Wednesday, January 14, 2015

በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል የሕብረት ባንክ ቅርንጫፍ ላይ በደረሰው ቃጠሎ የደንበኞች አገልግሎት አይስተጓጎልም

(ጥር 5/2007, (አዲስ አበባ))--በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል የህብረት ባንክ አክሲዮን ማህበር ቅርንጫፍ ከትናንት በስቲያ የደረሰው ከፍተኛ ቃጠሎ በደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መስተጓጎል እንደማይፈጠር የባንኩ ፕሬዚዳንት አስታወቁ።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ በመሃል ፒያሳ በሚገኘው የእተጌ ጣይቱ ሆቴል ላይ በደረሰው ከፍተኛ ቃጠሎ በግቢው ውስጥ ይገኝ በነበረው የሕብረት ባንክ አክሲዮን ማህበር ቅርንጫፍ ላይ ጉዳት ደርሷል። በቃጠሎውም በጥሬ ገንዘብና አስፈላጊ ሰነዶች ላይ ጉዳት አልደረሰም። በወቅቱ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ጥሬ ገንዘቡ ወደ ዋና መስሪያ ቤት ተወስዷል። ይሁንና አንዳንድ ሰነዶችና የመልገገያ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

ውድመት የደረሰባቸው ሰነዶችና የመገልገያ መሣሪያዎች ግምት ከሁለት ሚሊዮን ብር እንደማይበልጥና ባንኩ ኢንሹራንስ ስላለው በደንበኞች ወይንም ባንኩ ሀብት ላይ የሚያመጣው ኪሳራ እንደሌለም ጠቁመው፣ «ይሁንና በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል ላይም ሆነ በባንኩ ቅርንጫፍ ላይ የደረሰው ቃጠሎ የአገር ሀብት በመሆኑ አሳዛኝ ነው»ብለዋል። በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በሚገኘው ቅርንጫፍ ደንበኞች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይመጡ እንደነበር አመልክተው ፤ነገር ግን ለጊዜው እንደሚቋረጥም አስረድተዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ንግግር፤ የባንኩ መረጃ አያያዝ በኔት ወርክ ሰንሰለት የተሳሰረ በመሆኑ ማናቸውም የደንበኛ አገልግሎት አይተጓጎልም። ደንበኞች በዋና መስሪያ ቤት ጨምሮ በሌሎች የሕብረት ባንክ አቅራቢያ ቅርንጫፎች መጠቀም ይችላሉ።

በቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ይሰሩ የነበሩ ሠራተኞ በዕለታዊ ኑሮአቸው ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደማይፈጠርና አስፈላጊውን የሠራተኛ መብትና ጥቅም እንደሚያገኙም አቶ ታዬ ጠቁመዋል።  ሕብረተሰቡ፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ የፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች መረጃ በፍጥነት በማስተላለፍ ቃጠሎውን ለመቆጣጠር ባደረጉት ርብርብ ጉዳቱን ለመቀነስ በማስቻላቸው ምስጋና አቅርበዋል።
ቅርንጫፍ ባንኩ ከ10 ሺ በላይ ደንበኞች እንደነበሩት አመልክተዋል።

የእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ ሲሆን በ1888 ዓ.ም የተገነባ ነው። ከትናንት በስቲያ በደረሰው ቃጠሎ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። ሆቴሉ የኢትዮጵያን ገፅታ በውጭው ዓለም በማስተዋወቅ ለገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚናም እንደነበረው ተጠቁሟል። ሕብረት ባንክ አክሲዮን ማህበርን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment