Wednesday, June 19, 2013

'የግብጽ ፕሮፓጋንዳ ግድቡን ይበልጥ እንድንደግፍ አነሳስቶናል' በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን

(Jun 19, 2013, (አዲስ አበባ))--የግብጽ መንግስት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ እያናፈሰ የሚገኘው ተራ ፕሮፓጋንዳ ለግድቡ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክሩ እንዳረጋቸው በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ገለጹ፡፡

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሰኔ 9/2005 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ጎብኝተዋል፡፡ ''ማየት ማመን ነው'' ያሉት ኢትዮጵያውያኑ በጉብኝቱ በተደረገላቸው ገለጻ ግንባታው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን መረዳታቸውንና ከዚህ ቀደም ስለግድቡ ግንባታ ከሰሙት ጋር ፍጹም ልዩነት አለው ብለዋል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ማንኛውንም ፕሮጀክት በድብቅ ማካሄድ እንደማይቻል ገልጸው መንግስት የግድቡ ግንባታ ከጅምሩ አንስቶ ለተፋሰሱ ሃገራትና ለዓለም ህብረተሰብ ግልጽ በሆነ መንገድ ማካሄዱ እጅግ የሚደነቅ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በቅርቡ የወንዙን አቅጣጫ ማስቀየር ተከትሎ በግብጽ መንግስት በኩል እየተናፈሰ የሚገኘው ከሃገሪቱ መንግስት የማይጠበቅ ተራ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን አስረድተው በግንባታው ላይ ምንም አይነት እንቅፋት እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡

የግብጽ መንግስት ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ተፋሰሱ ሃገራት ጠቀሜታ እንዳለው በመረዳት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ተባባሪ ሊሆን እንደሚገባም ኢትዮጵያውያኑ አስገንዝበዋል፡ በአሁኑ ወቅት የግብጽ መንግስት ግድቡን አስመልክቶ የያዘው አቋም ለግድቡ ግንባታ ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደዲቀጥሉ እልህና ቁጭት እንደፈጠረባቸውም ተናግረዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ በአካባቢው በሚፈጠረው የኢንቨስትመንት አማራጭ የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ኢትዮጵያዊያኑ ጠቁመዋል፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ በበኩላቸው በህብረተሰቡ የጋራ ርብርብ እየተገነባ የሚገኘው የህዳሴው ግድብ በተቀመጠለት ጊዜ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ወደሚኖሩበት አካባቢ ሲመለሱ በጉብኝቱ ያገኙትን ትክክለኛ መረጃ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው በማሳወቅ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ንጭ፡ ኢሬቴድ

No comments:

Post a Comment