(Apr 16, 2013, አዲሰ
አበባ))--በሳምንቱ መጨረሻ በኦስትሪያ ፣ በደብሊንና በሮተርዳም በተካሄዱ የግማሽ ማራቶን፣ የአስር ኪሎ ሜትርና የማራቶን ውድድሮች በቅደም ተከተል ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ጥላሁን ረጋሳ አሸናፊ ሆነዋል። የረጅም ርቀት ንጉሡ ኃይሌ ገብረሥላሴ በኦስትሪያ ቪየና የተካሄደውን የግማሽ ማራቶን ውድድር አሸንፏል። ኃይሌ ውድድሩን በተከታታይ በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ የእሁዱ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ ርቀቱን በአንድ ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከ14 ሰከንድ በሆነ ጊዜ ውስጥ በመግባት ነው አሸናፊ ሆኗል።
በሚቀጥለው ሣምንት አርባኛ የልደት በዓሉን የሚያከብረውና በአስር ሺ ሜትር ሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ኃይሌ ከውድድሩ አጋማሽ ጀምሮ በመምራት አሸናፊ ሊሆን መቻሉን ነው ዘገባዎች ያመለከቱት። በአውሮፓውያኑ 2013 ለመጀመሪያ ጊዜ የተወዳደረው ኃይሌ ኬንያዊውን ሆሴ ኪፕኬምቦይንና የአገሩን ልጅ መኳንንት አያሌውን አስከትሎ ነው ያሸነፈው። በውድድሩ ሁለተኛ የወጣው ኬንያዊው ኪፕኬምቦይ ርቀቱን በአንድ ሰዓት ከሁለት ደቂቃ ከ01 ሰከንድ ያጠናቀቀ ሲሆን፥ ኢትዮጵያዊው መኳንንት በ21 ሰከንዶች ዘግይቶ በመግባት ሦስተኛ መሆኑን የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ድረ ገጽ ዘግቧል።
ኃይሌ ከውድድሩ ፍፃሜ በኋላ በሰጠው አስተያየት «አነሳሴ ላይ ዘግይቼ ሊሆን ይችላል፤ ያሰብኩትን ያህል ፈጥኜ አልሮጥኩም፤ አሁንም ከዛሬው የተሻለ ፈጥኜ መሮጥ እንደምችል አምናለሁ » ብሏል። በዕለቱ በከተማዋ በተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች 41ሺ 326 አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ 10ሺ 588ቱ የማራቶን ተወዳዳሪዎች ነበሩ።
በእዚያው በቪየና በተካሄደው ዓመታዊ የማራቶን ውድድር በወንዶች ኬንያዊው ሄንሪ ሱጉት ለሦስተኛ ጊዜ ባለድል ሆኗል። እስከ አምስተኛ ያሉትን ደረጃዎችንም ኬንያውያን በበላይነት የተቆጣጠሩት ሲሆን ኢትዮጵያዊው ኤዴኦ ማሞ ስድስተኛ ሆኖ ውድድሩን አጠናቅቋል።
በሴቶች ተመሳሳይ ውድድርም ኬንያዊቷ ፍሎሜና ቼይች ቀዳሚ ስትሆን፤ ከውድድሩ በፊት የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ መስከረም አሰፋና እየሩሳሌም ኩማ ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥተዋል።
በአየርላንድ ደብሊን ከተማ በተካሄደው የታላቁ የአየርላንድ የአስር ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር በተደጋጋሚ ጉዳት ከውድድሮች ርቆ የቆየው ቀነኒሳ በቀለ አሸናፊ ሲሆን፤ ኢብራሂም ጄይላን ሦስተኛ ወጥቷል። የበርካታ ክብረ ወሰኖች ባለቤት የሆነው ቀነኒሳ በቀለ ውድድሩን በአሸናፊነት ያጠናቀቀው ምርጥ ብቃት በማሳየት ጭምር መሆኑን ነው ዘገባው ያስነበበው።
በአየርላንድ በተካሄዱ ውድድሮች ላይ አንድም ጊዜ ተሸንፎ የማያውቀው አትሌት ቀነኒሳ ውድድሩን በቀዳሚነት ያጠናቀቀው 28 ደቂቃ ከ51 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ነው። ቀነኒሳን ተከትሎ ዩክሬናዊው ሰርጌይ ሌቢድ በ29 ደቂቃ ከ08 ሰከንድ ሁለተኛ ሲወጣ፤ በደቡብ ኮሪያ ዴጉ ከተማ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በአስር ሺ ሜትር ለኢትዮጵያ የወር ቅ ሜዳሊያ ያስ ገኘው ኢብራሂም ጄይላን ሦስተኛ ወጥቷል። ኢብራሂም ርቀቱን ለማጠ ናቀቅ 29 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ የሆነ ሰዓት ወስዶበታል።
ያለፈውን ዓመት ተመሳሳይ ውድድር በ27 ደቂቃ ከ49 ሰከንድ በአሸናፊነት ያጠናቀቀው አትሌት ቀነኒሳ በአው ሮፓውያኑ 2002 በአየርላንድ በተካሄደው በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በሁለት ርቀቶች ተወዳድሮ የድ ርብ ድል ባለቤት መሆን መቻሉ ይታወሳል።
የአምስትና አስር ሺ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ቀነኒሳ በለንደኑ ኦሊምፒክ አራተኛ ቢወጣም በውድድሩ ወደ ቀድሞ ብቃቱ በመመለስ ላይ እንደሚገኝ አሳይቷል። ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት «በውድድሩ ባሳየሁት ብቃት ተደስቻለሁ። አሁን ቀስ በቀስ እየተሻሻልኩ ነው ። ይህ ዓመት ለእኔ መልካም ይሆንልኛል። በሁሉም ሻምፒዮናዎች የተሻለ ነገር አደርጋለሁ » ሲል ተናግሯል።
በተያያዘ ዜና በሮተርዳም በተካሄደ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ጥላሁን ረጋሳ ርቀቱን ሁለት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ከ38 ሰከንድ በመሮጥ አሸናፊ ሲሆን፤ ጌቱ ፈለቀ ሁለተኛ ወጥቷል። የውድድሩ አዘጋጆች በሁለት ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ የሆነው የሥፍራው ክብረ ወሰን ይሻሻላል የሚል ግምት የነበራቸው ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል። የሮተርዳም ማራቶን አዘጋጆች ሁለት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ የግላቸው ምርጥ ሰዓት ያስመዘገቡ በርካታ አትሌቶችን ቢያሳትፉም በሥፍራው የነበረው ሙቀት የስፍራው ክብረ ወሰን እንዳይሻሻል እንቅፋት ሆኗል።
አትሌቱ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት «ሰዓቱ የተጠበቀውን ያህል ፈጣን ባይሆንም በተገኘው ድል ደስተኛ ነኝ። አየሩ በፍጥነት የሚቀያየር መሆኑ ውድድሩን አስቸጋሪ አድርጎታል» ብሏል። የአገሩ ልጅ ጌቱ ፈለቀ በአንድ ደቂቃ ዘግይቶ በመግባት ሁለተኛ ሆኗል። አትሌት ጌቱ በሮተርዳም ማራቶን ሁለተኛ ሲወጣ ሁለተኛ ጊዜው ነው።
በሥፍራው በሴቶች መካከል በተካሄደ ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አበበች አፈወርቅ ኬንያዊቷ ጀሚማ ጄላጋትን ተከትላ ሁለተኛ ወጥታለች። ሰሜን ኮሪያ ዋና ከተማ ፒዮንግያንግ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ከተማ በቀለ በአሸናፊነት አጠናቅቋል። ከተማ ርቀቱን ሮጦ ለመጨረስ 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ03 ሰከንድ ወስዶበታል።
በሌላ ዜና ደቡብ ኮሪያ ዴጉ ውስጥ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ደበበ ቶሎሳ ርቀቱን 2 ሰዓት ከአስር ደቂቃ ከ23 ሰከንድ በሆነ ጊዜ አጠናቅቆ ሦስተኛ ደረጃን አግኝቷል። ውድድሩን በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ፈረንሳዊ የሆነው አብርሃም ኪፕሮቲች ሲያሸንፍ ኬንያዊው ቦኒፌስ ቩቢ ሁለተኛ ሆኗል።
በሴቶቹ የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ሙሉ ሰቦቃ ርቀቱን በ 2ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ43 ሰከንድ በማጠናቀቅ ሁለተኛ ወጥታ አጠናቅቃለች። ውድድሩን ኬንያዊቷ ማርጋሬት አካዪ አሸንፋለች።
ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment