Friday, January 02, 2015

መጪውን ምርጫ ነፃ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ኃላፊነት የሁላችንም ነው

(ታህሳስ, 24/2007, (አዲስ አበባ))--አምስተኛውን ብሄራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ አገራችን ተፍተፍ እያለች ነው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንደገለጸው ዘጠና በመቶ የሚሆነው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። ቀሪው አስር በመቶ ዝግጅትም በቅርብ እንደሚጠናቀቅ ተመልክቷል።

የምርጫው ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ነው። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ነው ቦርዱ እየገለጸ ያለው። በቅድመ ምርጫ ዝግጅት መከናወን ከሚገባቸው ስራዎች መካከል ብቃትና ክህሎት ያላቸው የምርጫ አስፈጻሚዎችን ማዘጋጀት አንዱ ነው። ብቃት ያላቸው አስፈጻሚዎችን ለማዘጋጀት ቦርዱ አስፈጻሚዎችን እያሰለጠነ መሆኑን አይተናል።

ስልጠናው እየተሰጠ ያለው የምርጫ አዋጅና ሌሎች ተያዥ ህጎች ላይ ነው። ይህም የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ስለአገሪቱ የምርጫ ህግ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ያስችላል። አስፈፃሚዎቹ ስልጠና ማግኘታቸው አዋጆቹንና ሌሎች ህጎችን መሰረት አድርገው ሁሉንም ፓርቲዎች ያለአድሎ እንዲያገለግሉ አቅም ይፈጥራል።

እስካሁን ለምርጫ አስፈጻሚዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የአራት ዙር ስልጠና ተስጥቷል። ሰሞኑንም የአራተኛው ዙር ስልጠና በቅርቡ በጅግጅጋና በሐረር ከተማ ተደርጓል። በሐረር ከተማ የተካሄደው ስልጠና ላይ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ የሐረሪና የኦሮሚያ ክልል ምርጫ አስፈፃሚዎች ተሳታፊ ነበሩ።

ስልጠናው ትኩረት ያደረገው የምርጫ የህግ ማዕቀፍ፣ በዕጩዎችና በመራጮች ምዝገባ አፈፃፀም፣ የአስፈጻሚዎች ሥነ ምግባር፣ በቅሬታ አቀራረብና አፈታት፣ የምርጫ ሰነዶች አያያዝና አጠቃቀም እና ሌሎች ከምርጫ ጋር በተያየዙ ጉዳዮች ላይ ነው።

ሰልጣኞቹ ስልጠናው ህጉን መሰረት አድርገው ምርጫውን ለማስፈጸም ግንዛቤያቸውን እንደጨመ ረላቸው አንስተዋል። ስልጠናው ሁሉንም ፓርቲዎች ያለ አድሎ በእኩል ለማገልገል አቅም እንደሚፈጥርም አስረድተዋል። ከዚህም ባለፈ ከቦርድ ጋር ተናቦ እንደ አንድ አካል ሆኖ ምርጫውን ለማካሄድ ያስችላል። መራጩ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ በሆነው የመምረጥ መብቱ እንዲጠቀም ለማድረግ አቅማቸውን እንደገነባ ላቸውም አመልክተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፊኛንቢራ ምርጫ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት ወይዘሮ መይሙና መሐመድ ስልጠናውን ከወሰዱት መካከል አንዷ ናቸው። በ1987 ዓ.ም በተካሄደው የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ ምርጫ፣ በምርጫ አስፈጻሚነት ተሳታፊ ነበሩ። በሁለተኛው ዙር ምርጫ በክልል ደረጃ ብቸኛዋ ሴት የምርጫ አስፈጻሚ ሆነዋል። በሦስተኛውና በአራተኛው ዙር ምርጫዎች ከጥቂት የክልል ሴት የምርጫ አሰ\ፈጻሚዎች አንዷ እንደነበሩ ይጠቁማሉ። ዘንድሮ ለሚካሄደው ምርጫ ሴቶች ከወንዶች እኩል የምርጫ አስፈጻሚ ሆነው ማያታቸው እንዳስገረማቸውም ይናገራሉ።

የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እየተሻሻለ መምጣቱን ያነሳሉ። በምርጫ ሂደቱ እየተሻሻለ የመጣው የሴቶች የአስመራጭነት ሚና እያደገ መምጣቱንም በምሳሌነት ያነሳሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ምርጫው «ነጻና ፍትሃዊ» እየሆነና እየተሻሻለ መጥቷልም ይላሉ። ሴቶች በምርጫ በነጻነት የመሳተፍ ሂደታቸው እየተሻሻለና እየጨመረ መምጣቱን መታዘባቸውን ሃላፊዋ ይናገራሉ።

የዘንድሮውን ምርጫ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ለማስፈጸም ስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ እንደጨመ ረላቸው ገልፀው፣ በስልጠናው ያገኙትን እውቅት በመጠቀም ህጉን ለማስፈጸም አቅም እንደፈጠረ ላቸው አንስተዋል። «ሁሉም ፓርቲዎች በህጉ መሰረት መንቀሳቀስና የሚሰጠውን አገልግሎት በተገቢው ሁኔታ መጠቀም አለባቸው። እኛ ሁሉንም በህጉ መሰረት ለማስፈጸም ዝግጁ ነን» ሲሉም ነበር ዝግጁነታቸውን የገለጹት። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስና የህዝቡን ውሳኔ አክብረው መንቀሳቀስ እንዳለ ባቸውም ያነሳሉ።

የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱን በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሲያካሂዱ እንደነበር ያነሱት ደግሞ የሐረሪ ክልል ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልሐኪም አብዱራህማን ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት የምርጫው ቅድመ ዝግጅት በክልላቸው በበቂ ሁኔታ እየተከናወነ ነው። የምርጫ እስፈፃ ሚዎችን መልምለዋል፤ አስፈጻሚዎቹም በክህሎትና በእውቀት ዝግጁ እንዲሆኑ ስልጠና እየተሰጠ ነው። የምርጫ ቁሳቁሱ በክልሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ደርሷል። እያንዳንዱ ስራ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል። ይህንኑ ጨምሮ በቀጣይ የሚከናወኑ የህዝብ ታዛቢዎችን ለማስመረጥና ስልጠና ለመስጠት ተዘጋጅተናልም ነው ያሉት።

በቆይታችን እንዳስተዋልነው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍትሃዊነት ለመስጠት ሰልጣኞቹ ተዘጋጅተዋል። ህብረተሰቡ ስለ ምርጫው ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ራሳቸውን የማብቃት እንቅሰቃሴዎችን እያደረጉም ነው። በምርጫ ቦርድ ለአስፈፃሚዎች እየተሰጡ ያሉት ስልጠናዎች የጀመሯቸውን ስራዎች ህግና ህግን መሰረት አድርገው ለማስፈጸም እንደሚያስ ችላቸውም ይናገራሉ።

በቦርዱ የተቀመጠውን እቅድ በተገቢው ለመፈፀም ተንቀሳቅሰናል የሚሉት የሐረሪ ክልል ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልሐኪም፣ አምስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ነጻ፣ ፍትህዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ሃላፊነቱን መወጣት አለበት ይላሉ። ቦርዱ ሁሉንም ፓርቲዎች በገለልተኛነት እንደሚያገለግል አምነው ህገ መንግስቱን፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን መሰረት አድርገን በገለልተኝነት መንቀሳቀስ አለብን ብለዋል። ቅሬታ የሚፈጥር ጉዳይ ቢያጋጥም በተቀመጠው የህግ አግባብ ቅሬታን መፍታት ይገባናል በማለትም አስረድተዋል። ህብረተሰቡም ይህንኑ በማገዝ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባው ያመለክታሉ።

የድሬዳዋ ምርጫ ቦርድ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ጊኒ ረሺድም ይህንኑ ይጋራሉ፤ እሳቸውም እንደሌሎቹ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች በድሬዳዋም በተመሳሳይ የዝግጅት ስራዎች መፈፀማቸውን ይናገራሉ። የቅድመ ምርጫ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ።

