Sunday, January 26, 2014

የግብፅ «እኔ ብቻ በልቼው ልሙት» ነጠላ ዜማ

(Jan 26, 2014, (አዲስ አበባ))--የግብፅ አቋም ዛሬም ግራ ከማጋባት የተፋታ አልሆነም። የጠራ አቋም መያዝ ተስኗት እዚህና እዚያ እየረገጠች ነው። ዛሬ ላይም የግብፅ ባለሥልጣናት ከሚጠቅመው ጎዳና ይልቅ የማይበጀውን መከተሉን የመረጡ ይመስላል። በድርድር መድረክ ተወያይቶና ተመካክሮ መፍትሄ ከማበጀት ይልቅ ተቀባይነትና አሳማኝ ያልሆነ ሀሳብ እያቀረቡ ከሠላማዊ መስመር መውጣትን መርጠዋል።ተፈጥሮአዊ ሀብትን በፍትሃዊነት የመጠቀም አካሄድን ማጣጣም እንደ እሬት መራራ አድርገውታል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ጊዜ ያለፈባቸውን የቅኝ ግዛት ውሎች እየመዘዙ «አድምጡን» ይላሉ።

እነዚህ ባለሥልጣናት እውነታውን መቀበል ተስኗቸው እርስ በርሱ የሚጣረስ አስተያየት ሲሰነዝሩ ይደመጣል። የግብፁ አስዋት ማስሪያ የተሰኘው ድር ገፅ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ናቢል ፋሚ ግብፅ የአባይ ወንዝ ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ የትብብር መንገድ የመጓዝ ፍላጎት እንዳላት መግለፃቸውን ዘግቧል። ሚኒስትሩ ታዲያ በሃሳባቸው መፅናት አልቻሉም። በፍትሃዊነት መጠቀም ተገቢ መሆኑን በተናገሩበት አንደበት « በማንኛውም አገር የማይደፈሩ ታሪካዊና ህጋዊ መብቶች አሉ» በማለት የቀድሞዎቹ ስምምነቶች መነካት እንደሌለባቸው ለመጠቆም ይሞክራሉ። «የግብፅ የውሃ ደህንነት ከብሔራዊ ደህንነት ተለይቶ የሚታይ ጉዳይ አይደለም»ሲሉም ያክላሉ።

ባለሥልጣናቱ «እኛ ብቻ እንብላ...» የሚለውን ደካማ አስተሳሰብ በተደጋጋሚ ያንፀባርቃሉ።በኃይል ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የተገደዱት የግብፁ ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ሙርሲ እኛ ብቻ መጠቀም አለብን የሚለውን ተቀባይነት የሌለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡ «አንዲት የውሃ ጠብታ እንድትነካብን አንፈልግም» እስከ ማለትም ደርሰዋል፡፡ለዚህ ደግሞ እኤአ የ1929 እና 1959 ውሎችን ያጣቅሳሉ፡፡እነዚህ የቅኝ ግዛት ውሎች ደግሞ የተፋሰሱን አገራት ያላሳተፉና ከተጠቃሚነት ያራቁዋቸው ናቸው፡፡ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ካላቆመች የኃይል እርምጃን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን እንደሚጠቀሙ ሲዝቱ ነበር። የኃይል እርምጃው ግን ወደ እሳቸው ዞሮ ከዙፋናቸው ወረወራቸው።

የግብፅ መገናኛ ብዙኃን ይዘው እየወጡ ያለው መረጃ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት የግብፅ ባለስልጣናትም ከቀደሞቹ የተሻለ አስተሳሰብና አመለካከት አለመያዛቸውን የሚያሳዩ ናቸው። ባለስልጣናቱ ዛሬም ከስህተት ጎዳና ለመውጣት ተቸግረው ይታያሉ። በተለይም የግብፅ የውሃ ሀብትና የመስኖ የሚኒስትር ሚስተር መሀመድ አብደል ሞትለብ አስተያየት ግራ የሚያጋባ ነው።ሚኒስትሩ ግብፅ ለራሷ ብቻ እንዲመቻት አድርጋ ያፀደቀችው የቅኝ ግዛት ውል መነካት እንደሌለበት በተደጋጋሚ ይሞግታሉ።

