Sunday, January 26, 2014

ዋ ል ያ «ወጣ ወጣና እንደሸንበቆ...»

(Jan 26, 2014, (አዲስ አበባ))-መቼም የሀበሻ ነገር ትንሿን ድል አጋግሎ ማድመቅ እንወዳለን፡፡ ለዘመናት ከሀገር በታች በድህነትና ኋላቀርነት ተኮራምታ የኖረችን ሀገር «የዳቦ ቅርጫት፣ ዙሪያ ገባዋ ለምለም....» እያልን ስንካክብ ኖረናል፡፡ አሁንም ቢሆን ገና ጣራችን ብዙ ነው ፡፡ በነፍስ ወከፍ ገቢና በድህነት መለኪያም ቢሆን ከ 200 የዓለም ሀገራት ከአስሩ ጭራዎች ተርታ የተሰለፍን መሆኑን መርሳት አጉል ትምክህት ይሆናል፡፡ ያገኘናቸው ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢኖሩም ይበልጥ ጠንክረን በሁሉም ዘርፍ ካልሠራን መጭው ጊዜ ፈታኝና የውድድር ነው።

ወደ ጉዳዩ ልመለስ ባለፉት ጥቂት ወራት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ጋር በተያያዘ የተቀጣጠለው ጣሪያ የደረሰ ስሜታዊነትም ተመሳሳይ ገፅታ አለው፡፡ ለዘመናት የኳስ ጨዋታ ድል የናፈቀው ህዝብ ለዓመታት የአውሮፓ ክለቦችን ሲደግፍ ኖሮ ሲያበቃ የተነቃቃ ለመሰለው የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት እጁን ሰጥቶ አቅሉን ጣለ፡፡ ከዳር ዳር አብዶ ኳስ ጨዋታ አለ በተባለ ቁጥር አረንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ መለያ ለብሶ ፊቱን ሳይቀር ቀለም እየተለቀለቀ ጮቤ ረገጠ ፡፡

ከሀገሪቱ መሪዎች እስከ ህፃናት፣ ከትልቆቹ ዘፋኞች «ዕውቅና» እስከሚሽቱ የነጠላ ዜማ ለቃቂዎች ድረስም ተዘፈነለት፡፡ በዚህ የታበዩት የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኞችም ዶክመንተሪ ፊልም አሰሩ፡፡ ከዚያም አልፈው በቻን ውድድር «ዋንጫ እናነሣለን» ብለው አቀዱ፡፡ ሌላው ቀርቶ «የውጭ ሀገራት ብሄራዊ ቡድን እንዳሰለጥንላቸው ጠይቀውኛል» ሲሉ ታበዩ። ይህ ሁሉ መሞጋገስና መኮፈስ ባልከፋ ፣ እውነታው ግን ብሄራዊ ቡድኑ ያረጀ ያፈጀ መሆኑ ብቻ ሣይሆን እግር ኳሳችን ገና እንጭጭና ቃሪያ መሆኑ በአደባባይ ተጋልጧል፡፡ በሀገር ውስጥ የክለቦች ውድድር ብቻ የሚሳተፍ የአፍሪካ 16 ቡድኖች በተሳተፉበት የቻን ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ የተሳተፈው ይህ ቡድን ከየትኛውም ተወዳዳሪ በተሻለ ሙሉ ቡድኑን ያሠለፈ ነው፡፡

ነገር ግን የሦስተኛውና የመጨረሻው ጨዋታ ኮሜንታተር እንደገለፀው «በአንድ ጎል ሲገባበት የሚደነግጥ፣ ጎል ማግባት የማይችልና እልህና ወኔ የጎደለው ብሄራዊ ቡድን» ካለነጥብ ተመልሷል። ይሄ በትክክል ያለንበትን ሁኔታ የሚያመለክት ነው፡፡ አሰልጣኙም ሆነ ቡድኑ ህዝቡ በፈነቀለው ድጋፍና «በዕድል» ጭምር ባለፉት ጊዜያት ድልን አሳይተውናል፡፡ ነገር ግን ቡድናችን ዜሮ ነው ብለን ከምንም ለመነሳት ካልተጋን በስተቀር በትንሹ መታበይ የማታ ማታ ውጤቱ ያየነው መሆኑ አይቀርም፡፡

ብሄራዊ ቡድናችን ለ270 ደቂቃ ሦስት ጨዋታዎችን ሲያካሂድ አምስት ጎል ሲገባበት አንድም ጎል ማስገባት አልቻለም ፡፡ ከአስራ ስድስቱ ቡድኖች የመጨረሻ ሆኖ ለመሰናበትም ተጋልጧል፡፡ አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ ተመልካቾች ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት «ከሚታሰበው ባነሰ ፍጥነት ውስጥ የተንኮታኮተ ብሄራዊ ቡድን» ሆኗል፡፡ ችግሩን እውን የሁለቱ አጥቂዎች አለመኖር ብቻ ነውን? ያስብላል።

