Monday, March 16, 2015

«የዓባይ ልጆች በመሆናችን በጋራ መስመጥን ሳይሆን በጋራ መዋኘትን መርጠናል» - ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ

(መጋቢት 7, 2007, (አዲስ አበባ))--«ኢትዮጵያ እና ግብፅ የዓባይ ልጆች በመሆናችን ዕጣ ፈንታችንም የጋራ ነው። አንድም በጋራ እንሰምጣለን አልያም በጋራ እንዋኛለን። እንደምታውቁት በጋራ መዋኘትን መርጠናል» ሲሉ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ። ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ያላትን ግንኙነት ልማትን በማፋጠንና ሽብርተኝነት በመዋጋት መተባበር እንደምትፈልግም አመለከቱ።

በሻርማ ኤል ሼክ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የኢኮኖሚ ልማት ጉባዔ የተካፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደተናገሩት፤ ልማት «የተቀናጀ ጥረትና በቅንነት ላይ የተመሠረተ አጋርነት» በመንግሥታትና በተቋማት መካከል ይሻል። ኢትዮጵያና ግብፅን የዓባይ ወንዝ እንዳስተሳሰራቸው ሁሉ ኢትዮጵያ ግንኙነቱን ልማትን በሚያራምድና ሽብርተኝነትን በመከላከል ዘርፎች እንዲጠናከር ትሻለች ብለዋል።

«በእርግጥም ለብቻችሁ ልማትን ማሳካት አትችሉም» በማለት የትብብርን አስፈላጊነት የአፍሪካና የባህረ ሰላጤው አገሮች ከግብፅ ጋር ያላቸውን አንድነት በገለጹበት ጉባዔ ላይ ተናግረዋል።«የዓባይ ልጆች በመሆናችን ዕጣ ፈንታችንም የጋራ ነው። አንድም በጋራ እንሰምጣለን አልያም በጋራ እንዋኛለን። እንደምታውቁት በጋራ መዋኘትን መርጠናል» ሲሉም አመልክተዋል። ግብፅ ሽብርተኝነትን በመዋጋትና አካባቢውን ሰላማዊ በማድረግ ተባብራ እንድትሠራም ጠይቀዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ


 

No comments:

Post a Comment