Thursday, June 13, 2013

ግብፅ ሆይ!የህዳሴው ግድብ ተጠቃሚነትሽን ያስድጋልና አቋምሽን ፈትሺ!

(June 12, 2013, (አዲስ አበባ))--ልማቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው፡፡ አባይ ለልማት መስገር ከጀመረም ከሁለት ዓመት በላይ ዕድሜ አስቆጠረ፡፡ ታላቁ ወንዝ  ለእናት አገሩ ባዳ ከመሆን አባዜ ተላቅቆ የብርሃን ምንጭ በመሆን ኢትዮጵያን ሊክሳት ደፋ ቀና ማለቱን ተያይዞታል፡፡ ድንፋታሙ አባይ አሁን ፀባይ ገዝቷል፡፡

ለያዥ ገላጋይ ማስቸገሩን ትቶ ልማቱ እንዲፋጠን ታዛዥ ሆኗል፡፡ በእዚህም ከባባድ የግንባታ መሣሪያዎችና ሠራተኞች በአባይ ላይ የጀመሩትን ልማታዊ ዘመቻ አጠናክረው ገፍተውበታል፡፡ የህዳሴው ግድብ የልማት ሠራዊቶች ግዳጃቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው፡፡ ሙሉ ትኩረታቸውን የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት መወጣት ላይ ካደረጉም ከአንድ ሺ ቀናት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ የሕዝቡ ድጋፍም አልተለየም፡፡ የግድቡን ዕውን መሆን በከፍተኛ ጉጉት የሚጠብቀው ኢትዮጵያዊ አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ድጋፉን ገፍቶበታል፡፡ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሥራው እንደቀጠለ ነው፡፡ የሕዝቡ ስሜትም አልተቀዛቀዘም፡፡ እንዲያውም እያደር ተጋግሏል፡፡ የራስ ሀብትን በራስ አቅም የማልማቱ ጉዞ ፍጥነቱ እየጨመረ ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን ሙሉ አቅም የሚገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተጓዘ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ፈታኝ ምዕራፎችንም ተሸጋግሯል፡፡ በቅርቡም ግድቡ በሚገነባበት ቦታ ላይ የወንዙን ተፈጥሮአዊ አቅጣጫ የማስቀየር ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህን የተመለከቱ ኢትዮጵያውያንና ልማቱን የሚደግፉ ወገኖች ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ አጠቃላይ ሥራ ከ20 በመቶ በላይ መድረሱም ፕሮጀክቱ በተያዘለት ዕቅድ መሠረት እየተጓዘ ለመሆኑ ሌላው ማሳያ ነው፡፡

የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ሲታቀድ የአባይን ውሃ በፍትሐዊነት መጠቀም የሚለውን መርህ መሠረት ያደረገ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የተፋሰሱን አገራት በማይጎዳ መልኩ የሚከናወን ልማት እንዲሆንም በቂ ጥናት ተደርጎበትና ተመክሮበት ነው ተግባራዊ የተደረገው፡፡ ከአካባቢ ጋር ወዳጅ የሆነ የልማት አጀንዳ መሆኑንም ብዙዎች መስክረውለታል።  ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው፡፡

እውነታው ይህ ቢሆንም ከመነሻው ጀምሮ ፕሮጀክቱን የሚቃወሙ አንዳንድ አካላት አልጠፉም፡፡ በአገኙት አጋጣሚም ቅሬታቸውን ሲገልጹ ተደምጧል፡፡ የቅሬታቸው መነሻ ውሃ የማይቋጥር ቢሆንም ዛሬም ከመሠረተ ቢስ ጥላቻ ሊላቀቁ አልቻሉም፡፡ በእዚህ ረገድ ግብፅ የፊታውራሪነቱን ቦታ ትይዛለች፡፡ ግድቡ በግብፅ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳርፋል የሚለውን ትችት ከመሰንዘር ታቅባ አታውቅም፡፡ ግድቡ በተፋሰሱ አገራት ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡ ይህንንም እውነታ በጥናት ላይ በተመሠረተ ተጨባጭ ማስረጃዎች ለማስረዳት ሞክራለች፡፡

ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚነሳውን ቅሬታ ለመፍታት እንዲቻል አማራጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት አድርጋለች፡፡ ይህን መሠረት ባደረገ መልኩም ከሦስቱ የተፋሰሱ አገራት(ኢትዮጵያ ፣ግብፅና ሱዳን) የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያቀፈ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በእዚህ ቡድን ውስጥም ከሦስቱ አገራት ስድስት ባለሙያዎች፤ እንዲሁም በሦስቱ አገራት በጋራ የተመረጡ አራት ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተካትተዋል፡፡

የባለሙያዎቹ ቡድን ለአንድ ዓመት ያህል የጥናትና የምልከታ ሥራውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ የግድቡን የጥናትና የዲዛይን ሰነድ መርምሯል፡፡ በግንባታው ቦታ በመገኘትም ሂደቱን ቃኝቷል፡፡ ከግንባታው ተቋራጮችና አማካሪዎች ጋርም ተወያይቷል፡፡በሦስቱ አገራትም የተለያዩ ስብሰባዎችን በማካሄድ ውይይት አድርጓል፡፡ እነዚህንና መሰል ጥናቶችን በጥልቀት ሲያከናውን የቆየው የባለሙያዎች ቡድን የመጨረሻውን ሪፖርት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ በእዚህም የግድቡ ግንባታ በግብፅና በሱዳን ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሌለ ገልጿል፡፡

የግድቡ ዲዛይን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ለሦስቱ አገራት(ኢትዮጵያ፤ግብፅና ሱዳን) ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑም ነው የተጠቀሰው፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ግብፅ እውነታውን ለመቀበል ተቸግራለች፡፡ ሰሞኑን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ይዘው የሚወጡትም ይህንኑ የግብፅ አቋም የሚያንፀባርቅ ነው፡፡

ከአባይ ውሃ 86 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የምታበረክተው ኢትዮጵያ« ውሃውን በፍትሐዊነት እንጠቀም» ከማለት ያለፈ አቋም አላንፀባረቀችም፡፡ የላይኛዎቹ የተፋሰሱ አገራትም ይህንን የኢትዮጵያ አቋም በመደገፍ ስምምነታቸውን በፊርማቸው አፅድቀዋል፡፡ ሱዳንም ቢሆን የግድቡን ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ ትደግፋለች፡፡ ይህንንም በተለያዩ ጊዜያት አንፀባርቃለች፡፡ ግድቡ ለሱዳን የሚጠቅም እንጂ የማይጎዳ መሆኑንም ገልጻለች፤እየገለጸችም ትገኛለች፡፡

የዓለም አቀፉን ሪፖርት ተከትሎም ሱዳን ለግድቡ እውን መሆን የሚጠበቅባትን ለማድረግ እንደምትሰራ አስታውቃለች፡፡ የሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትርና የመንግሥት ቃል አቀባይ ሚስተር አህመድ ቢላል ኡስማን በቅርቡ በካርቱም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሱዳን ግድቡን የመደገፍ አቋሟን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማስታወቃቸውን ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል፡፡ ግድቡ ለሱዳን የሚጠቅም በመሆኑ አገራቸው ባለሙያዎችንና ቴክኒሻኖችን በመላክ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቷን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሁሴን ኦማር አልበሽር እ.አ.አ በ2012 መንግሥታቸው የግድቡን ግንባታ እንደሚደግፍ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ይህም ግድቡ ለሱዳንና ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነት እንደሚያገለግል ቀደም ሲልም በሱዳን በኩል ተቀባይነት እንዳለው  ያስረዳል፡፡ «ግድቡ ቢፈርስ ካርቱም በጎርፍ ትጥለቀለቃለች…» እየተባለ በአንዳንድ ወገኖች የሚናፈሰው ወሬም ውሃ የማይቋጥር እንደሆነ ነው ሚስተር ኡስማን ያስረዱት፡፡ በምክንያትነትም ግድቡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የሚገነባ ፤ እንዲሁም ግንባታውን የሚያከናውነው የኢጣሊያ ኩባንያ በቂ ልምድ ያለውና አስተማማኝ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ሱዳን በእዚህ መልኩ ለግድቡ ግንባታ ግብ ስኬት እየጣረች መሆኗን እየገለጸች ትገኛለች፡፡ ምክንያቷ ደግሞ አንድና ግልጽ ነው፡፡ ግድቡ ሱዳንን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይህንንም ሱዳን በደንብ ተገንዝባለች፤ አረጋግጣለች፡፡ ግብፅ ታዲያ ይህን እውነታ መቀበል ተስኗት ስትዳክር እንመለከታለን፡፡ ከእውነታ የራቁና ሚዛን የማይደፉ ምክንያቶችን በመደርደር ግድቡ እንደሚጎዳት ታንፀባርቃለች፡፡ የተለያዩ የግብፅ መገናኛ ብዙኃንም ከግድቡ ጋር በተያያዘ ከእውነታ የራቁ አሉባልታዎችን እያሰራጩ ይገኛሉ፡፡

አገራቸውን ወክለው ከዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ጋር እንዲሰማሩ ግብፅ የመረጠቻቸው ግብፃውያን ባለሙያዎች በደንብ አጣርተውና አጥንተው የደረሱበትን እውነታም ለመቀበል ተቸግራለች፡፡ ከራሷ ባለሙያዎች በላይ ማንን ልታምን ነው? ያስብላል፡፡ ታማኝና በዘርፉ በቂ ዕውቀትና ልምድ አላቸው ብላ የመረጠቻቸውን ባለሙያዎች አለማመን እውነታውን ካለመቀበል ውጪ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡

ግድቡ በሚኖረው ጥቅምና ጉዳት ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ጥናት በማካሄድ እውነታውን በተጨባጭ መረጃዎች በማረጋገጥ ስለ ትክክለኛነቱ ባለሙያዎቹ ፊርማቸውን በማስፈር ለሦስቱም አገራት አቅርበዋል፡፡ ይህንን ሰነድ ነው እንግዲህ ግብፅ ችግር አለበት ያለችው፡፡ ዝርዝር መረጃዎችን ያልያዘ ሪፖርት በማለትም ለማጣጣል ሞክራለች፡፡ የግብፅ ባለስልጣናት ጉዳዩን በጥልቀት ከመመልከትና ዘላቂ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ በስሜታዊነት የመጓዝ አዝማሚያን የመረጡ ይመስላል፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን አሁንም የኢትዮጵያ አቋም አልተቀየረም፡፡ በፍትሐዊነት የመጠቀም መስመርን አላለፈችም፡፡ የህዳሴው ግድብ በግብፅ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ አለመኖሩንም ተጨባጭ መረጃዎችን በማቅረብ እያስታወቀች ነው፡፡ ከመጀመሪያውም ቢሆን ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማያደርስ በጥናት አረጋግጣለች፡፡ ወደ ትግበራ የተገባውም እነዚህ ጥናቶች ከተካሄዱ በኋላ መሆኑ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት በተለይም በግብፅ ዘንድ የጠራ ግንዛቤ እንዲፈጠር ኢትዮጵያ ተነሳሽነቱን ወስዳ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም አድርጋለች፡፡

ይህም በባለሙያዎቹ ቡድን ከፍተኛ ምስጋናን አስገኝቶላታል፡፡  የቡድኑ ሪፖርት ይፋ መደረግን ተከትሎም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አድናቆት ተችሯታል፡፡ ግድቡ አሉታዊ ተፅዕኖ የሌለው መሆኑ በሪፖርቱ መረጋገጡ ኢትዮጵያ በትክክለኛ ጎዳና እየተጓዘች ለመሆኑ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ልማትን ለማፋጠን የምታደርገው ጥረት በጥናት ላይ የተመሠረተና ሌሎችን በማይጎዳ መልኩ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ችሏል፡፡ ስለሆነም ግድቡን መደገፍና ኢትዮጵያን ማበረታታት እውነትን ከመደገፍ ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡

አሁንም ቢሆን ግብፅ ለምታነሳው ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥት በሩን ክፍት አድርጓል፡፡ በማናቸውም መልኩ ለመመካከርና ለመወያየት ዝግጁ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር ያላትን ግንኙነት ሰላማዊ በሆነ መልክ ለማስቀጠል ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት ያሳያል፡፡ ዛሬም ቢሆን ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ በፍትሐዊነት እንጠቀም እያለች ነው፡፡ በሌሎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማያስከትል መልኩ የህዳሴ ግድብን እየገነባች ይገኛል፡፡

ግብፅም ይህንን የሰላም ጎዳና መከተል ይኖርባታል፡፡ በሱዳን በኩል እንደተንፀባረቀው ሁሉ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎላውን ልማት መደገፍ በታሪክም የሚያስመሰግን ተግባር ነውና ግብፆች በትኩረት ሊመለከቱት ይገባል፡፡ እናም ግብፅ ሆይ የህዳሴው ግድብ ተጠቃሚነትሽን የሚያጎላ ነውና አቋምሽን መፈተሽ ይኖርብሻል፡፡

«የግድቡን ግንባታ ለማስቆም የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል» የሚሉ ግብፃውያን እንዳሉ ሁሉ «ጉዳዩ በውይይትና በምክክር ሊፈታ ይገባል፡፡» የሚሉም አልጠፉም፡፡ እነዚህንም ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣውም የእነዚህኞቹ አማራጭ ነው፡፡ እናም የሚጠቅመውን የመፍትሔ አማራጭ መከተሉ ተገቢ ነው፡፡ ለጋራ ተጠቃሚነት ደጀን የሆነውን የህዳሴ ግድብ መደገፍ ተገቢና ወቅታዊ እርምጃ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ግብፅ የምትሰነዝራቸው ጊዜ ያለፈባቸው ትችቶች፣ መሠረተ ቢስና ደካማ አስተሳሰቦች የግድቡን ግንባታ ለሴኮንድም ማስቆም እንደማይችሉ ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ በቀረርቶዎች በመደናገጥ ከልማት ሥራዋ ወደ ኋላ እንደማትልም ነው የተናገረው፡፡ ይህ እርምጃ ደግሞ ድህነትን ለመዋጋት ለተሰለፈ ዜጋ ትልቅ ኃይልና ብርታት ነው፡፡ እናም በሁሉም የሚደገፍ አቋም ነውና ይበል ያሰኛል፡፡

በመሆኑም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታን በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ከማስኬድ የሚያግድ አንዳች ኃይል አይኖርም፡፡ ሕዝቡም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃንና ማህበራዊ ድረ ገፆች በሚለቀቁ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች ሳይሸበር ድጋፉን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡ የህዳሴው ግድብ «የእንደጀመርነው እንጨርሰዋለን» ጉዞ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ነገም… ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ከአባይ ውሃ 86 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የምታበረክተው ኢትዮጵያ «ውሃውን በፍትሐዊነት እንጠቀም» ከማለት ያለፈ አቋም አላንፀባረቀችም፡፡ የላይኛዎቹ የተፋሰሱ አገራትም ይህንን የኢትዮጵያ አቋም በመደገፍ ስምምነታቸውን በፊርማቸው አፅድቀዋል፡፡ ሱዳንም ቢሆን የግድቡን ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ ትደግፋለች፡፡ ይህንንም በተለያዩ ጊዜያት አንፀባርቃለች፡፡ ግድቡ ለሱዳን የሚጠቅም እንጂ የማይጎዳ መሆኑንም ገልጻለች፤እየገለጸችም ትገኛለች፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ
 Home

No comments:

Post a Comment