Tuesday, March 11, 2014

የግብፅ መንግሥት ስጋት የወለደው እርምጃ

(Mar 11, 2014, (አዲስ አበባ))--መነሻው ሀገር የሚያስደንሰው ብሄራዊ መዝሙራችንን (የህዳሴ ግድብ) መሠረት በማድረግ የግብፅ የሽግግር መንግሥት አርቅቆ ለህዝበ ውሣኔ ያቀረበው ህገ መንግሥት አንቀፅ 44 ነው፡፡ «The state (of Egypt) commits protecting the Nile river maintain and minimizing its benefits net westing its water or polluting» ይላል በአንቀፁ የሰፈረው ነጥብ፡፡ ስለሆነም የግብፅ መንግሥት በታሪክ ስናውቃቸውና ዓባይን በተመለከተ ሲናገሩ የምናዳምጠውን «ታሪካዊ እና ተፈጥሮአዊ መብት» እንዲሁም የአላህ ስጦታነት አዲሱ የሽግግር መንግሥት በህገ መንግሥቱ ላይ ከማስፈሩ የተለየ አዲስ ነገር የለውም፡፡

ዋናውና የቀለም አብዮቱ አራጋቢዎች መነሻ የአንድ ሀገር ህገ መንግሥት የዜጎች ሁሉ የበላይ ከመሆኑ ጋር በማያያዝ ሥጋት መንዛትና ከፍ ሲልም እንደሰቆቃው ፍርሀት ተራኪ በቦንድ የተዋጣው ገንዘብ ውኃ እንደበላው እንዲቆጠርና የህዝቡን ተነሳሽነት በመገደብ ልማቱን ማደናቀፍ ነው፡፡

ዳሩ ግን በተለይም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አምነውበት የፈረሙበትን ጥቅል የሥምምነት ሰነድ (Comphrensive frem work agreement) መነሻ በማድረግ ግብፅ የነበረችበት፣ የምትኖርበትና ልትኖርበት ያቀደችው መንገድ እንደማያዋጣ በመግለፅ ለማግባባት በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ግብፅ በአዲሱ ህገ መንግሥቷ አንቀፅ 44 ላይ የከተበችውን ጉዳይ በተመለከተ በተደጋጋሚ እንደማውራቷ ሚዲያዎቿም ሆኑ ህዝቦቿ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዚሁ አካል ሆነው በአንድነት እየጮሁ መገኘታቸው እውነት ነው፡፡ ግብፅ በአሁኑ ወቅት በመንታ መንገድ ላይ ያለችና በሁለት እግሯ መቆም የተሳናት ሀገር ሆናም ሳለ በዓባይ ውኃ ላይ ምንም እንኳን ነጥቡ መርህ አልባም ቢሆን በአንድነት እየዘመረች ነው፡፡

እንደሚታወቀው በውኃ ላይ የሚነሳ ንትርክ በዓለም አቀፍ ተሞክሮም በተረጋገጠው አግባብ ፍጭቱ ቴክኒካዊ ቢመስልም (ግብፅ ውኃዬን ይቀንሳል፣ ድርሻዬን ያጎድላል፣ ተደርምሶ ያጠፋኛል እንደምትለው) ከዚህም በላይ የሆነው መነሻ ፖለቲካዊ ነው፡፡

የውኃ ፖለቲካ ተንታኞች እንዳሰመሩበት ከሆነም ግብፅ የምታነሳቸው ቴክኒክ ነክ ጥያቄዎች ማስመሰያ እንጂ ከምታነሳቸው አጀንዳዎች አንፃር ታላቁ የህዳሴ ግድብ ቢጠቅማት እንጂ አይጎዳትም፡፡ ይልቁንም በአፍሪካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ከፊት መስመር ተሰልፋ መገኘት ያሰጋታል፡፡ በዚሁ ላይ የልማቱ አቀጣጣይና የህዝቦቿ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነው ይህ ግድብ ተገነባ ማለት ግብፅ ካለችበት የፖለቲካና ዐረባዊ ፍልስፍና አንፃር የቁም ሞቷ እንደሆነ ታስባለች፡፡ ከንቱ ሥጋት!

አስተሳሰቡ ያረጀና ያፈጀ እንደሆነ ይልቁንም የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተና ማንም አሸናፊ ማንም ተሸናፊ የማይሆንበት መሆኑን አምናና ተቀብላ ወደ ትብብሩ ዓለም እንድትመጣ በተፋሰሱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት ላይ ተመክራለችም፤ ተዘክራለችም፡፡ በቴክኒኩ ረገድም ቢሆን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ለሦስት ጊዜ ባደረጉት የውኃ ሀብት ሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ከልመና ባልተናነሰ መልኩ ተጨባጩ እውነት ተነግሯታል፡፡ በተለይም ይህ መድረክ ሀገራቱ አምነውና ፈቅደው ያቋቋሙት ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን አጥንቶ ይፋ ያደረገው ሰነድ የግብፅን ሥጋት ሁሉ ያሟጠጠ እንደሆነ ወረቀት ተገልጦ ተበትኖላታል፡፡

ሆኖም ግን አውቆ የተኛ እንዲሉ ጉዳይዋ ቴክኒካዊ ሳይሆን ፖለቲካ በመሆኑ እምቢተኛነቷን ገፍታበታለች፡፡ ለእምቢተኝነቷ ደግሞ ሌላ ምክንያትም አቅርባለች፡፡ ምክንያቷም ውኃ የማያነሳና ፈቅዳ የራሷንም አካታ ያቋቋመችውን የባለሙያዎች ቡድን የጥናት ውጤት «አላመንኩ በትም» የሚል የቂል ምክንያት ነው፡፡ ቂልነቷ ወደ መጃጃልም ሄዶ ከዜሮ እንድንጀምር የሚጠይቅ ነው፡፡ ድርድር በየጊዜው እየተወያዩ፣ ከውይይቱ የተገኙ ሀሳቦችንም እያሰባሰቡና በየሀገራቱ መንግሥታት በግል እየመከሩ የሚቀጥልና ውጤቱም በሀገራት የሚታወቅ ከመሆኑ አንፃር ከግብፅ ጋር ያለው ውይይት አበቃለት ማለት ባይቻልም ከእነዚህ መድረኮች መነሻነትና ከአንቀፅ 44 ጥቅል ይዘት አንፃር አቋማችንና አቋማቸው ግልፅ የወጣና የለየለት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

በዚህ ግምት መሠረት ውጤቱ በኋላ የሚታወቅና ቁርጥ ያለ ነገር አሁን ላይ መናገር ባይቻልም የኢትዮጵያ አቋም ግን ፍትሃዊ፣ ለጋራ ልማትና ብልፅግና ያደላ፣ በዘመኑ መርህ የተቃኘና በማንኛውም መስፈርት አሸናፊ እንደሚሆን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህም ስለሆነ ለዘመናት ስለዓባይ በግብፅ አፍ የሚወራውና ስለዓባይ በግብፅ ወገብ ስትደንስ የነበረችው ሱዳንና ህዝቧ የቀፈደዳት የግብፅ መደለያ፣ ወጥሮ የያዛት ዐረባዊ ፖለቲካ፣ ምሣና ራቷ እንዳልሆናትና ይልቁንም ለህዝቦቿ ዘላቂ ልማትና ሠላም አዋጩ ጎዳና ዓባይን ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ሁሉ በጋራ ማልማት መሆኑን በመገንዘብ ሀሳቧን ለውጣለች፡፡

ይህ ለውጥ እዚያው ሳለ ለሱዳን መጥቀሙ እንደተጠበቀ ሀኖ የኢትዮጵያን አቋምና ፍላጎት ትክክለኛነት በተመለከተ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያስተላልፈውም ታላቅ ቁም ነገር ማዘሉን «ሥጋት ገባን፣ ገንዘባችንን ውኃ በላው» ብለው የሚያቃልጡ አብዮት ናፋቂዎች ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ስለሆነም በግብፅ ዘንድ ታሪካዊ መብቴ የሚለው የአባይ ጂኒ ቁልቋል ስር የሰደደና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ከመሆኑ አንፃር በህገ-መንግስታቸው ላይ መፃፉና አለመፃፉ የግብፅን ገዢዎች የስልጣን ዕድሜ ከማራዘምና ካለማራዘም የዘለለ ፋይዳ በኢትዮጵያ በኩል የለውም፡፡

የሚጠበቅብን ኢትዮጵያዊያን መቼም ቢሆን ኅብረታችንንና አንድነታችንን አጠንክረን ልዩነት ቢኖረንም በሰከነና በሠለጠነ መንገድ እያራመድን የጋራ ቤታችንን መገንባት ብቻ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው።

ሌላው በግብፅ በኩል እየተለቀቀ ያለው ነጠላ ዜማ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንወስደዋለን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ህዝብ አያውቅም ብለው ይህንኑ የግብፅን ነጠላ ዜማ በማቀንቀን በማደናገር ሂደት ላይ ቢገኙም ህዝቡ ውኃውን የተመለከተ ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ ህግ እንደሌለና ውኃውን የሚዳኝ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሌለ መሆኑን በ«ሰቆቃወ ፍርሃት» ደራሲው «የግድብ ወዳጆች» የተባላችሁት ሁሉ መረጃ ልትሰጡ ይገባል፡፡ መንግሥትም የግድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ እንዲሆኑ ሳይጠበቅ ለዚህ ሥራ ሲባል የተቋቋሙ ተቋማትና ኃላፊዎቻቸው ተከታትለው የሆነ ማብራረያና መረጃ ለህዝቡ ሊሰጡት ይገባል፡፡

ከዚህ በዘለለ ግብፅ ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን ወደሚወክሉ ተቋማት ብትወስደው አጀንዳው የፖለቲካ ስለሚሆንና ፖለቲካዊ ምላሹም የኛውና የ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የሆነው በጋራ መልማትና በጋራ መጠቀም የሚለው ስለሚሆን ሥጋት ሊገባን አይገባም፡፡ 
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment