Tuesday, February 11, 2014

«ቤቶች ድራማ » ከእውኑ ዓለም እየራቀብን ነው! ሰለቸን መሠለኝ

(Feb 11, 2014, (አዲስ አበባ))--ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አዘጋጆች በኢቲቪ የሚተላለፍ ድራማን በተመለከተ አስተያየት ብልክ አታስተናግዱትም ብዬ አልጠራጠርም፡፡ በእርግጥ «ቤቶች ድራማን» በተመለከተ ለድርጅቱ ለመዝናኛ ክፍል ስልክ ደውዬ ቅሬታዬንና መስተካከል ያለበትን የግል ዕይታዬን ሣልጠቁም አልቀረሁም፡፡

ለመሆኑ ኪነ-ጥበብ ፋይዳዋ ምንድን ነው? ማሳቅ፣ አሰልችቶ ማሳቅ ብቻ ወይስ የተለመደ አሰልቺ ምክር ለመስጠት? ወይስ ምን ይሆን? በእርግጥ ሁሉንም የሥነ-ጽሁፍና የኪነጥበብ ስራን በአንድ አዝናኝ፣ አስተማሪ፣ መረጃ ሰጪ... ብሎ ለመፈረጅ አይቻልም፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ኮሜዲ፣ ትራጀዲ ፣ .... እያሉ አይደል በተለያየ ዘውግ የሚመደቡት፣

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ ከመጣው የስክሪን ፊልም ጋር በተያያዘ የቴሌቪዥን ድራማዎችም እየበዙ ነው፡፡ እነዚህ ድራማዎች ደግሞ ከየትኛውም የኪነ-ጥበብ ሥራ በላይ ለህዝቡ ተደራሽነት ስላላቸውና አዲሱን ትውልድ ለመቅረጽም ስለሚረዱ ጥንቃቄና ብስለት ሣይፈልጉ አይቀሩም። ቅዳሜ ምሽትና ማክሰኞ ማለዳ በኢቲቪ የሚተላለፈው ቤቶች ድራማም አንዱ አዝናኝ የኪነ-ጥበብ ሥራ ሲሆን በአብዛኛው ወደ ቤት (ጓዳ) ድራማ (Home VADIO) የሚያደላ የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ በዚህ ረገድ በአዘጋጁና ተዋናዩ ረገድ ጫና ሳይፈጥር የሚሠራ የሳሎን ትዕይንት መሆኑም አይዘነጋም።

ነገር ግን ይሄ ድራማ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከነባራዊው ዓለም እየራቀ፣ ከአስተማሪነት ይልቅ አሰልቺ ዋዛ ፈዛዛ እየሞላው ነው፡፡ ማን ይሙት በየትኛው ቤት ነው እንደ «እከ» ያለ ዘበኛ ያለው? የፈለገውን እየተናገረ፣ ባለቤቶቹን ቁጭ ብሎ እያናገረ እየዘለፈ . . . እውነት ልጆቹስ በእንዲህ አይነት ግብረገብነት ከቤተሰብ ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ መጋጨት መነጋገር፣ ማንጓጠጥ ያደጉት በኢትዮጵያዊ ባህል ነው? ወይስ? አሁን አሁን እንደአሸን እየፈላ ባለው « ስልጡን» ኢትዮጵያዊነት

የነ ትርፌስ ጉዳይ የቤት ሰራተኛና ዘመድ አፍሮ ተከብሮና በልኩ ሆኖ መኖር እንጂ እንደፈለገ የሚፈነጥዝበት ሥርዓት በየትኛው ትውልድ ታይቷል ? የአንዱ ሳምንት ትዕይንት ከሌላው ጋር ባይተሳሰርም፣ በየጊዜው የሚነሳው ጭብጥ ግን ፋይዳው እየኮሰሰ መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ በጥቂት ደቂቃ ቪዲዮ (ስፖት) ልንመለከተው የሚገባንን አጭር አስቂኝ ክስተት እያንዘላዘሉ 30 ደቂቃ ማሰልቸትስ ጥበባዊ ዋጋ (art vslue) አለው ያስብላል፡፡

እባካችሁ የምናከብራችሁ አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች የህዝብን አኗኗርና ነባራዊ እውነታ ዕወቁ ማንነትን የሚመጥን ጥበብም አቅርቡልን ተመልካቾቻችሁ ደግሞ በአዲስ አበባ በቅንጦት በጥበቃ የሚኖረው ጥቂት ሀብታም ብቻ ሳይሆን በአስር ሚሊዮን የሚቆጠር ድሃና መካከለኛ ገቢ ያለው ከተሜና የገጠር ህዝብ ጭምር መሆኑን መርምሩ ዘመኑን የቧልትና የሹፈት አታድርጉት፡፡
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
አልአዛር ጌቱ , ( ከአ.አ.ዩ)

No comments:

Post a Comment