Tuesday, February 11, 2014

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ «... የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው»

(Feb 11, (አዲስ አበባ))--የኢፌዴሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካደረጓቸው ወርቃማና ታሪካዊ ንግግሮች መካከል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥና ሕዝቡ ለፕሮጀክቱ ሙሉ ድጋፉን ሊያረጋግጥ አደባባይ በወጣበት ወቅት ያሰሙት ይጠቀሳሉ። በንግግራቸው ደጋግመው የገለጹትም ይህ ከፍተኛ ፕሮጀክትና ከሀገር አልፎ ለጎረቤት ሀገሮችም የሚተርፈው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጠንካራ ርብርብ የሚገነባ መሆኑን ነበር።

ይህንንም «... የታላቁ የህዳሴ ግድብ መሐንዲሶችና ቀያሾች እኛው፣ግንበኞች እኛው፣ የፋይናንስ ምንጮች እኛው፣ አስተባባሪዎችና አስፈጻሚዎች እኛው በመሆናችን በአባይ ወንዝ የመጠቀም የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታችን ነው» በማለት በአጽንኦት ገልጸውታል። ይህ አባባል የግብፅ የቀድሞ መሪዎች ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ፕሮጀክት ቀርጻ ድጋፍ እንዳታገኝ ሲጥሩ የኖሩበትን መንገድ ያመከነ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ለዘመናት በአቅም ማነስና በአመራር ብስለት እጦት ለመፈጸም ሳይችሉ የኖሩትን ታላቅ ስራ በድፍረት ተነሳስተው እንዲጀምሩና በአንድ ድምጽ እንዲቆሙ ማድረግ ችሏል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ሦስተኛ ዓመቱ እየተቃረበ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ መላው ሕዝብ በቦንድ ግዥና በስጦታ መልክ ከአምስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ አውጥቷል። መንግሥትም ለፕሮጀክቱ ሙሉ ትኩረቱን በመስጠቱ ግንባታው ለአንድም ደቂቃ ሳይቋረጥ እስከአሁን በስፋት የግንባታ ግብዓት አስገብቶ፣ የመሠረት ዋነኛ ግንባታና ውስብስቡን የዝግጅት ሥራ ጨምሮ 30 በመቶ የተከናወነ ሲሆን፤ በዓመቱ መጨረሻ 36 በመቶ ይደርሳል።

ከዚሁ ተግባር ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡ በተለይ ለጎረቤት ሀገሮችና ለታችኛው የተፋሰሱ ሀገሮች ያለውን ፋይዳ ከማስረዳት አልተቆጠበም። ምንም እንኳ በግብፅ በኩል ለዘመናት ሲቀርብ የኖረው « የታሪካዊና የተፈጥሯዊ መብት ጥያቄ» ከፍትሐዊ የውሃ ሀብት ክፍፍልና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ዓለም አቀፍ ስምምነት የራቀ መከራከሪያ እስከአሁን ቢደመጥም ሁሉም ወገኖች እውነቱን እንዲገነዘቡ እየተደረገ ነው በተለያዩ ውይይቶች፣ የጋራ የቴክኒክ ቡድን አቋቁሞ በማስጠናትና በሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ጭምር ጥረት ተደርጓል።

በግብፅ በኩል አሁንም ቢሆን የተያዙት የተምታቱ አቋሞችና «ኢትዮጵያ ለግድቡ ምንም ዓይነት ድጋፍ አታገኝም» የሚለው ሙግትም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ለዚህ ዓይነቱ አደናቃፊ አስተሳሰብ መመከቻ የሚሆነው ስንቅ ደግሞ መላው ሕዝብና መንግሥት ሙሉ ወጪውን በጋራ ጥረት ለመሸፈን ታጥቀው መነሳታቸው ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛዲግ አብርሃ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ግድቡን ለመገንባት የገንዘብ ምንጭ የሚሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ብቻ ናቸው። ስለሆነም ግብጽ የምታስተጓጉለው ምንም ዓይነት ብድርና ዕርዳታ አይኖርም። ገንዘብ እንዳናገኝ የማድረግ አቅምም የላትም።ግብፅ በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ገንዘብ ላይ የማዘዝ መብትም ችሎታም የላትም ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ኃላፊው የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡ በየትኛውም የተፋሰሱ አገራት ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ እንዳያደርስ አስጠንቶ እያስገነባ ከመሆኑም በተጨማሪ አንዳችም የውሃ መጠን በሚቀንስ መልኩ የሚሠራ እንዳልሆነ አረጋግጧል። ምንም ዓይነት የአካባቢ ተጽዕኖም አያሳድርም። ይህንን ባለሙያዎችም አረጋግጠዋል። ይህ ሁሉ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ የግብፅ መንግሥት መከራከሪያና ያልተገባ እንቅስቃሴ የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን ነው ያረጋገጡት። መፍትሔው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም፣ ለጋራ ተጠቃሚነትና ለእኩልነት የያዘውን በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም ማጠናከርና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ነው፡፡

ግብፃውያን ወገኖችም ይሄን ሐቅ ተገንዝበው ከአንዳንድ ፖለቲከኞቻቸውና ምሁራን ማደናገሪያ ወጥተው እውነትን ሊፈልጉ ይገባል። በድርድርና ውይይት ስም የሚነሱ ውሃ የማይቋጥሩና ተቀባይነት የሌላቸው ሃሳቦች ከማንሸራሸር ይልቅ ለትክክለኛና ዓለም ዕውቅና ለሰጠው ስምምነት ራስን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል። አንዳንድ የግብፅ መገናኛ ብዙኃንም ቢሆኑ ከኖረው አስተሳሰብ ወጥተው የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብን ቁርጠኝነትና የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎት መመርመር አለባቸው።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ለፕሮጀክቱ ሙሉ ቁርጠኝነት እንዳላቸው ማረጋገጥ የሚቻለው ብድርና ድጋፍ የሚሰጥ ወገን ቢኖር እንኳን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የሚገነባው በመንግሥትና በሕዝብ ጥረት ብቻ ነው። በግድቡ ዙሪያ ድጋፍ አልጠየቅንም። ቢገኝም አንቀበልም። ምክንያቱም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳሉት ግድቡ ኢትዮጵያውያን እንደ ሕዝብ ከድህነት ለመውጣት ቆርጠን መነሳታችንን የሚያመለክት የረጅም ጊዜ የህዳሴ ጉዞ ማሳያ ፕሮጀክት ነውና።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment