Thursday, June 13, 2013

የቦሌ አያት ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችን ያገተው ጅብ...

(June 12, 2013, (አዲስ አበባ))--ክስተቱ ብዙም የተለመደ አይደለም። የህንፃው ነዋሪዎች በፍርሃት ተውጠዋል፡፡ እንደወትሮዋቸው በማለዳ ተነስተው ከህንፃው በቀላሉ ለመውረድ አልቻሉም፡፡ በአንዳች አስፈሪ እንግዳ ፍጡር ታግተዋል፡፡ ሠራተኛውም ሆነ ተማሪው ከህንፃው ለመውረድ ተቸግሮ ባለበት በፍርሃት እየራደ ነው፡፡ በተለይም የህንፃ ቁጥር 154  የአራተኛ ፎቅ ነዋሪዎች የዕገታ ድራማው ዋና ተዋናዮች ናቸው፡፡

ከህንፃው ፊት ለፊት መሬት ላይ ቆሞ የዕገታውን ድርጊት የሚመለከተው የአካባቢው ነዋሪ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ አጋቹ በዚህም አልተገረመም፤ አልተደናገጠም፡፡ የዕገታው ድራማ እንደቀጠለ ነው፡፡ ሁሉም በሁኔታው ተገርሟል፤ ደንግጧል፡፡ የህንፃው ነዋሪዎች መላው ጠፍቷቸው በጭንቀት ተውጠዋል፡፡

የሠዓቱ መግፋት ደግሞ ሠራተኞችንና ተማሪዎችን አስጨንቋል፡፡ ጭንቀቱ ሲበረታ ነዋሪዎች አንዳች እርምጃ ለመውሰድ ተስማሙ፡፡ ፍርሃቱ እያደር እየለቀቃቸው በመምጣቱ መፍትሄ ያሉትን እርምጃ መውሰድ ጀመሩ፡፡ አጋቹን በኃይል ለማባረር፣ ታጋቾቹን በትግል ለማስለቀቅ። ዱላና ድንጋይን እንደ አማራጭ ተጠቀሙ፡፡ አጋቹ ግን በእዚህም የሚበገር አልሆነም፡፡ ዱላው ቢበረታበትም  ባለበት ሆኖ ከመቆጣት ባለፈ ከህንፃው ላይ ለመውረድ አልፈቀደም፡፡

ይህ ያልተጠበቀና አስደንጋጭ የእገታ  ድራማ ትናንት በቦሌ አያት ቁጥር አንድ ኮንዶሚኒየም ነበር የተካሄደው፡፡ አጋቹ ጅብ ሲሆን የታገቱት ደግሞ የህንፃ ቁጥር 154 ሦስተኛና አራተኛ ፎቅ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ጅቡ በስንት ሰዓትና እንዴት ወደ ህንፃው እንደወጣ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ አንዳንዶች «ሰው ለመብላት ተከትሎ መጥቶ ሳይሆን አይቀርም…» ሲሉ ሌሎች በበኩላቸው «ህንፃው ላይ በአጋጣሚ ወጥቶ ነግቶበት ይሆናል…» የሚል መላምት ሰንዝረዋል፡፡

 ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ግን ጅቡ የህንፃው ሦስተኛ ፎቅ ደረጃ ላይ በመተኛት አራተኛና ሦስተኛ ፎቅ  ላይ ያሉ ነዋሪዎችን ለሰዓታት አግቷል፡፡ በዱላ በመምታት ከፎቁ ላይ ለማስወረድ በነዋሪዎች የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ፖሊስ ተጠርቶ በጥይት ተገድሎ የአጋች ታጋች ድራማው ተጠናቅቋል፡፡ በዚህም ጅቡ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ሳያደርስ ሊወገድ ችሏል፡፡

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ይህን መሰሉ ድርጊት  በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም ከአሁን በፊትም በጋራ ቤቶቹ የተወሰኑ ህንፃዎች ላይ ተስተውሎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡  የጋራ መኖሪያ ህንፃዎቹ ዙሪያቸው ያልታጠረ በመሆኑ ጅቦች የጋራ መኖሪያ ህንፃዎቹ አካባቢ በተደጋጋሚ  እንደሚዘዋወሩ ነዋሪዎቹ ይገልፃሉ፡፡ ይህም በነዋሪዎቹ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ስጋትና ፍርሃት እያሳደረ መጥቷል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው አካል ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment