Friday, January 03, 2014

የእግር ኳሳችን ሌላው ካንሰር

(Jan 03, 2014, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያን እግር ኳስ የተለያዩ ፈተናዎች እየተጋረጡበት እጁን ሲሰጥ ቆይቶ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) ታሪክ ተደርጎ የማያውቀውን ከሁለት ሀገራት ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ አድርጎ ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ያለፈውን ብሔራዊ ቡድን እንደ ብሔራዊ ጀግና የሚያስቆጥር፣ ደካማው ካፍ ከሚያዘጋጃቸው ውድድሮች እጅግ ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠውን የቻን ውድድር ለመካፈል የሀገር ውስጥ ሊግ ውድድርን ቢያንስ ከሁለት ወር ላላነሰ ጊዜ የሚያቋርጥ፣

ከአንድ ክለብ የሚጫወቱ (ለክለቡ በቋሚነት ይጫወቱም አይጫወቱ) አስር ተጫዋቾችን ለብሔራዊ ቡድን የሚመርጥ አሰልጣኝ፣ ዳኛን ለመደባደብ እጁን የሚሰነዝር ተጫዋች፣ የዳኛን ካርድ ለመቀማት የሚዘል የክለብ አምበል፣ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የአሰራር ክፍተትና ብልሹ አስተዳደር ያለበት የፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፤ እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ ህልቆ መሳፍርት ፈታኝ ችግሮች የከበቡት እግር ኳሳችን ከዚህም በላይ ሌላ ጋሬጣ ፊቱ ላይ ተደቅኖበታል።

ካንሰሩ ምንድን ነው?
በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ባደረገበት ወቅት በዓመት ከስታዲየም ገቢ ያገኘውን ገንዘብ ይፋ አድርጎ ነበር።በክለቡ ይፋ የሆነው የገንዘብ መጠን 280ሺ ብር እንደሆነ ሲነገር የሰማ አንድ የእግር ኳስ ተከታታይ «ክለቦቹ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት በዝግ ስታዲየም ነው ወይ» ብሎ እስከመጠየቅ ቢደርስ አይፈረድበትም። እንደሚታወቀው ከላይ የተጠቀሰው ክለብ ሀገራችን ውስጥ ካሉ ባለበርካታ ደጋፊዎች ክለብ አንዱ ሲሆን ከኢትዮጵያ ቡና ያነሰ ደጋፊ ያላቸው ክለቦች በዓመት ምን ያህል ገንዘብ ከስታዲየም ገቢ ይሰበስባሉ? ብሎ መጠየቅ ይችላል።

እውነት ለመናገር አንድ ክለብ አንድ ገና በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ተጫዋች ለመግዛት ከሦስት መቶ ሺ ብር በላይ እያወጣ ዓመቱን ሙሉ ደመወዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ጨምሮ ከ100 በላይ ለክለቡ ሰራተኞች የሚያወጣውን ጠቅላላ ወጪ ሲደመር ቢያንስ ከሦስት እና አራት ሚሊዮን ብር በላይ እያወጣ ከስታዲየም የሚያገኘው ገቢ ግን ለአንድ ወጣት ተጫዋች ግዥ የማይሆን ገንዘብ መሆኑ «እውነት ግን እግር ኳሳችን ወዴት እየሄደ ነው?» ብለን የምንጠይቅበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።ከዚህ ሁሉ የባሰው ደግሞ ጭራሹኑ ደጋፊ የሌላቸው የሚባሉ ክለቦች በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መኖራቸው ነው።

ክለቦቹ ለምን ቁጥሩ የበዛ ደጋፊ ሊኖራቸው አልቻለም?
መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ ሰባት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቢኖሩም የአዲስ አበባ ስታዲየምን በደጋፊ የሚያጨናንቁት ክለቦች ግን ሁለት (ቡናና ጊዮርጊስ) ናቸው። በቅርቡ ደግሞ ደደቢት የሁለቱን ክለቦች ፈለግ እየተከተለ ይገኛል።ሌሎች ክለቦችን ስንመለከት ግን ስለደጋፊ ቁጥር ማነስ የሚያሳስባቸው አይመስሉም።ለዚህም የተማመኑበት አንዳች የገንዘብ ኃይል አለ ወደ ማለቱ እንድናመራ ያደርገናል።ይህ ገንዘብ ደግሞ የህዝብ የሆነው የመንግሥት በጀት ነው።

በርካታ ክለቦች በደጋፊ ድርቅ መመታታቸውን በተመለከተ «ደጋፊዎች ከስፖርቱ ሜዳ እየራቁ የሄዱት ክለቦች የራሳቸው ስታዲየም ስለሌላቸው ይሆን?» ብለን የጠየቅነው ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ የስታዲየም ግንባታ አስፈላጊነት እንደማያጠያይቅ ይናገራል።እንደ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ገለጻ፤ከስታዲየም ግንባታ በፊት ስፖርቱን የሚገነባበት መንገድ መፈጠር አለበት።ይህም ማለት ታዳጊዎች የሚጫወቱባቸው ማዘውተሪያ ቦታዎችን መገንባትና ታዳጊዎች ብቃታቸው የሚያድግበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል ማለት ነው።

«በርካታ ወጣት ተጫዋቾች በሀገራችን ሲገኙ ክለቦች ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ»የሚለው ጋዜጠኛ ኢብራሂም፣በአዲስ አበባ ስታዲየም ከሚደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ገብቶ ጨዋታቸውን የሚከታተልላቸው ክለቦች ቁጥር ሁለት ወይም ሦስት ብቻ መሆናቸውን ነው የሚናገረው።«ይህ የሚያሳየው ሌሎች ክለቦች ስፖርት አፍቃሪው እንዲደግፋቸው ራሳቸውን አላጠናከሩም ወይም ክለቦቹ ውጤት ስለሌላቸው ደጋፊ የላቸውም ማለት ነው» ሲል ነበር አስተያየቱን የሰጠው።

ከጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አነጋገር ተነስተን በአሁኑ ወቅት ያለውን የሀገራችን እግር ኳስ የሚገኝበትን ደረጃ ለማየት ስንሞክር እውነትም ሌሎች ክለቦች በደጋፊና በውጤት አሰባሰብ ዙሪያ ገና ያልሰሩት ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለ እንረዳለን።በርካታ ክለቦች በመንግሥት በጀት መንቀሳቀሳቸው ግልጽ ነው።ታዲያ እነዚህ በሀገርና በመንግሥት በጀት የሚወዳደሩ ክለቦች ራሳቸውን በገንዘብ የሚደግፉበትን መንገድ መቼ ነው የሚያመቻቹት? እንዴትስ ነው ወደ ሕዝባዊ ክለብነት ተቀይረው ከሕዝብ ወይም ከስፖንሰር ገቢ ሊያገኙ የሚችሉት? እንደዚህ ከሆነ ደግሞ ክለቦች እንዴት ነው ወደ ውድድር የሚገቡት? የሚሉትን ጥያቄዎች ይዘን ስንነሳ ውሃ የሚያነሳ መልስ ሊሰጠን የሚችል አካል ማግኘት አስቸጋሪ ነው።

ክለቦቹ ራሳቸውን የብዙ ደጋፊዎች ባለቤት ለማድረግ ምን መስራት አለባቸው? ብለን የዳሽን ቢራን እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ካሊድ መሐመድን ጠይቀነው ነበር።ካሊድ«ክለቦች ደጋፊ እንዲኖራቸው ከተፈለገ በቅድሚያ ሊሰሯቸው ከሚገቡ ሥራዎች መካከል የመጀመሪያው ክለባቸውን ጠንካራ ተፎካካሪ ማድረግ ነው።በዚህ ውጤታማ ከሆኑ ክለቦቹ የድርጅት ከሆኑም የድርጅቱ ሰራተኞች የክለባቸው ደጋፊ የሚሆኑበትን መንገድ መቀየስ ከቻሉና የደጋፊ ማህበር ካቋቋሙ የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት ይሆናሉ»ሲል እምነቱን ገልጾልናል።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ግን ከአሰልጣኝ ካሊድ ሀሳብ የተለየ አስተያየት ነው የሚሰነዝረው።ክለቦች የድርጅታቸው ሰራተኛ እንዲደግፋቸው የሚጠይቁ ከሆነ ሰራተኞችን ያለፍላጎታቸው ማስገደድ ሊሆን ይችላል ባይ ነው ጋዜጠኛ ኢብራሂም።ደጋፊው ራሱ ክለቡን አምኖበት የእኔነት ስሜት አድሮበት እንዲደግፈው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የሚናገረው።

