Thursday, June 13, 2013

ታላቁ የህዳሴ ግድብ መቼም ቢሆን አይደናቀፍም!

(June 12, 2013, (አዲስ አበባ))--የውሃ ማማ የምትሰኘው አገራችን  የከርሰ ምድርና ገፀ ምድር ውሃ ባለፀጋ ነች።  በተለይ በጋ ከክረምት የሚፈሱ ወንዞችን በልዩ ልዩ  ምክንያት አልምቶ ለመጠቀም ባለመቻላችን ግን ውሃ ላይ እየኖርን ስንራብ ቆይተናል። ጨለማን በኩራዝ ብቻ ድል እንድንነሳም ተደርገን ከመቶ ዓመት በላይ አስቆጥረናል።

ተፈጥሮ ያደለችንን እምቅ የውሃ ሀብት ባለመጠቀማችን ሕዝባችን በተለያዩ ጊዜያት በረሃብ አለንጋ ሲመታ አንዳንዶቹ «የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው» በማለት ተሳልቀውብናል። በተለይም አባይንና ገባሮቹን ገድበን ለመስኖ ልማትና ለኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት እንዳንጠቀም ባልተስማማንበትና  ፈጽሞ  ተቀባይነት በሌለው ሕገወጥ ድንጋጌ  «አባይን ብትነኩ 'ወዮላችሁ'» እየተባልን የበይ ተመልካች በመሆን ዘመናትን አስቆጥረናል።

በተለይም ግብፅ «አለኝ» በምትለውና አዲሲቷ ኢትዮጵያ በማታውቀውና ፍትሐዊነትና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጠው  ውል ሀገራችን  በአባይ ወንዝና በገባሮቹ ላይ ፕሮጀክት ስትወጥንም ሆነ እውን ለማድረግ ስትንቀሳቀስ በእንቅፋትነት  መሰለፍ የረዥም ዘመን ታሪኳ ነው።  ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እንኳ የአባይ ተፋሰስ አገሮች አባይን ፍትሐዊነት በሰፈነበት ሁኔታ አልምተው ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ፈጥረው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ ቅኝ ገዥዎች ለክተው በሰጧት ኢ-ፍትሐዊ ውል ዛሬም እንደትናንቱ ሁሉንም የተፋሰሱ አገሮች እግር ከወርች ለማሠር መከጀሏ  አልቀረም፡፡

ይህ ዓይነቱ አጉራ ዘለል አካሄድ ደግሞ ጊዜ ያለፈበትና የተፋሰሱ አገሮችም የማይቀበሉት መሆኑን ለዓመታት  በዘለቀ ስምምነታቸውና  በፊርማቸው ማረጋገጥ ችለዋል።  ይህንኑ የቃል ኪዳን ሰነድ  የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብና መንግሥታት እንዲያውቁት ማድረጋቸውም  የሚታወቅ ነው። የናይል ተፋሰስ አገሮች የስምምነታቸው ዋልታና ማገር ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች የሚመሩበት ዓለም አቀፍ ሕግ የመሆኑን ያህል የታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ለፍትሐዊ አሠራር እጃቸውን ቢሰጡ ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ አለመሆናቸውን ሊገነዘቡ በተገባቸው ነበር።

በእዚህ ረገድ ከሰማንያ ስድስት በመቶ በላይ የአባይ ወንዝ መነሻ የሆነችው አገራችን አባይን የመጠቀም መብቷን ማንም ሊሰጣት፣ ማንም ሊነፍጋት እንደማይችል በጽኑ በማመን እነሆ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጀመረች ሁለት ዓመት አስቆጥራለች።  በግድብ ሥራ እንደሚደረገው ሁሉ አባይ ለዘመናት ይፈስበት ከነበረው ፈለጉ ለቆ በተቀየሰለት መንገድ እንዲፈስም ተደርጓል። ከግድቡ ግንባታ በፊት መከናወን ያለባቸው ወሳኝ ቅድመ ዝግጅቶችም ተጠናቅቀዋል።

ይሁን እንጂ የግድቡ ግንባታ እዚህ ምዕራፍ ላይ መድረሱና በተለይም የወንዙን መቀልበስ ከሰሙበት ጊዜ ጀምሮ ለግብጽ ኅብረተሰብ ሳይቀር የጋራ ተጠቃሚነት አቋም ባልነበራቸው ዛሬም የሌላቸው ኃይሎች የተሳሳቱ አደገኛ የትግል ስልቶችን ለማራመድ ያላቸውን አሳፋሪ አቋም ሲገልጹ ተስተውለዋል። በኢትዮጵያ ተነሳሽነት ተዋቅሮ ሥራውን ያጠናቀቀው የሦስትዮሽ  የባለሙያዎች ፓነል  ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማያስከትል የአወጣውን ሪፖርት ሳይቀር እንደልማዳቸው ሊቀበሉት አልደፈሩም።

ያም ሆነ ይህ የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከትናንት በስቲያ እንዳረጋገጠው ግብጽ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማዘግየትና ከነአካቴውም ለማቋረጥ ጦርነትና ሌሎች አፍራሽ ስልቶችን እንደምትጠቀም በምታቀርባቸው አፍራሽ አስተሳሰቦችና ቀረርቶዎች በመደናገጥ ግንባታው ለሰኮንድም እንኳ እንደማይቆም ይፋ አድርጓል።  ይልቁንም የግብጽ ባለሥልጣናት መሠረተ ቢስና ጠብ አጫሪ አስተሳሰባቸውን በመተው በግድቡ የጋራ ተጠቃሚነትና ለሁለቱ አገሮች ወዳጅነት በመጠበብ ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን ሥልጡን አስተሳሰብ ሊሻገሩ እንደሚገባም መክሯል።

«... ኢትዮጵያ በራሷ ጥረትና በልማት አጋሮቿ ድጋፍ ድህነትን በአፋጣኝ እያሸነፈች በእድገት ጎዳና መረማመድ ከመጀመሯ በፊት በቆየው ድህነታችን ምክንያት በወንዞቻችን የመጠቀም መብታችን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በእጅጉ ተገድቦ ቆይቷል። ይሁንና እድሜ ለታታሪው ሕዝባችን ያን ዘመን በአስተማማኝ አኳኋን ተሻግረን ታላቁን የልማት ህልማችንን በህዳሴ ግድባችን አማካይነት እውን የምናደርግበት አዲስ ዘመን ተበስሯል። ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲያ በመብታችን እንዳንጠቀም የሚገታን ምንም ነገር አይኖርም። 

ዛሬ በአባይ ወንዝ ላይ ሊገነባ የሚችለውን ትልቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በማስጀመር የቆየውን ማነቆ ስንሰብር ... በመብታችን ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጐቱ ብቻ ሳይሆን አቅሙም እንዳለ ነው» በማለት ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ እንዳረጋገጡት ሁሉ በግብፅ መሠረተ ቢስ ፕሮፓጋንዳ በእዚህ ትውልድ ባለቤትነት እየተገነባ ያለውን ፕሮጀክት ዳር አድርሶ ለተጠቃሚነት ከመብቃት ወደኋላ እንደማይል ሕዝቡና መንግሥት በአንድ  ጽኑ አቋም  ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን በአገር ጉዳይ ያውም ለህዳሴው ግድብ ከምንም በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ሊታወቅ ይገባል። በአገር ጉዳይ በጋራ ቆሞ አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈል ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጎረቤት ሕዝቦች በጋራ እንዲጠቀሙ በሰላም እንዲኖር ከመመኘትና ከመምከርም ቦዝነው አያውቁም። ይሄን አኩሪ ታሪክ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment