Thursday, January 01, 2015

የኢትዮጵያና ግብፅ ግንኙነት ከስጋት ወደ ትብብር

(ታህሳስ, 23/2007, (አዲስ አበባ))-- «ኢትዮጵያና ግብፅ ከአንድ ምንጭ ሲጠጡ እንደመኖራቸው የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሁሉቱም ከአንዱ ጡት ከአባይ ወንዝ የሚጋሩ ልጆች ናቸው፡፡ እናት ልጆቿን አትለይም አንዱን አጥግባ አንዱን አታስርብም» የሚሉት የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ፣ የአባይ ወንዝን በትብብር ፍትሐዊ በሆነ መልኩ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። ይህንንም የግብፅ ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር መግለጻቸውንም ነው የሚያመለክቱት።

ሰሞኑን በግብፅ ጉብኝት አድርጎ የተመለሰው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ከትናንት በስቲያ በብሔራዊ ቤተመንግሥት የጉብኝቱን ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ያነጋገርናቸው ወይዘሮ እንግዳዬ ከልዑካኑ ጋር ተጉዟል።

ወይዘሮ እንግዳዬ የግብፅ ሕዝብ አቀባበልን ያደንቃሉ፡፡ ግብፃውያኑ ከአባይ ወንዝ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ስጋት እንዳለባቸው አስተውለዋል፡፡ በርካታ ግብፃውያን «የአባይን ውሃ ትገደቡብናላ ቸውሁን?» እያሉ እንደጠየቋቸው ወይዘሮ እንግዳዬ ይናገራሉ። «እናንተ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናችሁ፤ አንገድብባችሁም፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማምረት የሚያስችለንን ያህል ብቻ ተጠቅመን ስለምንለቅላችሁ ውሃው ወደናንተ መፍሰሱን አያቆምም» የሚል ምላሽ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በወንዙ ለመጠቀም የወሰነችው ግብፅን ለመጉዳት ብላ ሳይሆን ራሷን ከድህነት ለማላቀቅ ብላ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

በግብፅ ሕዝቡ ዘንድ የተሳሳተ መረጃ መንሰራ ፋቱን የሚጠቅሱት ፕሬዚዳንቷ፣ ግብፃውያን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን አቅም ሳይሆን በእሥራኤልና በአሜሪካ መንግሥት እየተገነባ ነው ብለው እንደሚያስቡም ነው የተናገሩት። በዋናነት በፍትሐዊነትና ተባብሮ መሥራት ላይ የግብፅ ሕዝብ ግንዛቤ እንዲኖረው የማድረግ አስፈላጊነትንም ጠቅሰዋል፡፡ የትብብር መንፈሱን ለማጎልበት ይህ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስመር ትልቁ አማራጭ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ነው ያስገነዘቡት፡፡

አባይን በፍትሐዊነት መጠቀምን አስመልክቶ ከግብፅ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይተዋል። ከግብፅ ነጋዴ ሴቶች ጋር ለመነጋገርም መድረኮችን እንደሚያመቻችቹ ተናግረዋል፡፡

ሌላኛዋ የልዑኩ አባል ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞንም «ኢትዮጵያውያን በአባይ ወንዝ ላይ እንጠቀማለን» ያሉት ከድህነት ለመውጣት ብለው እንጂ ግብፅን ለመጉዳት አስበው እንዳልሆነ ለግብፃውያን ማስረዳታቸውን ይገልጻሉ። ግብፃውያንም ኢትዮጵያውያን ወንዙን ሲጠቀሙ ግብፃውያንን በማይጎዳ መልኩ መሆን እንዳለበት መልዕክታቸውን ማስተላለፋቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ሙሉ ገለጻ፤ በትብብር መሥራት ከተቻለ የሚባክነውን የአባይ ውሃ መጠቀም ይቻላል፡፡ ስግብግብነት ከሌለ ውሃው በቂ ነው፡፡ አገራት ሲዋሀዱና አፍሪካ አንድ ስትሆን አባይ የሁሉም አፍሪካውያን ይሆናል፡፡ ስለዚህ በሁለም ቋንቋ በትብብርና በጋራ የመሥራትና የማደግ መንገድ ላይ አተኩሮ መሥራት ይገባል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ግርማ ሰይፉም ከሕዝብ ዲፕሎማሲ የልዑካን ቡድን ጋር ተጉዘዋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ግብፆች የኢትዮጵያን ብልጽግና እንደማይፈልጉ አድርገው የሚያቀርቡበት መንገድ ተገቢ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ «በእርግጥ ግብፃውያን ስጋት አለባቸው፡፡ ቢሰጉም አያስደንቅም፡፡ የግብፅ መንግሥት የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እስከ መጨረሻው ጥረት ማድረጉ እንደክፋት መታየት የለበትም » ያሉት አቶ ግርማ፣ መገናኛ ብዙሃን ግን መታረም እንዳለበቸው ነው የተናገሩት፡፡ ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲውም ሆነ ገዢው ፓርቲ በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን የግብፅ ሕዝብ ውሃ የማሳጣት ፍላጎት እንደሌላቸው ጠቅሰው፣ የግብፃውያንን ስጋት ለማስወገድ ግንኙነቱ በመተባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መሠራት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡

የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በጉብኝቱ በግብፆች በኩል የኢትዮጵያን ልማት የመደገፍና አብሮ የመልማት ፍላጎት እንዲሁም በጋራ የመጠቀም ሃሳብ እንዳለ ተረድተዋል። በተቃራኒው ደግሞ ፅንፍኛ አስተሳሰቦች እንዳሉም ተገንዝበዋል፡፡

በግብፅ የተደረገው ጉብኝት ጅምር እንደሆነና የግብፅን ሕዝብና መንግሥት አስተሳሰብ የቀየረ ነው ማለት እንደማይቻል ነው ያመለከቱት። የትብብር ሥራውን ለማጠናከርና የተጀመረው ሥራ እንዲሳካ ጥረት መደረጉን አብራርተው፣ ለቀጣይ ሥራ ጥሩ መሠረት መጣሉን አስታውቀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንደሚሉት፤ አዲሱ የግብፅ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻሻል እየታየበት ነው፡፡ የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቱ እየተሻሻለ መጥቷል። ግንኙነቱን ሙሉ ለማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ለማጠናከርም የኢትዮጵያን የተለያየ የህብረተሰብ ክፍል ሊወክሉ ይችላሉ ተብሎ የሚታመንባቸው አካላትን በሙሉ ያካተተ የሕዝብ ዲፕሎማሲ የልዑካን ቡድን በግብፅ ለአራት ቀናት ጉብኝት አድርጓል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ግንኙነት ከግብፅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አገራት ጋር መፈጠር እንዳለበት ዶክተር ቴድሮስ ጠቅሰው፤ ይህም በተቋም ደረጃ መቋቋም እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ ለዚህም ከውጭ ግንኙነት አኳያ ድጋፍ እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ አሁን በተከናወነው ተግባር የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት በመተባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን መሠረት የጣለ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የቀድሞዎቹ የግብፅ መንግሥታት «ግብፅ የበለጠ ተጠቃሚ የምትሆነው ኢትዮጵያ ስትዳከምና ስትቆረቁዝ ነው» የሚል አመለካከት እንደነበራቸው አስታውሰው፣ የግብፅ ሕዝብ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆነው ኢትዮጵያ ከለማችና ከበለጸገች ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

«ኢትዮጵያን ማልማት ማለት በአባይ ውሃ መጠቀም ብቻ ሳይሆን የተራቆተውን ደን መልሶ ማልማትን የያዘ ነው»ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤« አካባቢ ሲለማ ዝናብ ይኖራል፤ የአባይ ወንዝ ፍሰትም ዋስትና ያገኛል፡፡ ኢትዮጵያ ከቆረቆዘች ግን ሰው ከመሞቱ በፊት የቀረችውን እንጨት ያወድማል፡፡ ደን ከወደመ ዛፍ የለም፤ዛፍ ከሌለ የአባይ ወንዝ አይኖርም፡፡ የኢትዮጵያ መቆርቆዝ ለግብፅም ውድቀት ነው» ብለዋል፡፡ ይህን ሁሉ በግብፃውያን ዘንድ ለማስረፅ ጊዜ እንደሚወስድ ነው ያስገነዙቡት። ሠፊ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፍልግም ይናገራሉ። «ግብፃውያን የኢትዮጵያ ብልጽግናን በበጎ ጎኑ እንዲቀበሉት ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ አሁን የጀመረው የትብብር መንፈስም እንዲጎለብት ሁሉም መሥራት አለበት» ብለዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ 

No comments:

Post a Comment