Wednesday, June 12, 2013

ኢትዮጵያ በቀረርቶ ተደናግጣ ግንባታውን ለሰኮንድም አታቆምም- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

(ሰኔ 04/2005, (አዲስ አበባ))--የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል” በሚል ርዕስ ዛሬ ሰኔ 04/2005 ባወጣው መግለጫ የታላቁን ሕዳሴ ግድብ በሚመለከት የግብፅ ባለስልጣናት፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የሲቪል ሶሳይቲ ሃላፊዎች ሲያካሂዱት የከረሙትን አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ በሚመለከት ሚኒስቴሩ ከአሁን በፊት ማለትም ግንቦት 28/2005 መግለጫ መስጠቱን ያወሳል፡፡

በወቅቱ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ ያላትን ገንቢ አቋም ገልፃ ነገር ግን በግብፅ በኩል ያለውን አቋም በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደርን ከአንዴም ሁለቴ ጠርታ መጠየቋና ለግብፅ መንግስትም ጥያቄ ማቅረቧ ተገልጧል፡፡ ኢትዮጵያ ከምንም በላይ ለትብብር፤ ለወዳጅነትና ለጋራ ጥቅም ያላትን ፅኑ እምነት በዚሁ መግለጫ ግልፅ አድርጋ ነበር ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡

ይህ በንዲህ እንዳለ ሰኔ 3/2005 ብሔራዊ የናይል ኮንፈረንስ በተሰኘው ስብሰባ የግብፅ ፕሬዝዳንት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሚኒስትሮችና ሌሎችም በተገኙበት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ አፍራሽ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡፡

ከነዚህም መካከል የሕዳሴው ግድብ በግብፅ ላይ አደጋ የደቀነ በመሆኑ በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ተፅዕኖ የማሳረፍና የግድቡን ግንባታ እንድታቆም የማድረግ እንቅስቃሴ ስለማድረግ፤ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ፍላጎትና አድራጎት ውጭ እንደዚሁም የሕዳሴ ግድቡን እንዲያጠና ግብፅ ጭምር ያለችበት አለም አቀፍ የኤክስፐርቶች ቡድን ያቀረበውን ዘገባ ጭምር የሚያጣጥሉ ፀብ አጫሪ አስተያየቶች በመድረኩ ሲስተናገዱ ተስተውለዋል፡፡

በዚህ ረገድ በግብፅም ሆነ በሌላ ማንኛውም ወገን የሚቀርብ የግድቡን ግንባታ የማዘግየት ወይንም ከነአካቴው የማቋረጥ ነገር ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፤ በሕዳሴው ግድብ ሽፋን የውስጥ ችግርን ለማቃለል የሚደረገው ጥረትም የግብፅን ዘላቂ ጥቅም አይጠብቅም ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፡፡

ጦርነትና ሌሎች አፍራሽ ስልቶችን ስለመጠቀም የሚቀርቡት ሃሳቦች ያረጁና ያፈጁ፤ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚጠይቀውን የዘመነ አስተሳሰብ የማይሸከሙ ጤናማ ያልሆኑ አስተሳሰቦች ሲሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ ቀረርቶ ተደናግጣ ግንባታውን ለሰኮንድም እንደማታቆም ታረጋግጣለች ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡

የግብፅ ወገንም ከዚህ አፍራሽ ድርጊት ተቆጥቦ ለሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት መጠናከር የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትር የሕዳሴውን ግድብ ጠቀሜታ አስመልክተው ያሰሙት ሃሳብ ገንቢ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል ያለው መግለጫው ሌሎችም ከዚህ የሚቀስሙት ትምህርት እንዳለ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ይህ ግድብ ግብፅን ጭምር የሚጠቅም መሆኑን እንደገና እያሳሰበች ከግብፅ ጋር በወዳጅነት በትብብር ለመስራት ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ትገልፃለች ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ፅ/ቤት ለኢሬቴድ የላከው መግለጫ፡፡
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

Related topics: 
የግብፅ መሪዎች ካላበዱ በስተቀር ወደ ጦርነት አይገቡም- ጠ/ሚ ኃይለማርያም  
የታላቁ የኢትዬዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ  የታላቁ የኢትዬዽያ ህዳሴ ግድብ የዓለም አቀፍ የባለሙያወች ቡድን ባቀረበው ሪፖርት ላይ ከዉሃና ኢነርጂ የተሰጠ መግለጫ
የአዲስ አበባ የባቡር ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው 
የህዳሴው ግድብ በግብፅና ሱዳን አሉታዊ ተፅእኖ እንደማያስከትል ዳግም ያረጋገጠ ሪፖርት  
የህዳሴው ግድብ - የግብጽ መገናኛ ብዙሃንና ፖለቲከኞች  

No comments:

Post a Comment