Sunday, November 24, 2013

እኛ እና ሳዑዲ

(Nov 24, 2013, (አዲስ አበባ))--የእኛና የሳዑዲ አረቢያ ግንኙነት የጀመረው ከሁሉም እስላማዊ የታሪክ ክንውኖች በፊት ነው፡፡ ግንኙነቶቻችን የጀመሩት እስልምና ‹‹ሱኒ›› እና ‹‹ሺአ›› ተብሎ ከመከፋፈሉ በጣም በፊት ነው፡፡ አራቱ ታላላቅ የህዝበ ሙስሊሙ (ኡማ) መሪዎች (አቡከር፣ ዑመር፣ ዑስማን፣ አሊ) እንደመሪ ከመከሰታቸው በፊት ነው፡፡ የኢትዮጵያና የእስልምና ግንኙነት የተጀመረው ኻዋሪጅ፣ ወሃቢ፣ ሰለፊ… ወዘተ የሚባሉ አክራሪዎች ከመፈጠራቸው በፊት ነው፡፡

የሁለታችን ግንኙነት የጀመረው ከቁርአን ቀጥሎ ተአማኒ የሆኑት የሱኒ እና የሃዲስ ስብስቦች በነቡኻሪ (ሳሂህ ሲታ) አማካይነት በሰነድ ከመሰባሰባቸው እጅግ በጣም በፊት ነው፡፡ የነብዩ (ሰዐወ) ውድ ልጅ የሆነችው ፋጡማ አድጋ ለወግ ለማዕረግ ደርሳ አራተኛውን ከሊፋ አሊ አብደል ሙጣሊብን አግብታ ሐሰን እና ሁሴን የተባሉ ሁለት ልጆችን ወልዳ አባቷን (ነብዩን) አያት ሆነው የልጅ- ልጅ እንዲያቅፉ ለማድረግ ከመብቃቷ በፊት እኛና ሳዑዲዎች እንተዋወቃለን፡፡

የሁለታችን ግንኙነት የተጀመረው ቁርአን አልከሪም ከአላህ ሱብሃን ወተአላ ዋህዩ ተወርዶ ከማለቁ በፊት ነው፡፡ (የመካ እና የመዲና ሱራዎች የሚባሉትን አስታውሱ)፡፡ የእኛ ግንኙነት ታሪክ የጀመረው በእስልምና የመጀመሪያ ዓመታት የነብዩ የራሳቸው ዘሮች የሆኑት ቁሬይሾች ‹‹የሙሐመድን ነብይነት አንቀበልም›› ብለው ተከታዮቻቸውን መግቢያ መውጫ ባሳጡበት ጊዜ ጓዶቻቸውን (ሰሃባዎቻቸውን) ወደ አበሻ አገር ስደት እንዲሄዱ ካዘዙበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ያኔ ነብዩ ራሳቸው ወደ መዲና ስደት (ሂጅራ) ሳይሄዱና እስላማዊው አቆጣጠር በሂጅራ ከመሆኑ በፊት እስልምና ኢትዮጵያን ያውቃታል፡፡

እኛና ሳዑዲ የምንተዋወቀው ነብዩ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ነው፡፡ ያኔ ኢትዮጵያና አረቢያ ጠንካራና መልካም ግንኙነት በነበራቸው ጊዜ የእስላማዊ ሥነ ሕግ ትምህርት ማዕከላት (መዝሃብ) የሚባሉት አራቱን ሃነፊ፣ ሻፊኢ፣ ማሊኪ፣ ሀንባሊ የተባሉትን ጨምሮና ሌሎች ከ200 በላይ የነበሩት የሥነ- ሕግ ተቋማት በእስልምና ታሪክ ውስጥ አልነበሩም፡፡ እስላማዊ ሥነ-ሕግም ሆነ ተራ ሕግ በሳዑዲ ምድር ላይ ፈጽሞና ፈጽሞ ባልነበረበት ጊዜ እኛ እንተዋወቅ ነበር፡፡ ታላላቅ የሚባሉ ክስተቶች ለምሳሌ የካርባላ ጦርነት፣ በአሊ አብደል ሙጣሊብ (አራተኛው ከሊፋ) እና በዑስማን (ሦስተኛው ከሊፋ) ተወካይ ሙአዊያ (ያኔ የሶርያ ገዥ ነበር) መካከል በሲፊን የተካሄደው የሱኒ እና የሺአ ጦርነት (The battle of siffin)… የተከሰቱት ከኢትዮጵያና ከእስልምና ግንኙነት በኋላ ነው፡፡

የእኛና የእስልምና ግንኙነት የተጀመረው የነብዩን (ሰዐወ) የአላህ መልዕክተኝነት አንቀበልም፣ ከአላህ የወረደልኝ መልዕክት (ዋህይ) ነው የሚለውንም አንቀበልም፣ አናምንም ያሉ ቁሬሾች በመካ አላስቀምጥ ሲሏቸው ለእሳቸውና ለተከታዮቻቸው ስጋት ሲሆኑባቸው ወደ መዲና (ያትሪብ) ለመሰደድ ሲያስቡ የተወሰኑ ተከታዮቻቸውን ወደአበሻ ምድር ሄደው እንዲጠለሉ የንጉሱን መልካምነት፣ ከሰው ጥግ የማይደርስና ካልነኩት የማይነካ፣ ፈጣሪውን የሚፈራ መሆኑን ነግረውና መክረው አዘዟቸው፡፡ ነብዩ (ሰዐወ) ደግሞ ዝም ብለው (ከመሬት ተነስተው) አያዝዙም፡፡ አሏህ ባዘዛቸውና በመራቸው ብቻ የሚሄዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ኢትዮጵያ ለእስልምና መጠለያነት ከሌሎች የዓለም አገራት ሁሉ በቅድሚያ የተመረጠች ቅዱስ ህዝብና ቅዱስ መሪ ያለባት መሆኗን ነው፡፡

የነብዩ (ሰዐወ) ሰሃባዎች (ጓዶች) የነበሩት በትዕዛዙ መሠረት ወደአበሻ ምድር (ወደኛ አገር) ሲመጡ የአበሻው ንጉስ በክብር ተቀብሎ ስለሃይማኖታቸው (እስልምና) ይዘት ጠይቆና ተረድቶ እውነትነቱንም አረጋግጦና ተደስቶ በአገሩ እንደማንኛውም ዜጋ እንዲኖሩ ሊያጠቃቸው የሚነሳ ኃይል ቢኖር እንደሚከላከልላቸው ቃል ገብቶ አስቀመጣቸው፡፡ ያኔ በዚህ ሁኔታ የተፈጠረው ግንኙነታችን እየተጠናከረ መጥቶ ዛሬ እስልምናና እኛ የአንድ ቤተሰብ ልጆች ሆነናል፡፡ የግንኙነታችንን ታሪክ ከነብዩ መነሳትና ከእስልምና ጋር ማቆራኘታችንና ከመካ ወደ አበሻ ምድር ከመጡት የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ጋር ማገናኘታችን ተገቢ የሚሆነው ከዚያ በፊት ባሉት ዘመናት የአረቢያ ምድር እዚህ ግባ የሚባል አንዳችም የረባ ታሪክ የሌላት በመሆኗ ነው፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ተብላ መጠራት ከጀመረች እንኳ መቶ ዓመት ቢሆናት ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ አሏህ ነብዩን(ሰዐወ) በመሪነት ባያስነሳላትና ቁርአን አልከሪምን ባያወርድላት ኖሮ ሳዑዲ አረቢያ እንኳን ሊኖሩባት ቀርቶ በአጠገቧ የማያልፉባት ለምንም የማትሆንና ለማንም የማትመች ምድረ በዳ ነበረች፡፡ ነጋ ጠባ በጐሳ ጦርነት እርስ በርሱ ሲዋጋና ሲገዳደል የሚኖር ህዝብ መፈንጫ ነበረች፡፡ ሴት ልጅ ሲወልዱ ከማፈራቸውና ከመጥላታቸው የተነሳ ከነሕይወቷ የሚቀብሩ ጨካኞች አገር ነበረች፡፡ ነብዩ ይህን አድራጐታቸውን እያወገዙ አላህ የሰጣችሁን ሴት ልጅ በምን ሀጢአቷ ከነነብሷ እንደቀበራችሁት ፈጣሪ ይጠይቃችኋል እያሉ በማስተማር እንዲስተካከል ባያደርጉ ዛሬም ድረስ ይቀጥል ነበር፡፡ ያን ጊዜ አረቦች ሴት ልጅ ሲወለድላቸው አይወዱም፡፡ የዚያኔዎቹ የአረብ ወንዶች መጠጥ ወዳድ መሸተኞች ነበሩ፡፡ ነብዩ ሰክራችሁ ወደሶላት አትቅረቡ(ላ ተቅርቡ ሶላት ወአንቱም ሱካራ..) እያሉና መጠጥ ጥንቆላና ቁማር የሸይጣን ሥራ ነው፣ ራቁ…(ኢነማል ኸምሩ… ሚን አመሊ ሸይጣን፤ ፈጅተኒቡሁ ለአለሁም ቱፍሊሁን) እያሉ በማስተማር ለመለወጥ ችለዋል፡፡

የያኔዎቹ አረቦች በ365 ጣዖታት የሚያመልኩ አረማውያን ነበሩ፡፡ የያኔዎቹ የአረብያ ሴቶች ሰውነታቸውን ገላልጠው ወንድ ለመሳብ ጠንካራ መአዛ ያለው ሽቶ ተቀብተውና ድምፁ ከሩቅ የሚጣራ ጫማ ተጫምተው የሚሄዱ ነበሩ፡፡ ይሄ የመሃይምነት ዘመን መገላለጥ (ተበሩጂል ጃሂሊያ) ነው ብለው እያስተማሩ ያስቀሩላቸው ነብዩ (ሰዐወ) ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው ስለአረቢያ ስናወራ ከነብዩ መሐመድና ከቁርአን ጀምሮ ባለው የግንኙነታችን ታሪክ ላይ ማተኮር ያለብን፡፡

የአረቢያ ምድር ህዝቦች ከዛሬ 60-70 ዓመት በፊት ነዳጅ እስከአገኙበት ጊዜ ድረስ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚማቅቁ ነበሩ፡፡ በየአገሩ ተበታትነው የእለት ጉርስ ፍለጋ መከራቸውን ሲያዩ ኖረዋል፡፡ ለችግረኞቹ የአረብ ህዝቦች አንዷ መዳረሻ ይቺው የአበሻ አገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ አረቦች በኢትዮጵያ በተሸካሚነት (በኩሊነት)፣ በጋሪ ገፊነት፣ በዳቦ ጋጋሪነት፤ በፓስቲ ጠባሽነትና በሻይ ቤትነት እንዲሁም እስከገጠር ድረስ ዘልቀው ገብተው ሱቅ እያበጁ በቸርቻሪነትና በሚዛን ቀሻቢነት ተሰማርተው ተዳድረዋል፡፡ ከአገራችንም ሲወጡ ከዚህ ያገቧቸውን የእኛን ሴቶችና ልጆቻቸውን እንዲሁም ያፈሩትን ሀብት ይዘው በክብር መሄዳቸውን እናውቃለን፡፡

በዚያን ጊዜ አንድም አረብ የመኖሪያ ፈቃድ አልነበረውም፡፡ ዝም ብሎ መጥቶ ዝም ብሎ ይኖራል፡፡ ባዶ እጁን መጥቶ እዚህ ይከብራል፡፡ ይዳራል ልጅና ሀብት ያፈራል፡፡ የሚጠይቀው የለም፡፡ የሚሠራው ለራሱ ነበር እንጂ ለአበሾች ተቀጥሮ አልነበረም፡፡ ስለዚህ የደረሰበት ግፍም ሆነ በደል የለም፡፡ በኋለኛው ዘመን ነዳጅ እያገኙና እያወጡ መክበር ሲጀምሩ ጠባያቸውን መለወጥ ጀመሩ፡፡ በፔትሮ ዶላራቸው አማካይነት በሁለቱ ቅዱሳን ስፍራዎች በመካ እና በመዲና ማዕከላት የራሳቸውን ሕግ እያወጡ ኃይላቸውን ሲያጠናክሩ ሙጠዋእ የሚባሉትን ጢም አስረዛሚና ሱሪ አሳጣሪ የሃይማኖት ፖሊሶችን አደራጅተው በወሃቢያ ጠበል እንዲነከሩ አደረጉ። በኋላም ፀረ-ወሃቢያና ፀረ-ሳውዲ ትምህርቶችንና እንቅስቃሴዎችን የሚያፍን ፣ ራቢጣ አል ኢስላሚያ የተባለ መቺ ኃይል አቋቋሙ፡፡ የዱሮ ደጋፊዎቻቸውን ችላ አሉ፡፡ የተደረገላቸውን ውለታ ረሱ፡፡

