Friday, May 24, 2013

አዲስ አበባ ለአህጉራዊው ተቋም መቀመጫነት እንዴት ተመረጠች?

(May 24, 2013, (አዲስ አበባ))--አዲስ አበባ የቀድሞ አፍሪካን አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ህብረትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ሽር ጉድ እያለች ነው። ከተማዋ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ. ም የሚከበረውን የህብረቱን የ50 ዓመት የምስረታ በዓል በደማቅ ሁኔታ ልታከ ብር የሚያስችሏትን  ዝግጅቶችን አጠናቅቃለች። በግን ባታ ላይ የነበሩ መንገዶች በፍጥነት ተጠናቅቀዋል።

African Union Headquarters in Addis Ababa
የነባር መንገዶች የጥገና ሥራ ተከናው ኗል። ለአፍሪካ ህብረት ጽሕፈት ቤት ህንፃ መሥሪያ ቦታ ከሊዝ ነፃ የሰጠችው አዲስ አበባ አሁንም የህብረቱን የ50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ መሪዎቹ በህብረቱ ስም ሀገር በቀል ዛፎችን የሚተክሉበት የእፅዋት ማዕከል በጉሌሌ አዘጋጅታለች፡፡ የሀገራችንና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በምን ሁኔታ ለአህጉራዊው ድርጅት መቀመጫነት እንደተመረጠች ያውቃሉ?

የአ.አ.ድ. ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ አመራረጥ
እ.ኤ.አ. በግንቦት ወር 1963 ዓ.ም. የአፍሪካ አንድነት ድርጅት(አ.አ.ድ) ቻርተር በአዲስ አበባ ተፈርሞ ድርጅቱ ቢመሠረትም፣ የዋና ጽሕፈት ቤቱ መቀመጫ አገር አልተወሰነም ነበር፡፡ በወቅቱ አገራችን ጉባዔውን በማስተናገዷና የካዛብላንካንና የሞኖሮቪያ ቡድኖችን በማስታረቋ የዋና ጽሕፈት ቤቱን መቀመጫ የማግኘት ተስፋ አላት የሚል እምነት ነበር፡፡

ነገር ግን እ.ኤ.አ. ነሐሴ ወር 1963 ዓ.ም. ለአ.አ.ድ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እልባት ይሰጣል ተብሎ ከተጠበቀው የዳካር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ አንድ ሳምንት አስቀድሞ በቤኒን የተሰበሰቡት የ15 የፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የአ.አ.ድ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ በዳካር (ሴኔጋል) እንዲሆን መስማማቸው ያልታሰበ ክስተት ነበር፡፡

ዳካር በተካሄደው የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ የዋና ጽሕፈት ቤቱ ጉዳይ እንዲወሰን ከናይጄሪያና ከሴኔጋል በቀረበው ሃሣብ መሠረት አገሮች እጩነታቸውን ገልፀዋል፡፡ በእዚሁ መሠረት የሴኔጋል፣ የናይጄሪያና የኮንጐ (ዛየር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ዋና ከተሞቻቸውን በዕጩነት አቅርበዋል፡፡

ስብሰባው የዋና ጽሕፈት ቤቱ መቀመጫ በድምጽ ብልጫ እንዲወሰን ተስማምቶ በተደረገው ምርጫ አዲስ አበባ 15፣ ዳካር 12፣ ኪንሻሳ 1 ሲያገኙ ናይጄሪያ ምንም ድምጽ ሳታገኝ ቀርታለች፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ የአ.አ.ድ ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫ ሆነች፡፡  የኢትዮጵያ መንግሥትም ለጽሕፈት ቤቱ አገልግሎት እንዲውል አዲስ የገነባውን የፖሊስ ማሠልጠኛ ኮሌጅ ሕንፃና የሚገኝበትን ቅጥር ግቢ በስጦታነት አበርክቷል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ጽሕፈት ቤት መቀመጫ አወሳሰን
የአፍሪካ ህብረት መመስረቻ ሰነድ እ.ኤ.አ. በ2000 ዓ.ም. በሎሜ (ቶጐ) ለማጽደቅ በተካሄደ ውይይት የመቀመጫው ጉዳይ ወደፊት እንዲወሰን ሃሣብ ቀርቦ ነበር፡፡ታላቁ መሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነትና ብልጽግና የተቻላትን ሁሉ ማድረጓን በመግለጽ፣ ለአፍሪካ ህብረት ዋና ጽሕፈት ቤት መቀመጫነት ከኢትዮጵያ የተሻልኩ ነኝ የሚል ካለ በመድረክ ቀርቦ ውይይት ይደረግበት ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ይሁንና የተነሳው ሃሳብ በጉባዔው ድጋፍ ባለማግኘቱና ብዙኃኑ አባል አገራት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗን በመደገፋቸው በህብረቱ የመመስረቻ ሰነድ አንቀጽ 24 ላይ ዋና ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ የንብረቱ መመስረቻ ሰነድም ጸድቋል።

እ.ኤ.አ. በሐምሌ ወር 2ዐዐ4  በአዲስ አበባ በተደረገው የመሪዎች ጉባዔ ወቅት የዋና ጽሕፈት ቤቱ መቀመጫ እና ኮሚሽኑ እንዲለያዩ ሃሣብ ቀርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ጉባዔው የህብረቱ ኮሚሽንና የዋና ጽሕፈት ቤቱ መቀመጫ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በማረጋገጥ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በእነዚህና በሌሎችም አጋጣሚዎች ሁሉ  የህብረቱ አባል አገራት ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ ሆና እንድትቀጥል እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡
ምንጭ አዲስ ዘመን ጋዜጣ


No comments:

Post a Comment