አንዳንድ የብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች በታክቲክና ቴክኒክ ብቻ ሳይሆን በአቅምና ጉልበታቸው «አማተር ነታቸው» በገሃድ ወጥቷል፡፡ ተንሸራትተው ከወደቁበት ሣይነሱ የተቃራኒ ቡድን ጎል ያስገባባቸው ተከላካዮች «ምርጥ» ስንላቸው የኖርናቸው ተከላካዮች ናቸው፡፡ በሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አላሲዝ ብለው በየሜዳው የቆጥ የባጡን ሲቀባጥሩ የነበሩ ተጨዋቾች ሁሉ ደረጃቸው የት ጋር እንደሆነ በግልፅ ተረድተናል፡፡ በድምሩ ሀገሪቱንና ህዝቦቿን የሚመጥን ተኪ ሃይል በማያባራ ሁኔታ ለማግኘት ካልተሰራ እግር ኳሳችን ከድህነታችን በላይ አሽቀንጥሮ የሚጥለን ባዶ ጉሠማ ነው፡፡

ሀበሻ «ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት» የሚል ወጊ ተረት አለው፡፡ አንገቷን ለመበጠስ ምላጭ አልያም፣ አርዶ ለመጣል አንድ እጅ እየበቃት ለዶሮ መጫኛ መጎተትን አስቡት ፡፡ እኛም አንዳንዴ የምናደርገው ከዚህ የተለዬ አይደለም፡፡ ይሄ ብሄራዊ ቡድን አማተር ብቻ ሳይሆን በልጆቹ የግል ጥረት፣ በቀናነትም ፣ በፀሎትም እዚህ እንደደረሰ እያወቅን በከንቱ ከልኩ በላይ ሃላፊነት ጫንንበት፡፡ ራሱን ከማዬት ይልቅ የእኛን ልብ ትርታ ሰምቶ ብቻ «ዋንጫ አመጣለሁ» የሚልበት አጣብቂኝ ውስጥ ከተትነው። ይሄው በዜሮና መጨረሻ ሆኖም አገኘነው፡፡

ይህ በመሆኑም የማይሞቃቸውና የማይበርዳቸው አሰልጣኞች «በክብር ስራ እንለቃለን» እንኳን ሣይሉ « ስራ መልቀቅ ስለማልፈልግ እቀጥላለሁ» ከማለት አልተቆጠቡም ፡፡

በአህጉር ደረጃ ለሦስተኛ ጊዜ ባሳለፍናቸው ቀናት እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ የቻን እግር ኳስ ዋንጫ አዳዲስ ተጫዋቾች ለዓለም አቀፍ የኳስ መድረክ የሚታጩበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ግን አዳዲስ ተጫዋቾችን ሣያቀላቅል የተጓዘው ነባሩ የዋልያ ቡድን እምብዛም ሣይሳካለት የመጨረሻ ቡድን (ምንም ጎል ሳያስገባ፣ አምስት ጎሎችን አስተናግዶ ) ሆኖ ተመልሷል፡፡

የቡድኑን ትክክለኛ ገፅታ ባለማሳየት በተለይ ገንቢ የሆነ ትችትና ክፍተትን ማሳየት ባለመቻላቸው በቀዳሚነት የሚወቅሱት የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በተለይ ወሬያቸው የማያልቀው « የኤፍ.ኤም ስፖርት » ዘጋቢዎች ናቸው፡፡ ከጥቂት በሳል ጋዜጠኞች በስተቀር አብዛኛዎቹ «የእምቧይ ካብ» ሲኮለኩሉ ነው የከረሙት ፡፡ ሌላው ቀርቶ የአቅምና ብቃት መጓደል፣ የአጥቂ እጥረት፣ ኳስ ማንሸራሸር እንጂ አጥቂ አለመኖር ማን ደፍሮ አንስቶ ያውቃል፡፡ አንዳንዶቹን ተጫዋቾች ከልክ በላይ ክበን እንድንመለከት ያደረገንስ ማን ነው፣ የህልም እንጀራ ጋጋሪ የሆኑት የስፖርት ጋዜጠኞቻችን ናቸው ብል ስህተት አይሆንም፡፡

በአጠቃላይ « አሁንም ጊዜ አለን» ለማለት የሚቻለው ሁላችንም በእውነት ላይ ተመስርተን ሳንደባብቅ በጉዳዩ ላይ መነጋገር፣ ያገኘነውን መልካምም ሆነ ደካማ ተሞክሮ ቀምረን ለመማር ስንችል ነው፡፡ አሰልጣኞቹ ፣ የፌዴሬሽኑ አካላት፣ የስፖርት ቤተሰቡና ተጨዋቾችም ቢሆኑ ራሳቸውን በዝርዝር ፈትሸው ለለውጥ መነሳት ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡

በእርግጥም «እንደ ፉክክር» በየክልሉ ጥሩ ጥሩ ስቴዲየሞችን እየሰራን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ዩኒቨርሲቲዎችና አንዳንድ መለስተኛ የትምህርት ተቋማትም መለስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ገንብተዋል፡፡ ግን ማን ሊጫወትባቸው ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የወጣቶችና ታዳጊዎች የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች የት አሉ? በአንዳንድ ክልሎች የተገነቡ የአትሌቲክስ መንደሮችና የስፖርት ካምፖችስ የት ደረሱ፣ እውን የፕሪሜየር ሊግ ክለቦቻችንስ ከአማተር አስተሳሰብ እየወጡ ነውን? ወጣትና አዲስ ተተኪ ሃይልስ በስፋት ታይቶባቸዋል በዝርዝር መፈተሽ ያለባቸው ተጠይቆች ናቸው፡፡

የስፖርት ሴክተሩን በተለይ እግር ኳሱን እየመሩ ያሉ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤቶችም በጥልቀት ውስጣቸውን ሊፈትሹ ይገባል፡፡ ሌላው ቀርቶ በጠራ ስትራቴጂ መነሻና መድረሳቸውን ያውቁታልን፣ ግልፅ በሆነ ራዕይና ተልዕኮ በመመራት ግባቸውን ለማሳካትስ እየተጉ ነው ማለት ይቻላል ወይስ «ንፋስ አመጣሽ» እንደሚባለው ድንገት በመጣ ድል ተንበሽብሸው «ኳሳችን አድጓል!» የሚል መፈክር ነው እያነሱ ያሉት።

ዛሬ እኮ ስፖርት ያውም እግር ኳስ ትልቅ የፖለቲካና ኢኮኖሚ መሳሪያ ነው፡፡ በዓለም ላይ በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች ኢንቨስት የሚደረግበት፣ የዜጎችን ብሄራዊ ስሜት ከምንም በላይ የሚቀሰቅስ፣ የህዝቦች መዝናኛና የአእምሮ ማረፊያ ነው፡፡ ለዚህም ነው የድሃ ሀገራት ህዝቦች ሳይቀሩ በሀገራቸው ሊግ ሣይረኩ ሲቀሩ የአውሮፓን እግር ኳስ ለማምለክ እየተዳረጉ ያሉት፡፡ ከዚህ አንፃር እግር ኳስን የመሠሉ ወሳኝ ስፖርቶችን በማግለል « ልማት» ብለን የማህበረሰብ ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡

ሰሞኑን በቻን ውድድር ያባረሩን ሐገሮች የቅርብ ጊዜ ታሪክን ለፈተሸ ሊቢያ ላለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ እንኳን እግር ኳስ የተረጋጋ መንግስትም ያላገኘች፣ ኮንጎ ብራዛቢልም ከአንድ የሃገራችን ክልል ህዝብ በላይ እንኳን የሌላት ድሃ ሀገር ነች፡፡ በኳስም ሆነ በሌላው ገፅታዋ የተሻለች የምድብ ሦስት ተጋጣሚያችን ጋና መሆኗ ባይካድም እኛ ግን ከሁሉም ጭራ ቡድን እንዳለን ግልፅ ሆኗል፡፡ ለነገሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ በደቡብ አፍሪካ ባካሄድናቸው ሰባት ጨዋታዎች ብሄራዊ ቡድኑ ላይ 12 ጎል ሲቆጠር ያስገባነው ሁለት ብቻ ነው፡፡ በአንዱ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ ጋር አንድ እኩል ብንወጣም በሁሉም ተሸንፈን መመለሳችንንም ያስታውሷል ፡፡

በአጠቃላይ እግር ኳስ የምንወድም ሆንን ለሀገራችን ክብርና ፍቅር ያለን ዜጎች ኳሳችን ያለበትን ደካማ ደረጃ ተገንዝበን ለለውጥ እንነሣ፡፡ አጉል መካካቡና መንጠራራቱ የትም የሚያደርስ አይመስለኝም፡፡ ጋዜጠኞቻችንም ቢሆኑ « በጥራዝ ነጠቀ» ኮሜንተሪ ሁሉንም ከማደናገር ወጥተው የበሰለና በሣይንሳዊ ምርምር ላይ የተመሠረተ መረጃ ሊሰጡን ግድ ይላል፡፡ የመንግስትንና የህዝቡንም ድርሻ ደጋግሜ እንዳነሳሁት ነው፡፡ ለሁሉም ላቅ ላለ ውጤት ከፍ ባለ ትኩረት እግር ኳሱ ላይ ሊሠራ ይገባል ለማለት እወዳለሁ፡፡ ሠላም!!!
(ፀሃፊዋን በኢሜል አድራሻቸው Emu2001@yahoo.com ያገኟቸዋል)
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ 

1 comment:

ELIAS EBRAHIM said...

ha ha it`s amazing don`t say this stupid writer they are our " patriots "

Post a Comment