«የምርጫ ቁሳቁስ ተረክበናል፤ ለከፍተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎች ስልጠናዎች በተዋረድ እየተሰጡ ነው። እስካሁን መሰራት ያለባቸው የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም ተከናውነዋል» ብለዋል።

በቀጣይም የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማውረድ፣ የህዝብ ታዛቢዎችን የማስመረጥና ሌሎች ስራዎች ለማከናወን እየተዘጋጁ እንደሆነ የገለፁት ሃላፊዋ ሁሉንም ስራዎች ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የነገሩን።

ምርጫውን ለማስፈጸም በቂ የምርጫ አስፈጻሚዎች አሉን ያሉት ኃላፊዋ፣ ከመጀመሪያው የምርጫ ጊዜ ጀምሮ የተሳተፉ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ከአዲሶቹ ጋር በማጣመርና በቂ ስልጠና በመስጠት በከተማዋ ደረጃውን የጠበቀ ምርጫ ለማካሄድ መዘጋጀታቸው ነው ያመለከቱት።

«ቦርዱ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልና በህጉ መሰረት ያገለግላል፤ ለዚያም ተዘጋጅተናል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሚመሩበትን የሥነ ምግባር ደንብ አክብረው መራጩን ህዝብ በአግባቡ ለማገልገል መንቀሳቀስ አለባቸው። ችግሮች ካጋጠሙም በተቀመጠው የቅሬታ አፈታት ደንብ መሰረት በሰለጠነ መንገድ በመፍታት ለአገራቸው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መስራት አለባቸው» ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አባል አቶ ፍቅረማርያም በረደድ በ2007 ዓ.ም ለአምስተኛ ጊዜ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ ምርጫ ቦርዱ ዝግጅቱን በተጠናከረ ሁኔታ እያካሄደ መሆኑን አውስተዋል። ለምርጫ አስፈፃሚዎች እየሰጠ ያለው ስልጠና ምርጫው ከስህተት በጸዳ ሁኔታ ለማካሄድ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

ቦርዱ ከማንም ሳይወግን በገልለተኛነት ምርጫ እንዲያከናውን በህገ መንግስቱና በአዋጅ ሃላፊነት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት አራት የምርጫ ሂደቶች ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣቱን አመልክተዋል። የዘንድሮው ብሔራዊና የክልል ምርጫም ከባለፉት ምርጫዎች በተሻለ እንዲከናወን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ልምዶች መቀመራቸውን፣ ከባለፉት ምርጫዎችም ልምድ መወሰዱን አስረድተዋል። ከዚሁ ልምድ በመነሳትም አስፈፃሚዎች የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ስልጠና እንዲሰጥ መደረጉን ጠቁመዋል።

ሰልጣኞች የተሰጣቸውን ስልጠና እንደ አቅም ተጠቅመው አዋጆቹንና መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል። ለዚህም ክፍተቶችን በሥልጠና እየሞሉና እየተማማሩ መሄድ ይገባል ነው ያሉት። በምርጫ ሂደቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ህጉን መሰረት አድርገው እየተነጋገሩና እየተወያዩ የተቃና ምርጫ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

አገር የምታድገው ህዝቡ በመረጠው መንግስት ሲተዳደርና ህዝብ የመረጠው መንግስት ሲመሰረት ነው ያሉት አቶ ፍቅረማርያም ይህ እንዲሆን የሁሉም ተሳትፎ አስፈላጊ ነው፤ ቦርዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሰራሩን በማሻሻል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ዝግጁ ነው፤ ሆኖም የቦርዱ ጥረት ስኬታማ የሚሆነው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በንቃት ሲሳተፍ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። በምርጫው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች በተቀመጠው የችግር መፍቻ መንገድ ይስተናገዳሉ፤ ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድም ተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መትጋትና ዝግጁ መሆን እንደሚኖርበት አስረድተዋል።
ምንጭ: ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment