Sunday, November 24, 2013

ሕገወጥ ስደትን ለመከላከል የተጀመረው እርምጃ በሁሉም አቅጣጫ መጠናከር ይገባዋል

(Nov 24, 2013, (አዲስ አበባ))--የኢትዮጵያ መንግሥት በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን ዜጎች በአፋጣኝ ወደ አገራቸው ለማምጣት ርብርብ ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሏል። ችግሩ ከተከሠተ ጀምሮ ባደረገው ጥረት ከ3 ሺ 255 በላይ ስደተኞችን ወደ አገራቸው መመለስ ችሏል። በስደት ላይ ከሚገኙት መካከል በየዕለቱ በተለይም ለሕጻናትና ሴቶች ትኩረት በመስጠት ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ላይ ይገኛል። በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙትን እነዚህኑ ዜጎች በ12 ቀናት ውስጥ ወደ አገር ለመመለስ እንዲቻል ሌት ተቀን ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።

እነዚህ ዜጎቻችን ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም ሁኔታዎች እንዳይከብዷቸው ለጊዜው የሚያርፉበትን ቦታ ከማዘጋጀት ጀምሮ ድጋፍ እየተሠጣቸው ነው። በሰላም ወደ አገራቸው በመመለሳቸው እፎይታ እንዲሰማቸው እየተደረገም ነው። ይህም ዜጎች በታሰበው የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት ወሳኝነት እንዳለው ይታመናል።

በእርግጥ መንግሥት ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ የጀመረው ከሐምሌ 2005 ዓ.ም ጀምሮ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ እድል የተጠቀሙት ግን 329 ብቻ ናቸው። ይህም ዜጎች በወቅቱ የተፈጠረውን እድል ቢጠቀሙ ኖሮ አሁን ያጋጠመውን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ ያስችል ነበር።

መንግስት በሳዑዲ አረቢያ ያሉትን ዜጎች ችግር በአፋጣኝ ለመፍታት ርብርብ እያደረገም ጎንለጎን መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችለውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል። ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል መሰረተ ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው። በየክልሉ እስከታች ቀበሌ ድረስ በመውረድ የሚሰራው ሥራ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚደረገው እንቅስቃሴ መካከል ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል። የዜጎችን አመለካከት በመቀየር፣ ወጣቶች በተለይም ሴቶች በቀላሉ ተደልለው ወደ ተለያዩ አገሮች እንዳይሄዱ ለማድረግ የሚያስችል ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በህገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቆም ያስችላል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለመግታት የህዝቡን ተሳታፊነት ለማሳደግ፣ የህግ ክትትልን ለማጠናከርና የንቅናቄ ተግባራት ለመፈጸም የተቋቋመው አገር አቀፍ ብሔራዊ ምክር ቤት ትናንት ባደረገው ስብሰባ እንዳሳወቀው ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ጠንካራ ስራዎች ተሰርተዋል። ከነዚህም መካከል በህብረተሰቡ ዘንድ ቁጭት መፈጠሩ ትልቁ ጉዳይ ነው። በየክልሎችም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ብሎም ህገ ወጥ ደላሎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል። እንዲሁም ጥብቅ ቅጣት መውሰድ ተጀምሯል። በተለያየ ደረጃ ያሉ አደረጃጀቶችንም እንደ አንድ አማራጭ በመውሰድ መልካም ስራ እየተሰራ ነው። ይህ ውጤት እያሳየ የመጣውና በተግባር እየተዩ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን የበለጠ አጠናክሮ የመቀጠል ጉዳይ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።

ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለውን ትስስር በማጠናከርና በማስፋት ውጤታማ ሥራ መሥራት በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የአመራር አባላትን ትኩረት የሚሻ ነው። በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝም በሌሎች ተግባራትም የሥራ እድል ፈጠራው ላይ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። ወጣቶች በተማሩት ሙያም ሆነ በአዳዲስ የስራ ፈጠራ እየታገዙ ራሳቸውን ችለው ሊሎችንም እንዲያበረታቱ መሥራት ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት ያወጣው እገዳ ሲያበቃ ዜጎች ወደ ውጭ የመሄድ መብታቸው እንደሚጠበቅ ይታወቃል። ይህን አስመልክቶ አገር አቀፍ ምክር ቤቱ ዜጎች በቂ ሥልጠና የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ ነው የሚያመለክተው። የህግ ማስከበር ሥራዎችም መቀጠል እንዳለባቸው አጽንኦት መሰጠቱም ተገቢ ነው።

በመሰረቱ መንግስት እነዚህን ተግባራት በማከናወን ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ በሚያደርገው ትግል የእያንዳንዱ ዜጋ አስተዋጽኦ እጅግ አስፈለጊ ነው። በተለይም በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የራሳቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ግለሰቦችን ለህግ በማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ በመድረግ በኩል መረባረብ ያስፈልጋል። ዜጎች በአገራቸው የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ለመሳተፍ የሚያስችል እድል እንዳለ እንዲያስተውሉ እና የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ የማድረግ ስራ መስራት ይገባል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ራስን በመለወጥ የአገርን መልካም ገጽታ ሳይበላሽ ወጤታማ መሆን እንደሚቻል በተግባር የታጀበ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል። ይህ ተግባር ለመንግስት ብቻ የተተወ አይደለምና!!!
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment