Monday, January 05, 2015

የሀና ላላንጎ ጉዳይ በዝግ ችሎት መታየት ጀመረ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2007
አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2007
(ታህሳስ 27/2007, (አዲስ አበባ))--የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሶስተኛ ወንጀል ችሎት የ16 ዓመቷን ታዳጊ ሃና ላላንጎን አስገድደው የመድፈር ወንጀል ፈፅመውባት ለህልፈት ዳርገዋታል የተባሉትን አምስት ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ክስ ለማንበብ ይዞት በነበረው ቀጠሮ ጉዳዩ በዝግ ችሎት እንዲታይ ወሰነ፡፡

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በዝግ ችሎት እንዲታይ የወሰነው የህብረተሰቡንና የተጎጂ ቤተሰቦችን ሞራል ለመጠበቅ፣ ከባህል አኳያ የሚያስከትሉትን አንድምታዎች ከግምት በማስገባትና ከወንጀል ድርጊቱ ጋር በማዛመድ እንዲሁም በክሱ ላይ የጠቀሳቸውን ሞራል የሚነኩና አስጸያፊ ነገሮች ዓቃቤ ህግና ተከላካይ ጠበቆች በግልጽ ለመነጋገር እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡አንድ ጉዳይ በዝግ እንዲታይ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ባህልን፣የተጎጂ ቤተሰቦችን ሞራል የሚጎዳ ጉዳይ በዝግ እንዲታይ የሚፈቅድ የህግ ድጋፍ መኖሩም ታውቋል፡፡

በህገ መንግሥቱ ስለተከሰሱ ሰዎች መብት በአንቀጽ 20 እንደሚደነግገው የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመስማት መብት አላቸው፡፡ሆኖም የተከራካሪዎቹን የግል ህይወት፣የህዝብን የሞራል ሁኔታና የሀገሪቱን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል፡፡

ፍርድ ቤቱ በትናንት ውሎው በተከሳሽ ጠበቆች በኩል የቀረቡትን ሁለት መቃወሚያዎች ውድቅ አድርጓል፡፡ሁለት ክሶች መቅረባቸውን አረጋግጦ ጥር 1ቀን 2007ዓ.ም የዓቃቤ ህግን ምስክር ለማድመጥ ቀጥሯል፡፡

አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ መስርቶት የነበረው ክስ፤ በመድፈር ወንጀል የወንጀል ህጉን 626 (1)ና በተፈፀመባት አሰቃቂ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተያይዞ ለህልፈት በመዳረጓ ደግሞ የወንጀል ህጉን 539 (1)ሀ በመጥቀስ ነበር፡፡626 (1)ብሎ የጠቀሰውን «የተፈፀመው የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በስምምነት እንደሆነ መልዕክት ስለሚያስተላልፍና በሟች ላይ የተፈፀመው ድርጊት ግን እንደ ክስ ዝርዝሩ ተገዳ እየጮኸች በመሆኑ ክሱን በደንብ ሊያብራራ የሚችለው አንቀፅ 620 (3) ነው» በማለት እንዲቀየርለት መጠየቁ ይታወቃል፡፡ፍርድ ቤቱም በወንጀል ህጉ 119 መሰረት የቀረበው ምክንያት ክስ ለማሻሻል በቂ በመሆኑ አቤቱታውን ተቀብሎ መቀየሩ ይታወሳል፡፡አንቀፅ 620 (1) የሚያስከትለው ቅጣትም ከቀደመው 626 (1) ከፍ ያለ ነው፡፡ክሱ የሚታየውም በተሻሻለው ክስ መሰረት ነው፡፡
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ

Related topics: 
በሃና ላይ የመድፈርና የግድያ ወንጀል በፈጸሙ ተጠርጣሪዎች ላይ እስከ ሞት የሚያስቀጣ ክስ ተመሰረተ:
«ለሃና ፈጣን እርዳታ አልተደረገም» ሲሉ አባቷ ተናገሩ 
Kidnapped, raped and left for dead: who will protect Ethiopia's girls?


No comments:

Post a Comment