Tuesday, January 13, 2015

ከጀጎል ማዶ - የዳያስፖራ መንደር

(ጥር 4/2007, (አዲስ አበባ))--በከተሞች ዜጎች ደጋግመው ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል ዞሮ መግቢያ ቤት ዋናው ነው። የጥያቄው ብዛት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲጨምር ይታያል። ምንም እንኳ ችግሩን ለመፍታት ደፋ ቀና እየተባለ ቢሆንም ቀደም ባሉት ጊዜያት የሚፈለገው ቤት ሳይሰራ ሲንከባለል በመምጣቱ ጫናውን አክብዶታል። መንግሥት ጥያቄውን ለመመለስ እዚያም እዚህም ተስፋ ሰጪ ነገሮች እያሳየ ነው። ሆኖም ያለው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ አሁንም ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ የሚያመላክት ነው። የቤት ፈላጊው ቁጥር ሲሰላ ቁጥሩ ቀላል አይደለም። ቤት ጠይቆ ካገኘው ያላገኘውም ይበልጣል።

በክልል ዋና ዋና ከተሞችና በአዲስ አበባ የቤት ፈላጊዎች ቁጥር በሚሊዮን የሚቆጠር ነው። ቤት ፈላጊዎች ይህን ቁጥር አስልተው «መቼ ይደርሰኝ ይሆን?» ብለው ራሳቸውን ሲጠይቁ ለብዙዎች በጭላንጭል የምትታይ የብርሃን ተስፋ ያህል ይሆንባቸዋል። መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሲንከባለል የመጣውን ችግር ለመፍታት ወገቡን እጥብቆ እየሠራ ቢሆንም አሁንም ገና ከፊቱ ለፊቱ ብርክ ብርክ የሚያስብል ዳገት እንደሚጠብቀው የቤት ፈላጊው ቁጥር ያሳያል።

የዞሮ መግቢያ ጥያቄ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ብቻ አይደለም። በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵ ያውያንም ጥያቄ ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ትኩረት የተደረገው ለአገር ውስጥ ዜጎች ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ጥያቄ እየገፋ መጥቷል። መንግሥት እንደ አገር ውስጥ ዜጎች ሁሉ ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጥ አሰራር በመዘርጋት ጥያቄውን እየመለሰ ነው። የሐረሪ ክልል ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ አስራር ከመዘርጋቱ በፊት በራሱ ተነሳሽነት ቀደም ብሎ በውጭ ለሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የቤት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ፕሮጀክት ቀርጾ ተግባራዊ አድርጓል። በዚህም በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የቤት ጥያቄያቸው ከማንኛውም አካባቢ ቀድሞ መልሶላቸዋል።

የፕሮጀክቱ ጅማሬ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ነው። የሐረር ቀን ሲከበር በውጭ አገር የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ታድመው ነበር። በድግሱ ላይ በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች በሐረር ነዋሪ እንዲሆኑና ቅርበታቸው እንዲጨምር የቤት ባለቤት የሚያደርግ ፕሮጀክት ተነደፈ። የተነደፈው ፕሮጀክትም ተግባራዊ እንዲሆን አሰራር ተዘረጋ።

በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ዝግ የሂሳብ ደብተር በመክፈትና ውክልና ሰጥተው ለቤቱ የሚያስፈልገውን ሃያ በመቶ እንዲቆጥቡ በማድረግ ሥራው ተጀመረ። የከተማ አስተዳደሩ አቅማቸውንና የሚፈልጉትን የቤት አይነት ማጥናት ጀመረ። በጥናቱም በውጭ የሚኖሩት ዜጎች አቅም ዝቅተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ሆኖ አገኘው። ፍላጎቱን መሰረት በማድረግም ስድስት አይነት የቤት ዲዛይኖችን አዘጋጀ። አቅማቸውንና የዲዛይን ምርጫቸውን መሰረት በማድረግም በመጀመሪያው ዙር ሃምሳ ቤቶቹን መገንባት ጀመረ። ባለፈው መስከረም ቤቶቹ ተጠናቅቀው ከፍያውን ሙሉ በሙሉ ላጠናቀቁ ሃምሳ ሰዎች ቤቶችን አስረክቧል።

ቤቶቹ የተሰሩበት አካባቢ «የዲያስፖራ መንደር» የሚባል ስያሜ ተሰጥቶቷል። መንደሩ ከከተማዋ በስተደቡብ ምዕራብ ይገኛል። መሐል ከተማ ሆኖ ቁልቁል አሻግረው ሲያዩት በመስመር ይታያሉ። ዘመናዊና ባህላዊን የሐረሪ ቤት አሰራር የሚያንጸ ባርቁት ቤቶች ከተጨናነቀው የጀጎል ግንብ ጋር እላይና ታች ሆነው ይገራመማሉ። «እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ» ፉክክር የያዙ ይመስላሉ። የቤቶቹ አሰራር እጅግ ማራኪ ነው። የሐረሪ የኪነ ህንጻ አሰራር ጥበብ ያንጸባርቃሉ።

ወደ ውስጣቸው ሲዘለቅ ባህላዊና ዘመናዊን የቤት ውስጥ አሰራር አጣምረው ይዘዋል። ዘመናዊ ገጽታቸው ሳሎን፣ የአዋቂዎች መኝታ ቤት፣ የልጆች መኝታ ቤትና የመሳሰሉትን ይዘዋል። የሐረሪዎችን ባህላዊ የቤት ውስጥ ገጽታ ደግሞ ከበሩ ፊት ለፊት በተደራራቢ መደብ አሸብርቆ ይታያል። ከጎኑ የተለያዩ ባህላዊ ክፍሎችም አሉት። ቤቶቹ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የተመልካችንም መንፈስን ይገዛሉ።

ፕሮጀክቱን በመጠቀም የቤት ባለቤት ከሆኑት መካከል አቶ ሰለህዲን እንድሪስ አንዱ ናቸው። ለሃያ ዓመታት ያህል በካናዳ ቶሮንቶ ኖረዋል። በ2002 ዓ.ም መጥተው በነበረበት ወቅት ከከተማ አስተዳደሩ የቀረበላቸው «የቤት ባለቤት ሁኑ» ጥያቄ ተቀብለው ተግባራዊ በማድረግ የቤት ባለቤት መሆናቸውን ይናገራሉ።  ሥራው ሲጀመር መንግሥት ላይ ትንሽ ጥርጣሬ እንደነበረባቸው ያነሳሉ። እየፈሩም ቢሆንም ግን ጥያቄውን ተቀበሉ። ዛሬ ላይ ሆነው በወቅቱ የወሰኑት ውሳኔ ትክክል መሆኑን አምነውበታል። ምክንያቱም ደፍረው በመግባታቸው ዛሬ ዘመናዊና ባህላዊ አሰራርን ያዋሀደ ዘመናዊ ቤት ባለቤት «ሆኛለሁ» ይላሉ። የሚፈለጉትን አይነት ቤት ተሰርቶ መስጠታቸውንና በጣም ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራሉ።

በሥራው ሂደትም ምንም ዓይነት ችግር አለመግ ጠሙንና በሚፈለገው ጥራትና ወቅት መረከባቸውን ያነሳሉ። አሁን የቀራቸው መብራትና ውሃ ማስገባት ብቻ ነው። «የመብራትና ውሃ አገልግሎት ሳገኝ በቤቱ ውስጥ መኖር እችላለሁ። ጊዜ ሳላባክን በተመጣጣኝ ዋጋ ይህን አይነት ቤት በማስረከቡ የከተማ አስተዳደሩን አመሰግናለሁ» ሲሉ ነው የከተማ አስተዳደሩ ላደረገላቸው ነገር ምስጋና ያቀረቡት። በውጭ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መምጣት ይፈልጋሉ። ወደ እዚህ መጥተው ለመኖር ሲያስቡ የሚኖሩበት ቤትና ሌሎች ነገሮችን ሲያስቡ ተሰፋ ይቆርጣሉ። መንግሥት የቤት ችግሩን በዚህ መልኩ ከፈታላቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ ብዙዎች ያስባሉ። እርሳቸውም የቤት ባለቤት ከሆንኩ በኋላ ወደ አገራቸው ለመመለስ ቀልባቸው እንደተነሳሳ ይናገራሉ። በሪልእስቴት ለመሰማራት ጥናት እያጠኑ እንደሆነም ያነሳሉ። መንግሥት በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች የቤት ባለቤት ለማድረግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ያሳስባሉ።

የሐረሪ ክልል የመኖሪያ ቤቶችና የመንግሥት ቤቶች ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱልሐኪም አብዱልመልክህ ለከተማ ነዋሪዎች ከሚያደረገው የ20/80 እና የ40/60 የቤቶች ግንባታ በተጨማሪ በውጭ ለሚኖሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ቀደም ብሎ ቤት በመገንባት የክልሉ መንግሥት አርአያነት ያለው ሥራ ማከናወኑን ይጠቁማሉ።  ክልሉ የ20/80 የሁለት መቶ ፎቆችን ግንባታ አጠናቅቆ ለተጠቃሚዎች አስረክቧል። ሦስት ሺ አባወራዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ቤቶቹ ለተጠቃሚዎቹ ከመተላለፋቸውም በላይ ለግንባታው ወጪ የተደረገው ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር ተመልሷል። ቀድሞ ብድርን በመክፈልም ክልሉ አርአያነት ያለው ሥራ ሠርቷል። በግንባታው ሂደትም አስር ሺ የሚሆኑ ኢንተር ፕራይዞች በመሳተፍ ተጠቃሚ ሆነዋል።

በሐረር ከተማ ከአስር ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የቤት ፈላጊዎች መኖራቸው በጥናት ተረጋግጧል። የቤት ፍላጎቱን ለመፍታት በአሁኑ ወቅት የ40/60 የቤት ፕሮጀክት እየተሠራ ነው። በቀጣይ ዓመት የፌዴራል መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መገንባት የተቋረጠውን የ20/80 መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት ለመጀመር ክልሉ ዝግጅት እያደረገ ነው። ኃላፊው እንደሚሉት ለዲያስፖራዎች የቤት ግንባታ የተጀመረው የአካባቢው ተወላጆች ከአገራቸው ጋር ለማስተሳሰር ነው። በሂደትም ወደ አገራቸው ያላቸውን ሀብትና እውቀት ይዘው በመምጣት ራሳቸውንና አገራቸውን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለመገፋፋት ያለመ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን የከተማዋን የቤት ችግር ለማቃለል። የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት ነው። ተሰርተው ከተላለፉት ቤቶች ሃምሳ ሁለት ሚሊዮን ብር ተገኝቷል።

ግንባታቸው አልቆ የተላለፉት ቤቶች ለመገንባት የተገባው «በጨበጣ ነው» የሚሉት ኃላፊው ውጤቱ ከተጠበቀው በላይ አጥጋቢ እንደሆነ አንስተዋል። ዲዛይን ሠርቶ ከማስመረጥ ጀምሮ ግንባታውን አጠናቅቆ እስከማስረከብ የተለያዩ ውጣ ውረዶች ማሳለፋቸውንና ብዙ ትምህርት መውሰዳቸውን አንስተዋል። ከዚያ ትምህርት በመውሰድ ሌሎች በውጭ የሚኖሩ አንድ ሺ ዲያስፖራዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ አቅደው መንቀሳቀስ መጀመራ ቸውንና ከዚያ ውስጥ የመቶ ቤቶችን ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ሥራው ሲጀመር በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ጥርጣሬ ነበራቸው የሚሉት ኃላፊው፤ ከፍተኛ የሆነ የማስገንዘብና የማስረዳት ሥራ በመደረጉ ችግሩ ተቀርፏል። ገንዘብ ባገኙ ጊዜ እንዲቆጥቡ በማድረግ ቤቶቹ ተሠርተው እስኪ ጠናቀቁ ድረስ እንደሚገነባላቸው ከሦስት መቶ ሺ እስከ ሰባት መቶ ሺ ብር ሙሉ በሙሉ በመክፈል ቤታቸውን በዕጣ በፍትሐዊነት ተረክበዋል። እየተዘጋጀ ያለው የዲያስፖራ ቤት ልማት መመሪያ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን የቤት ፍላጎት በወጥነት ለመፍታት እንደሚያስችል አንስተዋል። በክልላቸው የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው ለመቀጠል እንደሚ ያግዛቸው ይገልፃሉ።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከአገራቸው ጋር ለማስተሳሰርና የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለማድረግና በልማት ለማስተሳሰር የሚያስችል የዲያስፖራ ቤቶች ልማት መርሃ ግብር ለመዘርጋት መመሪያ ተዘጋጅቶ ውይይት ተደርጎበታል። በቅርብ ጊዜ ውስጥም ተግባራዊ መሆን እንደሚጀመር ተገልጿል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የቤት ባለቤት ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት መልካም ነው። ጅምሩ ተጠናክሮ ከቀጠለ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል። ለአገራቸው እውቀትና ሀብታቸውን በማፍሰስ አገራቸውንና ራሳቸውን ተጠቃሚ ያደርጋሉ።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment