን ለማድረግም እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ የሚጠናቀቅና በኤምባሲዎች የሚከናወን አጠቃላይ የዳያስፖራ ሁኔታና መረጃዎች ዳሰሳ እየተካሄደ ነው። የግድቡን የቦንድ ሽያጭ ከማከናወን ጎን ለጎንም በየአካባቢው   የህዳሴ ግድብ ቦንድ ሽያጭና ድጋፍ አሰባሳቢ ምክር ቤቶችንም የመመስረት ሥራም ይከናወናል። በተጨማሪም የዳያስፖራውን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና የተሻሻለ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

 አምባሳደር ሻሜቦ እንደሚሉት በመጪው ሰኔ 8 ቀን 2005 ዓም በአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነው የዳያስፖራ ፖሊሲ ይፋ ይደረጋል። በዚሁ እለትም በተለያዩ የዓለም ጥጎች የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ የሚወክሉ 150 የዳያስፖራው ታዋቂ አባላት ወደ አገር ቤት ይመጣሉ። ይህንኑ ተከትሎም   በዳያስፖራው ተሳትፎ ዙሪያ ከሚዘጋጁት የምክክር መድረኮች በተጓዳኝ እነዚሁ ተወካዮች የህዳሴውን ግድብ ይጎበኛሉ። በጉብኝታቸውም ግድቡ የደረሰበትን ደረጃ ከተመለከቱና እስካሁንም ያደረጉት ድጋፍ የቱን ያክል በተግባር ላይ እንደዋለ ከተረዱ በኋላ ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ መነሳሳትን የሚፈጥሩበትና በተለይም ወደ የመጡበት አካባቢ ሲመለሱ ሌላውንም ዳያስፖራ በማነቃነቅ ረገድ ከፍ ያለ የቤት ሥራ ይዘው እንዲያቀኑ ይደረጋል።

 ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሆኑ የውጭ አካላት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሱ የውጭ ባለሀብቶችና የጎረቤት አገር ዜጎችም ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል። ዳያስፖራው በአገር ልማት ላይ ሁለገብ ተሳትፎ የማድረግ አቅም እንዳለው መንግሥት በቅጡ ተገንዝቧል። ለተግባራዊነቱም ቀላል የማይባሉ ርምጃዎችን ተጉዟል። ለማሳያነትም በየክልሉና በትላልቅ ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ በክፍለ ከተሞችም ጭምር የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚከታተሉ አካላትን አዋቅሯል።

 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ከተማ እንደሚሉት ዳያስፖራው በአሁኑ ወቅትም ቢሆን የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ማግስት እንደነበረው ዓይነት ሊባል የሚችል ደጋፍ እያደረገ ይገኛል። ለማሳያነት ከሰሞኑ እንኳን ዳያስፖራው በኒው ዮርክ የ100ሺ ዶላር፤ በካናዳ የ80ሺ ዶላር፤ በሂዩስተን የ50ሺ ዶላር፤ በዱባይ የ2ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በኖርዌይ የ151 ሺ የኖርዌይ ክሮነር ቦንድ ገዝቷል። ግድቡ ዳያስፖራውን እያሳተፈ ከመሆኑም በላይ በአገሪቱ የታዩትን ለውጦች እንዲያጤንና ከመቼውም በበለጠ ለአገሩ እንዲቆረቆር በማድረግ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

 በተመሳሳይ ዳያስፖራው ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እስካሁንም መቀጠሉን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃዎች የሚያመለክቱት። ከሰሞኑ እንኳን በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፎች እየተደረጉ ነው። ለማሳያነት  በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖምና በዩናይትድ   ኪንግደምና በስካንዲኔቪያን አገሮች የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ከበደ በተመራው የሰሞኑ የሎንዶን ምክክር መድረክ ላይ በአገራቱ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ለህዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት። ዶክተር ቴዎድሮስም ዳያስፖራው በግድቡ የቦንድ ግዢ ያሳየው ተሳትፎ የሚያስመሰግን መሆኑን በመጠቀስ ይህም እስከ ግድቡ መጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚያስፈልግ ነው በአጽንኦት የገለጹት።

 በሌላ በኩል በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ስዩም መስፍን በተገኙበት ምክክር ያደረገው በቤጅንግ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ማህበርም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የሚጠበቀው። በተመሳሳይ በቅርቡ በቻይና ሻንጋይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን 26ሺ 400 ዶላር ቦንድ የገዙ ሲሆን፤ ድጋፋቸውንም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው በሻንጋይ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ያስታወቀው። እነዚሀ ሁሉ እንቅስቃሴዎች ታዲያ ይበልጥ መስፋት ያለባቸው ሲሆን፤ በተለይም መንግሥት በኤምባሲዎችና ቆንስላዎች አማካኝነት ዳያስፖራውን የማስተባበርና ንቅናቄ የመፍጠር ሥራዎችን አጠናከሮ ሊቀጥል ያስፈልጋል።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

3 comments:

Anonymous said...

The Ethiopians living in the country and the diaspora have the same stand when it comes to the so called renaissance dam. We all know it is a strategy orchestrated by the ex-dictator to loot Ethiopians and deny their freedom. Ethiopians, unlike you people who fought us along side with Eritreans and Egyptians, love their country. And, it is very funny that you have the gut to preach about EThiopiawinet after u gave our lands to sudan and port to Eritrea.

Anonymous said...

IF YOU ARE NOT ETHIOPIAN YOU DON'T LIKE THE PROGRESS AND PROSPERITY OF THE COUNTRY STAY BACK
AND YOU WILL SEE THE FUTURE OF OUR MOTHER LAND
ETHIOPIA ABIBI GETA KANCHI GAR NEW LEZELALEM

Anonymous said...

TPLF/EPRDF has no moral ground to preach about Ethiopia & Ethiopiawnet. They are the ones working against the unity and the interest of Ethiopia since their birth.
To date, as far I know, they failed to organize a meeting under the name of Ethiopia in the Diaspora (as most of the meetings held under Tigray, Amhara, Oromo, ...); but telling us that they are the 'best Ethiopians' and the people who don't buy bond are not Ethiopians. As we are aware, TPLF, as the name indicated, is a liberation front and ironically this same party run the entire country-Ethiopia. The question of Ethiopia & Ethiopianwet should go to this party first and most, then we all are ready to answer.

Post a Comment