ጋዜጠኛ ኢብራሂም እንደሚናገረው፤ክለቦች ደጋፊ ሊኖራቸው የሚችለው ደጋፊዎቹ ክለባቸውን «የራሴ» ብለው የሚመለከቱት ሲሆን ነው። ለአብነት ያህልም አሰልጣኝ ካሊድ የሚያሰለጥነው ዳሽን ቢራ በፕሪሚየር ሊጉ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ዝቅተኛ ቢሆንም ክለቡ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ የሚመለከተው ደጋፊ ብዛት ስታዲየሙን ከአፍ እስከ ገደፉ ይሞለዋል።

ይህ የሚያሳየው ዳሸንን እየደገፈ ያለው የክለቡ ውጤት ያስገኘው ደጋፊ ወይም የፋብሪካው ሰራተኛ ብቻ አለመሆኑን ነው።ታዲያ ዳሽን ይህን ያህል ደጋፊ እንዴት ሊያገኝ ቻለ? ለዚህም ካሊድ መልስ አለው«የከተማ ክለቦች የበርካታ ደጋፊ ባለቤት እንደሆኑ አለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ማየት ይቻላል።እኛ ብቻ ሳንሆን ሌሎች የደቡብና የኦሮሚያ ክልል ክለቦችንም ብታዩ ክለቦቹ ጨዋታ ሲያደርጉ ስታዲየማቸው ልክ እንደኛው ይሞላል» ይላል።ከካሊድ አነጋገር ተነስተን የክለቦቻችንን ደጋፊዎች አደጋገፍ ስንመለከት ጋዜጠኛ ኢብራሂም እንደተናገረው ደጋፊዎች የአካባቢያቸውን ክለብ ከውስጣቸው በመነጨ ስሜት (Blood and Soil) እየደገፉት እንደሚገኝ ነው።

ይህንን አባባል ትክክል ሆኖ የምናገኘው በ2005ዓ.ም ሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ወላይታ ዲቻና ዳሽን ቢራ እግር ኳስ ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲያደርጉ ወላይታ ዲቻን ለመደገፍ ስታዲየም ተገኝቶ የነበረውን ሕዝብ ቁጥር ነው።በእለቱ በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚኖሩ የወላይታና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች ለአካባቢያቸው ተወካይ ወላይታ ዲቻ ያደረጉት ድጋፍ እውነትም ኢብራሂም ሻፊ «ሰውን አሳምነህ እንጅ አስገድደህ የክለብህ ደጋፊ ልታደርገው አትችልም» ያለው አባባል ትክክል ነው ብለን እንድንቀበል ያደርገናል።

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) ደግሞ ከካሊድም ሆነ ከኢብራሂም ሃሳብ የተለየ አስተያየት ነው የሚጠቅሰው።ለማንጎ ክለቦች ደጋፊ የሚኖራቸው «የመጀመሪያው የደጋፊ ማፍሪያ (ማብዣ) መንገድ ክለቡ ሜዳ ላይ የሚያሳየው ጨዋታ ነው።

ለምሳሌ የእኛ ክለብ(ኢትዮጵያ ቡና) ዋንጫ ካነሳ ረጅም ጊዜው ቢሆንም ደጋፊዎቹ ግን አሁንም ክለባቸውን ከማበረታታት ወደ ኋላ የሚሉ አይደለም። ምክንያቱም ማራኪ ጨዋታ እያገኙ ነው።እንዲሁም በብሔራዊ ሊግ የሚወዳደሩትን ሰበታ ከነማንና ሱሉልታ ከነማን ሳሰለጥን የገጠመኝም ተመሳሳይ ነው።ክለቦቹ ለተመልካች አዝናኝ ጨዋታ እንዲያሳዩ ተደርገው የተቀረጹ ስለሆኑ ደጋፊው በክለባቸው ማራኪ ጨዋታ እየተዝናና ይደግፋቸዋል» ይላል።ለአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ክለቦች በርካታ ደጋፊ የሚኖራቸው ክለቦቹ ሜዳ ላይ በሚያሳዩት ውበት ያለው ጨዋታ ነው።
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ  

No comments:

Post a Comment