Thursday, June 13, 2013

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀን እየወጣለት ነው

(June 12, 2013, (አዲስ አበባ))--ዋልያዎቹ በራሳቸውም ሆነ በተጋጣሚዎቻቸው ሜዳዎች ማሸነፍ እየቻሉና የአገሪቱ እግር ኳስ እያደገ መሆኑን እያስመሰከሩ መጥተዋል፤ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አገሪቱ ከመሠረተችው የአፍሪካ ዋንጫ ተፎካካሪነት ከራቀችና የሩቅ ተመልካች ከሆነች ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ መሳተፉን እንዲሁም የአገሪቱ አንጋፋ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ያሳየውን ተፎካካሪነትን ተከትሎ በርካታ የስፖርቱ ጸሐፍት «ኢትዮጵያ የእግር ኳስ የበላይነቷን እያስመለሰች ነው» ማለት ጀምረዋል ።

ጸሐፍቱ እንዲህ ማለት ከጀመሩ የሰነባበቱ ቢሆንም፣ ዋሊያዎቹ ባለፈው ቅዳሜ ቦትስዋናን በሜዳዋ ላይ ሁለት ለአንድ ከረቱና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው የምድብ መሪነታቸውን ያስጠበቀ ውጤት ካስመዘገቡ በኋላ አጠናክረው ቀጥለዋል።

ይህንን ሐሳብ ከሚጋሩት መካከል ኢኬና አጉ የተሰኘው ጸሐፊ ይገኝበታል። ጸሐፊው ዋሊያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ምድባቸውን መምራት መቻላቸው የአገሪቱ እግር ኳስ መነቃቃት እያሳየ እንደሚገኝና ኢትዮጵያም ወደፊት በስፖርቱ ብርቱ ተፎካካሪ አገር እንደምትሆን አመላካች መሆኑን ጽፏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሶማሊያውን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ሳይጨምር አራት ጨዋታዎች አድርጎ አንድም አለመሸነፉ ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዋሃደና ጥንካሬ እያገኘ በመሄድ ላይ እንደሚገኝም ጸሐፊው ጠቁሟል።

ዋሊያዎቹ ምድብ አንድን በአስር ነጥብ ከደቡብ አፍሪካ በሁለት ነጥቦች በልጠው ከአናት መቀመጥ መቻላቸውና ደቡብ አፍሪካን በአዲስ አበባ የሚያስተናግዱ መሆናቸው ከምድቡ የማለፍ ከፍተኛ እድል በመያዝ ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል ሲልም በጽሑፉ አስነብቧል። «ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኗ ለዓለም ዋንጫ አልፎ ባያውቅም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2014 ላይ በብራዚል የሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ይህን የቆየ ታሪክ የሚቀየርበት እንዲሆን ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ይመስላልም » ብሏል ኢኬና አጉ።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራቿና የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም ዋንጫውን ያዘጋጀችና ያሸነፈችዋ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ በስፖርቱ ከነበራት ስፍራ ቀስ በቀስ እየተንሸራተተች ሄዳ ደካማ ከሚባሉ አገሮች ተርታ መመደቧን ጸሐፊው አስታውሶ፣ «የ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ የአገሪቱ እግር ኳስ እያንሰራራ ለመምጣቱ ግልጽ ማሳያና አገሪቱ በአህጉሪቱ የነበራትን ስፍራ ለመመለስ በሂደት ላይ መሆኗን አመላካች ሆኗል» ብሏል።

ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ ማጣሪያው ማለፍ ባይችልም እንኳን ነገሮች በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ እንደሚገኙ አመላካች እንደነበሩ ያመለከተው ጸሐፊው፣ ከዚያ በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የምድብ ድልድል ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መግባቱና ዋሊያዎቹ በአራት ጨዋታዎች ባገኟቸው አስር ነጥቦች ምድብ አንድን መምራት መቻላቸውን በማሳያነት በጽሑፉ ጠቅሷል።    

የኢኤስፒኤን ጸሐፊው ፍርዶስ ሙንዳም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ ከጻፉት መካከል አንዱ ነው። ጸሐፊው ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 1962 የአፍሪካ ዋንጫ ብታነሳም እስካሁን በአህጉራዊ ውድድሮች ምድብ ድልድል ውስጥ የገባ አንድም ክለብ እንዳልነበራት ያስታውስና ኤሲ ሌኦፓርድ የተባለው ክለብ የኮንጎን እግር ኳስ እንዳነቃቃ ሁሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅርቡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስመዘገበው ውጤት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ከፍተኛ አዎንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ግምቱን አስፍሯል።

 ከዚሁ ጋር አያይዞ ብሔራዊ ቡድኗ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በማሳየት ላይ የሚገኘው አስደናቂ ብቃትና ውጤታማነት የአገሪቷን የእግር ኳስ ስፖርት አፍቃሪ እጅጉን ማርካቱን ጠቁሟል። ዋሊያዎቹ በሚቀጥለው እሁድ ከባፋናባፋናዎች ጋር አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉትን ጨዋታ በበላይነት የሚያጠናቅቁ ከሆነ ሕዝቡ የሚኖረው ደስታ ባለፈው ጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም ሱዳንን በማሸነፍ ከ31 ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉን ያረጋገጠበት እለት ካሳየው በእጅጉ የተለየ ሊሆን እንደሚችል ገምቷል።

«ዴይታይምስዶትኮምዶትኤንጂ » የተሰኘው ድረ ገጽም በተመሳሳይ  « የአፍሪካ የእግር ኳስ ኃያልነት ቀስ በቀስ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰ ነው » ሲል ጽፏል። ድረ ገጹ ለማሳያነትም የቅዱስ ጊዮርጊስንና ዋሊያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በማስመዝገብ ላይ የሚገኙትን ውጤት ጠቅሶ፤ የአገሪቱ ውጤት በአጭር ጊዜ ከአህጉሪቱ ኃያል ከሚባሉት ተርታ ሊሰለፍ እንደሚችል ገልጿል።

ዋሊያዎቹ በማስመዝገብ ላይ የሚገኙት ውጤት የአገሪቱ እግር ኳስ ስፖርት መነቃቃትና በአፍሪካም ደረጃ ወደፊት ከፍተኛ ተወዳዳሪ እንደሚሆን ማሳያ ሆኖ በብዙዎች ዘንድ ተወስዷል። ይህንን ተከትሎም በቀጣይነት ከዋሊያዎቹ ጋር በአዲስ አበባ ላይ ጨዋታ የሚያደርጉትን የደቡብ አፍሪካን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ጎርደን ኢግሰንድንና የቀድሞ የቡድኑን አባላት አስግቷል። ባፋናባፋናዎች በዓለም ዋንጫው ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከዋሊያዎቹ ጋር አድርገው ሳላዲን ሰኢድ ባስቆጠራት ግብ ሲመሩ ከቆዩ በኋላ አቻ ለ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል። የባፋናባፋናዎች አሠልጣኝ  ጎርደን ኢግሰንድ ባለፈው ቅዳሜ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ካሜሩን ላይ ከመጫወታቸው በፊት ብዙ የሚያሳስባቸው አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእርሳቸው በተጨማሪ የቀድሞው የቡድኑ አምበል ሉካስ ራዴቤ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው ለመሳተፍ በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ተፎካካሪ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሆነ አስተያየቱን ሰጥቷል። ባፋናባፋናዎች አዲስ አበባ ላይ የሚያደርጉት ጨዋታ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆንባቸውም ግምቱን ከሰጠ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማድረግ ላይ የሚገኘው መሻሻል እንዳስደነቀው ተናግሯል።

በበርካታ የእግር ኳስ ስፖርት ተንታኞችና ጸሐፍት ዘንድ አድናቆትንና ሙገሳን በማግኘት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው መመራት ከጀመረ በኋላ በሥነልቡና፣ በቴክኒክና በታክቲክ ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱ እውነት ነው። ይህንንም አገሪቱን በስፖርቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደመነሻ መውሰድና መሥራት ይጠበቃል።
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

1 comment:

Anonymous said...

ARIF NEW SEWENET BERTU....

Post a Comment