Thursday, June 06, 2013

አየር መንገዱ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ ያሰለጠናቸውን የአውሮፕላን አብራሪዎችን አስመረቀ

(ግንቦት 29/2005, (አዲስ አበባ ))--የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነ መልቲ-ክሩ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ ያሰለጠናቸውን 26 የአውሮፕላን አብራሪዎችን ዛሬ አስመረቀ። በዓለም ላይ በጥቂት አገሮች ብቻ ተግባራዊ በተደረገው መልቲ-ክሩ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ አየር መንገዱ ካሰለጠናቸው ባለሙያዎች መካከል አንዷ ሴት ናት።

እንዲሁም 68 የአውሮፕላን በረራ አስተናጋጆችን አስመርቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ለአቬሽን ስልጠና ሐብት በማፍሰስ ለበረራ ሙያ ብቁ ክህሎትና ዕውቀት ያላቸውን ባለሙያዎች በማፍራቷ ለአየር መንገዱ ስኬታማነት ዘወትር የጀርባ አጥንት ነው።

"አየር መንገዱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2025 ላስቀመጠው ፈጣን፣ ትርፋማና ዘላቂ ዕድገት ግብ ስኬታማነት በአፍሪካ የመጀመሪያ በሆነ መልቲ-ክሩ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ የሰለጠኑት ባለሙያዎች መሠረት የሚጥሉ ናቸው"

ብለዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ ላስገነባው የአቬሽን ስልጠኛ ማዕከል ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ50 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል። ማሰልጠኛ ማዕከሉ የአውፕላን አብራሪዎችንና የበረራ አስተናጋጆችን በማሰልጠን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን በዘርፉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በአፍሪካ አገሮች የሚታየውን የሙያተኛ እጥረት ማቃለል ጭምር እንደሆነም ጠቁመዋል።

ማዕከሉ የአቬሽን ባለሙያዎችን የማሰልጠን አቅሙን በማሳደግ በየዓመቱ አራት ሺህ ብቁ ባለሙያዎች እንዲያፈራ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በአዲሱ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ የሰለጠነችው ካፒቴን ሰላም ተስፋዬ በበኩሏ የአየር መንገዱን ራዕይ ለማሳካትና በአፍሪካ ያለውን የቀዳሚነት ደረጃ ይዞ እንዲጓዝ ተመራቂዎች ባላቸው እውቀትና ክህሎት የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብላለች።

በዛሬው ዕለት በመልቲ-ክሩ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ የሰለጠኑት የአውሮፕላን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች በጨዋ ሥነ-ምግባርና ትጋት አገራቸውን ለማገልገል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል። በትምህርታቸው ብልጫ ያገኙ ተመራቂዎች ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እጅ ዋንጫና ሰርተፊኬት ተቀብለዋል። መልቲ-ክሩ የአውሮፕላን በረራ ፈቃድ ሙያ አንድን አውሮፕላን ሁለት አብራሪዎች ማብረር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ነው።
ምንጭ:  ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት

2 comments:

Anonymous said...

i am proud of being Ethiopian

Anonymous said...

Ehiopia i am proud of ya!

Post a Comment