Monday, April 20, 2015

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በንጹሃን ዜጎች ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ

(ሚያዚያ, 12/2007, አዲስ አበባ , (ኢ ዜ አ)))--ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አይ ኤስ በተሰኘው የሽብር ቡድን በግፍ በተገደሉ ኢትዮጵያውያን ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገለጹ። "የሐይማኖት ጭንብል ለብሶ ዓለምን ሊያጠፋ የመጣውን አሸባሪነት በጋራ ለመታገል ይገባል" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝተዋል። በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ወደ አገራቸው ለመመለስ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን የግፍ ግድያ በጽኑ ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሆነው ሽብርተኝነትን ሊዋጉ ይገባል ብለዋል። "የሐይማኖት ጭንብል ለብሶ መምጣቱ ሳያዘናጋን መላውን የሰው ዘር ለማጥፋት የተወጠነ መሆኑን በመገንዘብ በአንድነት በአንድ ሃሳብ መቆም አለበን" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ወደ አገራቸው ለመመለስ መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎችን ኢላማ በማድረግ በደቡብ አፍሪካ የተከሰተውን ግድያና ማፈናቀል ለማስቆም መንግስት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ወደሚገኙ አገራት ለመሄድ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንም ከድርጊታቸው በመቆጠብ በአገር ውስጥ እየተፈጠረ ባለው የስራ እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ: የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት 

No comments:

Post a Comment