Wednesday, January 14, 2015

ፓትሪያሪኩ ወደ ግብፅ ሄዱ

(ጥር 4/2007, (አዲስ አበባ))--በኢትዮጵያ ኦርቶ ዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መካከል ያለው ግንኙነት በዳበረ ቁጥር የአገራቱ የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነትም የበለጠ እንደሚጎለብት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። ብፁዕነታቸው ከግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ መሪ ከሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ በተደረገላቸው ግብዣ መሠረት ወደ ግብፅ አምርተዋል።



OCP News Service
OCP News Service
Courtesy of theorthodoxchurch

በግብፅ በሚያደርጉት የአምስት ቀናት ጉብኝት የሁለቱን እህትማማች ቤተክርስቲያን ወዳጅነት በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ዙሪያ ከግብፁ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን አቻቸው ጋር እንደሚወያዩ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ ከእስልምና መሪዎች እና ከህብረተሰቡ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩም ተናግረዋል።

«ኢትዮጵያውያን አባይን እየገደቡ ያሉት ራሳቸውን ከድህነት ለማውጣት እንጂ የግብፅን ሕዝብ የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላቸው፣ ግድቡም ለሁለቱም አገራት ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አስረዳለሁ» ብለዋል። ሁለቱ ቤተክርስቲያናት ታሪካዊና ጥንታዊ ወዳጅነት እንዳላቸው የገለጹት አቡነ ማቲያስ፤ «ይህን ግንኙነታቸውን ለማጎልበት በሁለቱም አገራት ያለው ፍላጎት መልካም በመሆኑ ወዳጅነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል» ብለዋል።

የቤተክርስቲያናቱ ግንኙነት በዳበረ ቁጥርም በአገራቱ መካከል የሚኖረው ወዳጅነት የበለጠ እንደሚጎለብት ገልጸው፤ በጋራ የሚሠሩባቸውና የሚመክሩባቸው ጉዳዮችም እየጨመሩ እንደሚሄዱ ጠቁመዋል።  በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የግብፅ ጉዞ ሽኝት ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር መሐመድ እድሪስ በበኩላቸው፤ ቤተክርስቲያናቱ የሁለቱ አገራት የትብብር መስኮች እንዲያድጉ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
 
ቤተክርስቲያኒቱ የሚያደርጉት ግንኙነት በአገራቱ መካከል መተማመንን እንደሚፈጥርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን እንደሚያጎለብት የገለጹት አምባሳደሩ፤ ግንኙነቱን ለማሳደግ በሁለቱም አገራት መካከል ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የግብፁ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ያላቸው ግንኙነት ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ ሲሆን፤ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በሁለቱም አገራት በሚደረጉ የሲኖዶስ ምርጫዎች ላይ ድምፅ ይሰጣሉ።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
 
 
Related topics:

No comments:

Post a Comment