ሰውዬው እአአ የ1959 ውልን በማጣቀስ እንዲህ ይላሉ «... ግብፅ 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ድርሻ እንዲኖራት ስምምነት ላይ ሲደረስ (ከሱዳን ጋር የተደረሰውን ስምምነት ለማለት እንደሆነ ልብ ይሏል) የግብፅ ህዝብ 25 ሚሊዮን ነበር። አሁን የግብፅ ህዝብ 85 ሚሊዮን ደርሷል። ስለዚህ 80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያስፈልገናል...» ይህ አስተያየት እንግዲህ የግብፅ ባለስልጣናት ከራሳቸው ውጭ ለሌሎቹ የተፋሰሱ አገራት ምንም ደንታ እንደሌላቸው ያሳያል።

ሚኒስትሩ የሁሉንም አገራት ወንዙን በፍትሃዊነት የመጠቀምን መብት ደፍጥጠዋል። ከዚህም በላይ ደግሞ የግብፅ ህዝብ ሲጨምር የሌላው አገር ህዝብ መጨመሩን መቀበል ተስኖዋቸዋል።እነሱ የግብፅ ህዝብ በመጨመሩ ተጨማሪ ውሃ እንደሚያስፈ ልጋቸው እየተናገሩ የሌሎቹ አገራት ህዝብ ቁጥር መጨመር ግን ደንታ አይሰጣቸውም።የግብፅ ፍላጎት እስከተሟላ ድረስ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገራት ተጠቃሚ ሆኑ፤ አልሆኑ አያስጨንቃቸውም።ለዚህም ነው ከ «እኔ ብቻ በልቼ ልሙት» አባዜ አልተላቀቁም ማለት የሚቻለው።

የግድቡ ግንባታ በየትኛውም የተፋሰሱ አገር ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢትዮጵያ ስትገልፅ መቆየቷ ይታወሳል። የግድቡ ግንባታ የተፋሰሱን ሀገራት እንደማይጎዳ ተገቢው ጥናት ተደርጎና ታምኖበት ነው ወደ ተግባር የተገባው፡፡ይህ እውነታ ደግሞ በዓለም ዓቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ተረጋግጧል፡፡ዓለም ዓቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ለአንድ ዓመት ያህል ከግድቡ ጋር በተያያዘ ተገቢውን ጥናት ሲያካሂድ ቆይቶ የመጨረሻውን የጥናት ሪፖረት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡በዚህም ግድቡ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለው ማረጋገጡን ቡድኑ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ አሳውቋል፡፡የግድቡ ዲዛይን ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ከመሆኑም በላይ በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተፅዕኖ አለመኖሩ በጥናት ግኝቱ ዳግመኛ ተረጋግጧል፡፡

የጥናቱ ሪፖርት ኢትዮጵያ ስለ ግድቡ ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ስትገልፀው የነበረው መረጃ ትክክልና በጥናት የተረጋገጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡በተፋሰሱ አገራት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ የማያስከትል፤ በአንፃሩ ልማትን የሚያፋጥን ሰነድ ሆኗል፡፡ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማመንጨት የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት የጀመረችው ጤናማ አካሄድ አንዱ አካል ለመሆኑም ምስክርነት ሰጥቷል፡፡የዓለም ሃገራት ትልቅ ስጋት እየሆነ የመጣው የከባቢ አየር ብክለትን ለመዋጋት አገሪቷ እየሄደችበት ያለውን የአረንጓዴ ልማት ጥረትንም ያሳያል፡፡

የሶስቱ አገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ድርድሮችን ሲያካሂዱ መቆየታቸው አይዘነጋም። ሚኒስትሮቹ ዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህም ዓለም ዓቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረበውን ጥናት ተግባራዊነት የሚከታተል ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲቋቋም መግባባት ላይ ተደርሷል።

ኮሚቴው በባለሙያዎቹ የቀረበውን ጥናት ተግባራዊ ለማድረግ የውጭ አማካሪ ቅጥር በመፈፀም አማካሪው የሚያቀርበውን ሐሳብ ገምግሞ የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት። ይህ ሂደት የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም ግብፅ የቀድሞ ሃሳቧን በውይይት መድረኩ በማንፀባረቅ ሂደቱን አደብዝዛ ዋለች።

በመሆኑም ቀደም ሲል ከናይል ተፋሰስ አገራት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ በየአገራቱ ፓርላማ ፀድቆ ህግ ሆኖ እንዲሰራ አገራቱ የተስማሙበትን የትብብር ማዕቀፍ በድጋሜ ለውይይት ለማቅረብ ሞክራለች። ይህም ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን የውሃ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ ከድርድሩ በኋላ ለጋዜጣው ሪፖርተር ተናግረዋል።የግብፅ ተደራዳሪዎች ተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ ባለሙያ እንዲቀጠር ሃሳብ ማቅረባቸውም ነው የተገለፀው። ይህም በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነትን ሳያገኝ ቀርቷል።በኢትዮጵያ በኩል «ዕውቀቱ ያላቸው ዓለም ዓቀፍ ባለሙያዎች ከተቀጠሩ ተጨማሪ ባለሙያ መቅጠሩ አስፈላጊ አይደለም» የሚል አቋም መኖሩን ሚኒስትሩ ያስረዳሉ።

በግልጽ ውይይት በድርድር መድረክ የቀረቡትን አሳማኝ ምክንያቶች መቀበል ያቃታቸው የግብፅ ባለሥልጣናት የሀሰት ፕሮፓጋንዳዎችን መንዛት ከጀመሩም ሰነባብተዋል።በቅርቡ በሱዳን ካርቱም በተካሄደው ድርድር ላይ ሃሳባቸው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ፊታቸውን ወደ «በሬ ወለደ» የፈጠራ ወሬ አዙረዋል። በዚህም የግብፅ የውሃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር በቃል አቀባያቸው ሚስተር ካህሊድ ዋሴፍ በኩል «የግድቡ ግንባታ ከፍተኛ የገንዘብ እጥረትና የቴክኒክ ችግር አጋጥሞታል። የግንባታው ሂደትም በጣም የተንቀራፈፈ ነው...» በማለት የሀሰት ፈጠራውን ለመንዛት ሞክረዋል።

በኢትዮጵያ በኩል እየተገለፀ ያለው የግድቡ ግንባታ 30 በመቶ መድረስን እነ ሚስተር ዋሴፍ « ኢትዮጵያ ለሚዲያ ፍጆታ የምታናፍሰው ወሬ ነው። ይህም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው» በማለትም ያጣጥላሉ።ባለሥልጣናቱ ግብፅን ሊጎዳ በሚችል ማንኛውም ጉዳይ ላይ አንደራደርም በሚል አደናጋሪና ከእውነታው በራቀ የተሳሳተ ሀሳብ ሠላማዊውን መድረክ እየረገጡ ይገኛል።የተፋሰሱ አገራት የወንዙን ውሃ በፍትሃዊነት እንጠቀም እንጂ የግብፅን ህዝብ እንጉዳ ያሉበት ጊዜ አለመኖሩ ግልፅ ነው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁሉንም የተፋሰሱን አገራት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከግንባታው ይፋ መሆን ጀምሮ ሲገለፅ የነበረ ጉዳይ ነው።የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ፕሮጀክቱ በተለይም ለተፋሰሱ የታችኛው አገራት ለሆኑት ሱዳንና ግብፅ ጥቅሙ ቀላል አይደለም፡፡ከጎርፍ ስጋትና ከደለል ሙሌት ይታደጋቸዋል፡፡የውሃውን ትነት መጠን በመቀነስ ረገድም ድርሻው ጉልህ ነው፡፡ጎረቤት አገራትም የኤሌክትሪክ ኃይልን ከኢትዮጵያ ለማግኘት ይረዳቸዋል።የግንባታ ሂደቱም በተያዘለት ዕቅድ መሰረት እየተጓዘ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ግንባታው 30 በመቶ መድረሱን ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ። ።

የግድቡ ግንባታ የቴክኒክ ችግር አጋጥሞታል እየተባለ የሚናፈሰው ወሬም ፍፁም ሀሰት መሆኑ ተገልጿል። ግንባታው በቀጣይም በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲጓዝ ይደረጋል። ይህንንም የኢትዮጵያ መንግስት «... ኢትዮጵያ ግንባታውን ለደቂቃም አታቆምም» በማለት አረጋግጧል። የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥ ግብፅ እያደረገች ያለውን ዓለም ዓቀፍ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጥረትም አጥብቃ ትቃወማለች።

የኢትዮጵያ መንገድ ዘመኑ የሚጠይቃቸውን በጋራ የማልማትና የመጠቀም አካሄዶችን ያጠናክራል፡፡ በተፋሰሱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆንም በር የከፈተ እርምጃ ነው፡፡ይህ ጤናማ አካሄድ ታዲያ በግብፅ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ አይመስልም፡፡ የግብፅ ባለስልጣናት እውነታውን ተቀብሎ በትብብር ከመስራት ይልቅ በአሁኑ ዘመን ተቀባይነት የሌለውን የተሳሳተ አስተሳሰብና አመለካከት ይሰነዝራሉ፡፡

ኢትዮጵያ የዚህ ዓይነቱ የ«እኔ ብቻ በልቼ ልሙት...» አካሄድ መቆም እንዳለበት ነው ስትሟገት የቆየችውና እየተሟገተች ያለው። ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ወንዙን በፍትሀዊነት መጠቀም እንዳለባቸውም ስታሳስብ ቆይታለች፤ እያሳሰበችም ይገኛል። ይህንንም ከግብፅ በስተቀር ሌሎቹ የተፋሰሱ አገራት ደግፈውታል፤ ተቀብለውታልም።

ግብፅ ከአባይ ወንዝ 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ያለምንም ተቀናቃኝ ስትጠቀም ኖራለች፡፡እኤአ በ1959 ከሱዳን መንግስት ጋር አዲስ ስምምነት በማድረግ 18 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለሱዳን እንዲደርሳት በመፍቀድ በአባይ ወንዝ ላይ በበላይነት የመፍቀድና የማዘዝ መብትን ይዛ ቆይታለች፡፡ይህ የ«እኔ ብቻ በልቼ ልሙት… »አባዜ ደግሞ ዘመኑ ያለፈበትና ያፈጀ አካሄድ ነው፡፡ ለዚህም ነው በተፋሰሱ አገራት ዘንድ ተቀባይነት ያጣውና የተወገዘው፡፡ በዘመነ ዴሞክራሲና ግሎባላይዜሽን «እኔ ብቻ ልብላ» ቦታ የለውም፡፡ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያልተመሰረተ አመለካከትና አስተሳሰብ የመከነና ጊዜ ያለፈበት ነው፡፡
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

4 comments:

Anonymous said...

We do not give our hand for Egypt.Egypt like or not we have the right to use & construct the great RENAISSANCE dam. This is the matter of sovereignty.In my attitude I am ready to pay any devotion based on this great dam & also the whole Ethiopian people. We should not accept the old fashion agreement.We Ethiopian must be strengthen our internal unity & we have to wake up about our country.The time is for Ethiopians & we have to accomplish any activities with Ethiopians government. The late prime minister Meles Zenawi & his followers vision will be successful.

Muluneh Tsegaye(Ass.Inspector)
Addis Ababa (Mexico)

Anonymous said...

I have seen most of the time the Egyptian leader make mistake,but the Ethiopian government & the people not hurry to decision.Because they study the matter deeply & smoothly by their wisdom. So the Ethiopian government & the people every time should follow this kind of method for there mother land benefit.We Ethiopians should proud by our country& our government. We have to support the government.Internally we can solve our problem by discussing around the table.I thank for the late Prime minister Meles Zenawi, because he has shown the way.Prime minister Meles Zenawi not died and I also admired the current Prime minister H/mariam Desalegn by keeping his promise & strongly he has accomplished his mission by commitment with his government.

Muluneh Tsegaye
( A/Inspector)
Addis Ababa(Mexico)

Anonymous said...

it's a good article. i appreciate z writer. by z way addis zemen on z good trake keep ip up

Anonymous said...

Egypte is first its country and people,
We Ethiopia also -first our country and people

Post a Comment