Wednesday, November 01, 2017

በባህር ዳር ከተማ ጫት በየቦታው እንዳይቃም ተከለከለ

(ጥቅምት 22, (ባህርዳር))--በባህርዳር ከተማ የጫት አሉታዊ ጎን በወጣቱ ላይ እየሰፋ በመምጣቱ ጫት በየቦታው እንዳይቃም መከልከሉን የከተማዋ ኮምንኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የጽ/ቤቱ ሀላፊ አቶ በሰላም ይመኑ እንደገለፁት ከጫት ጋር ተያይዞ ህገ-ወጥ ንግድ ቤቶች ተስፋፍተዋል፤ ከባህል የራቁ እንቅስቃሴችም ተበራክተዋል፡፡ የከተማዋን ዓለም አቀፋዊነት እና የቱሪስት ማዕከልነት ለማበልፀግ በሚደረገው እርምጃም ጫት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉም ተገልጿል፡፡

በተገለፁት ምክንያቶች ጫት በከተማዋ ውስጥ በየቦታው እንዳይቃም የከተማ አስተዳደሩ መከልከሉን አቶ በሰላም ተናግረዋል፡፡ የወጣውን ደንብ ተከትሎም የከተማዋ አስተዳደር እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በሀገሪቱ ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በጫት መሸፈኑም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአማራ ክልል የሞጣ ከተማ አስተዳደር ቀድማ ጫት በየቦታው እንዳይቃም በመከልከል ቀዳሚ ሆናለች፡፡

የአማራ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን በጫት ላይ 5 በመቶ ተጨማሪ የታክስ ጭማሪ በመጣል ጫት መቃም እንዳይበረታታ ለማድረግ እሰራለሁ ብሏል፡፡ የጫት ገበያም በውስን ቦታዎች ብቻ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በአማራ ክልል ከሚመረት ጫት ውስጥ 20 በመቶ ብቻ ወደ ውጭ እንደሚላክ ከገቢዎች ባለስልጣን የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡
ምንጭ፡- የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት
ኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን

No comments:

Post a Comment