እድሜ ለነዳጅ ብሬ አሉ፡፡ ህጋቸውን ሁሉ ለማንም እንዳይመች አደረጉ፡፡ ከአገራችን ያፈሩትን ሀብትና ሴቶቻቸው ሳይደፈሩ ይዘው እንዳልወጡ እነሱ ግን የእኛ ዜጐች የሚደርስባቸውን በደል ሁሉ ችለው ያፈሯትን ጥሪት ነጥቀውና አንገላተው እንዲወጡ አደረጉ፡፡ ሰበቡ በህገ-ወጥ መንገድ የገቡ ናቸው፤ የመኖሪያ ፈቃዱ የሌላቸው ናቸው፤ ለእናንተ ብቻ አይደለም፤ ለሁሉም አገር የወጣ አዋጅ ነው፡፡ ህግና ሥርዓት እናስይዛለን… የሚል ነው፡፡ ቢሆንስ? ከማንም አገር በላይ የነብዩን መልዕክተኞች በክብር ተቀብላ ላስተናገደች አገር ዜጐች ጥቂት እንኳ ለየት ያለ አስተያየትና አያያዝ ማድረግ ለምን ተሳናቸው? ሲሰቃዩ የምንሰማው የእኛ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ የሌላው አገር ዜጋ የኛን ያህል በደል ሲደርስበት አላየንም! አልሰማንም!

ልዩ አስተያየት አድርገው እዚያው ሰርተው መኖራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ለምን አልቻሉም? የሳዑዲን ትልቁን ዩኒቨርሲቲ የሰሩት በሺዎች የሚቆጠሩ የጉልበት ሠራተኞች በህገ-ወጥ መንገድ የገቡ መሆናቸው ዛሬ ለምን ታያቸው? የዩኒቨርሲቲው ግንባታ ሲያልቅ የዜጐቻችንን ጉልበት ሙጥጥ አድርገው ከበሉ በኋላ ‹‹የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ናቸው›› ማለትን ምን አመጣው? ይህም ይሁን ብንል እንኳ እህል ውሃ በማያሰኝ ዱላና በሰደፍ በወታደር ጫማ እርግጫና በፖሊስ ጡጫና በጥይት ጭምር ሳይደበድቡ፣ አካላዊ ጉዳት ሳያደርሱና ህይወት ሳያረግፉ ወደአገራቸው ለመመለስ ለምን ፈቃደኛ አልሆኑም? ኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ምን አስፈለጋቸው? ከተመላሾች አንዱ ሲናገር እዚያው ሳዑዲ ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደሚፈልግበት ሌላ ቦታ ለመሄድ ታክሲ ውስጥ ሲገባ ባለታክሲው በቀጥታ ይዞት ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ ለፖሊሶች አሳልፎ ሲሰጠው ‹‹ይሄው አንድ ኢትዮጵያዊ ይዤላችሁ መጣሁ›› እያለ ብሄራዊ ግዳጁን እንደተወጣና ምርኮኛ ይዞ እንደመጣ ጀግና እየተኩራራ ነበር፡፡

የእኛና የሳዑዲ ግንኙነት በመኖሪያ ፈቃድ አለመያዝና በሕገ-ወጥ መንገድ ከመግባት ጋር ብቻ የሚያያዝ አይደለም፡፡ እንዲያውም ይሄ ሽፋን ብቻ እንጂ ምክንያት ሊሆን የሚችል አይመስለኝም፡፡ አሁን እዚያ ያሉት የእኛ ሰዎች ቁጥር አንዳንዶች እንደሚሉት ባይበዛም ቀላል አይሆንም። እነዚህን ሁሉ ዜጐች በማስወጣት ሰበብ ምናልባት የእኛ መንግሥት የማይፈልገውን የሃይማኖትና የሳዑዲ መንግሥት አቋም ለዜጐቹ ደህንነት ሲል ሳይወድ በግድ እንዲቀበል የመንግሥታችንን እጅ ለመጠምዘዝ የሚያደርጉት ፖለቲካዊ ሴራ ሊሆን ይችላል ብሎ መጠርጠር ሞኝነት አይደለም፡፡

የእኛ መንግሥት በዚህ የሳዑዲ ድርጊት ዙሪያና ውስጥ ከበስተፊትና ከበስተኋላ ያሉትን ችግሮች በሙሉ አሳምሮ እንደሚያውቅ አልጠራጠርም፡፡ የታላቁ የህዳሴ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሥራ ጅማሮ አካባቢ ግድቡን ከተቃወሙ አረቦች ዋናው የሳዑዲው የመከላከያ ም/ሚኒስትር የነበረ ነው፡፡ በማያገባው ገብቶ ግብጽ ድረስ ሄዶ ከራሱ አገርና የጦር ኃላፊነት ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ጉዳይ ላይ ቅስቀሳ ሲያደርግብን ነበር፡፡

የስደተኞቹ ኑሮ በሕገ-ወጥ መንገድ የተካሄደ ቢሆን እንኳ ከ1400 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ግንኙነታችን በጋራ ካዳበርነው ታሪክና ባህል አንፃር ሲታይ ይሄ ሁሉ መጉላላትና ጉዳት በኢትዮጵያውያን ላይ መድረስ የለበትም፡፡ ይህ ማለት ግን ‹‹ሕገ-ወጥነት›› መቀጠል አለበት ማለት አይደለም፡፡ ያለ አንዳች ጥርጥር ሕገ-ወጥነት መቆም አለበት፡፡ መንግሥት በሕገ-ወጥ አስተላላፊዎች ላይ ከፍተኛ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በአሁኑ ሁኔታ እንኳ ሲታይ በሕገ-ወጥ መንገድ የሄዱ ዜጐች የደረሰባቸውን ጉዳትና ሞት ትተን በህይወት ያሉትን ለመመለስ ብቻ 50 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል፡፡ ከስደተኛ ዜጐቻችን ቁጥር አንፃር ሲታይ ግን የብሩ መጠን በአራትና በአምስት እጥፍ ሊጨምር ይችላል፡፡

ይህ ወጪ የሚወጣው ለማን ነው? ስደተኞቹ ተጐድተው እንጂ ጥቅም አግኝተው አልመጡም፤ መንግሥት ከዜጐች ዝውውር ላይ በቀጥታ ያገኘው የሳንቲም ጥቅም የለም፡፡ ዋነኛው ተጠቃሚ ህገ-ወጥ ደላላው ነው፡፡ ሕገ-ወጥ ደላሎች የበሉትን እዳ ነው መንግሥት እየከፈለ ያለው፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ ሲታይ ሕገ-ወጥነት መቆም አለበት፡፡ ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ምንም እንኳን በዜጐቻችን ላይ የደረሰው የመከራና የግፍ ሥራ አንጀታችንን ያቃጠለ ቢሆንም የነገር አያያዙን ጫፍ ድረስ መወጠርና ማክረር አስፈላጊ አለመሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡

‹‹አረብ›› የተባለን ሁሉ በጅምላ እስከመጥላት ድረስ መሄድ ፍፁም ትክክል አይደለም። መንግሥትም በጉዳዩ ሰበብ ከተገቢው በላይ የሆነ እርምጃ እንዲወስድ እጁን መጠምዘዝ ተገቢ አይሆንም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ይህን የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግር የሳዑዲ አንዳንድ ኃላፊዎች በዜጐቻችን ላይ ያደረሱትን በደል) እንደ ፖለቲካ አጀንዳ የውስጥ ፍላጐት ማራመጃ ላለማድረግ መጠንቀቅ አለብን፡፡
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

1 comment:

Babey Zeleke said...

በኢትዮጲያ ውስጥ ሲኖሩ የነበሩት አረቦች "አረብ ይውጣ " የደረሰባቸውን ታሪክ ለመሆኑ ታውቀዋለህ ፡፡

Post a Comment