Wednesday, June 12, 2013

የግብፅ መሪዎች ካላበዱ በስተቀር ወደ ጦርነት አይገቡም- ጠ/ሚ ኃይለማርያም

(June 11, 2013, (አዲስ አበባ))--ኢትዮጵያ የታላቁ የሕዳሴ ግድብን ግንባታ ይፋ ካደረገችበት ግዜ ጀምሮ የጋራ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ አቋም ይዛ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተግባርም ይህንኑ የሚያንፀባርቅ እርምጃ እየወሰደች መቆየቷን ገልፀዋል፡፡

የግድቡን ግንባታ በተመለከተ በተለይ በኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ግብፅ መካከል የመተማመን ስሜት እንዲፈጠር ከሶስቱም ሃገራት ሁለት ሁለት ተወካዮች የተሳተፉበት 10 አባላት ያሉት የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ጥናት እንዲካሄድ ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡

የጥናቱ ውጤትም ግድቡ ሶስቱንም ሃገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከኢ.ሬ.ቴ.ድ ጋር ባደረጉት ቆይታ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የፀረ ድህነት ትግላችን አካል በመሆኑ ማንም ሊያሰቆመው አይችልምም ብለዋል፡፡ “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የድህነት ትግላችንን የሚደግፍ ፕሮጀክት ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በመሆኑ የሚያሰቆመው አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡”

የግብፅ መሪዎች የግድቡን ግንባታ ለማስቆም ማናቸውንም አማራጭ እንጠቀማለን ማለታቸው የውስጥ ችግራቸውን የትኩረት አቅጣጫ ወደሌላ ለማዞር ያለመ ነው ብለውታል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡ በመሆኑም ግብፅ የታላቁን የሕዳሴ ግድብ በተመለከተ የያዘቸውን ተገቢ ያልሆነ አቋም መልሳ እንድታጤነው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳስበዋል፡፡ “በውስጥ ጉዳያቸው የተወጠሩ የግብፅ መሪዎች በመሆናቸው አጀንዳ ለማሰቀየር የአባይን ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ ማጋጋል መፍትሄ አድርገው የወሰዱ ነው የሚመለስለኝ፡፡”

የግብፅ መሪዎች ካላበዱ በስተቀር ወደጦርነት ይገባሉ የሚል ግምት የለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ይህን የማይጠቅም አቋም ወደጎን ትተው ለጋራ ተጠቃሚነት ተባብረው እንዲሰሩ መክረዋል፡፡

“ወደድርድርና ወደ ጋራ መድረክ መምጣት ነው የሚጠቅመው ብለን እናምናለን፡፡ የአባይ ጉዳይ የውስጥ ችግራቸውን ማቃለያ አድርገው መውሰድና መቀበል ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡” የሱዳን ህዝብና መንግስት ከመጀመሪያው ጀምር የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ ሲደግፉ መቆየታቸውን ያስታወሱት  አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በፅ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሯቸው የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይህንኑ ዳግም እንዳረጋገጡላቸው አብራርተዋል፡፡

“ሱዳኖች ይህ ግድብ መሰራቱ ሁላችንንም ይጠቅማል የሚል ቋሚና ፅኑ አቋም ነው ያላቸው፡፡ ሚኒስትሩም ይህንኑ ነው የገለፁልኝ፡፡ የጀመርነውን ሁሉ በጋራ ለማስቀጠልና ግድቡ ለሁላችን ይጠቅማል የሚል አቋማቸውን በፅኑ ሁኔታ እየገለፁ ነው ያሉት:: በዚህ አጋጣሚ የሱዳን ህዝብና መንግስትን በከፍተኛ ደረጃ አመሰግናለሁ፡፡”

ኢትዮጵያ ወደፊትም ለጋራ ተጠቃሚነት ትኩረት ሰጥቶ መስራት ፅኑ አቋሟ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አረጋግጠዋል፡፡
ምንጭ፡ ኢሬቴድ

Related topics: 
የታላቁ የኢትዬዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ 
የታላቁ የኢትዬዽያ ህዳሴ ግድብ የዓለም አቀፍ የባለሙያወች ቡድን ባቀረበው ሪፖርት ላይ ከዉሃና ኢነርጂ የተሰጠ መግለጫ
የአዲስ አበባ የባቡር ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እየፈጠረ ነው 
የህዳሴው ግድብ በግብፅና ሱዳን አሉታዊ ተፅእኖ እንደማያስከትል ዳግም ያረጋገጠ ሪፖርት  

የህዳሴው ግድብ - የግብጽ መገናኛ ብዙሃንና ፖለቲከኞች  

No comments:

Post a Comment