Friday, May 24, 2013

ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመቅረፅ የሃይማኖት ተቋማት ሚና መጎልበት ይጠበቅበታል

(May 24, 2013, (አዲስ አበባ))--ከአምስት የሃይማኖት ተቋማት የተውጣጡት የሃይማኖት አባቶችና ወንጌል ሰባኪዎች ተሰብስበው መክረዋል። የፀረ ሙስና ትምህርትን ፅንሰ ሃሳብ ተገንዝበው በየቤተ እምነታቸው የሚያስተምሯቸው ምዕመናን ለሥነ - ምግባር ብልሹነት እንዳይጋለጡ ለማስተማር የተዘጋጀ መድረክ ነው።

ይህ ደግሞ ከሚከተሉት አስተምህሮ ጋር ልዩነት እንደሌለው በሥልጠናው ላይ በመሳተፍ የሚገኙት ያነጋገርናቸው ሰባኪያን የሚገልጹት።

አዲስ ዘመን ጋዜጣ, አዲስ አበባ
የፌዴራል የሥነ - ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን  ለሃይማኖት አባቶቹና ወንጌላውያኑ በአዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና  ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት፣ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ ከወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን እና ከቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን የተውጣጡ 250 ያህል  የሚሆኑ የሃይማኖት አባቶችና ወንጌላውያን ተሳታፊ ናቸው።

ሁሉም  በጋራ የሚስማሙት ሙስና ሌብነት መሆኑን ነው። «ሌብነት ደግሞ ሀጢአት ነው» በማለት ተሳታፊዎቹ ይናገራሉ። ይህንኑ ለምዕመኑ በአስተምሮአቸው እንደሚገልጹም ነው ያረጋገጡት። ለሙስና መከሰት ዋነኛ መንስኤ ብልሹ ሥነ - ምግባር እንደሆነ አስተያየታቸውን የሰጡት የሃይማኖት አባቶቹና ወንጌላውያኑ ይህንን ችግር ለማስወገድ ኃላፊነታቸው ድርብ መሆኑን ነው የሚጠቁሙት።

«ሙስናን ማጥፋት የሚቻለው ትግሉ ከእኔ መጀመር ሲችል ነው» የሚሉት የቃለ ሕይወት ቤተክርስቲያን መጋቢ አላምረው ዮሴፍ፤ ለሚያስተ ምሯቸው ምዕመናን አርአያ መሆን የሚችሉትም በመልካም ሥነ ምግባር ሲታነፁ እንደሆነም ያመለክታሉ። ይህን የሚያደርጉትም ሙስና ለአገር ዕድገት ፀር በመሆኑ ትውልድ ወደእዚህ አፀያፊ ተግባር እንዳይገባ የበኩላቸውን ለመወጣት መሆኑን ይገልጻሉ።

መንግሥት በቅርቡ በሙስና ተጠርጣሪዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ «መልካም ጅማሬ» ብለውታል። እርምጃው በሙስና ሰንሰለት ውስጥ በሚገኙት ዘንድ ድንጋጤን የሚፈጥር  እንደሆነም ያመለክታሉ። ወደ መስመሩ ለመቀላቀል በመንደርደር ላይ ላሉት ደግሞ ከባድ ማስጠንቀቂያ መሆኑን ያብራራሉ። በሂደት ሌሎቹን የመንግሥት ተቋማትም ማንኳኳት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።

«የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ያላቸውን ተጠርጣ ሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል መንግሥት  ሰሞኑን የወሰደው እርምጃ ለሌሎች መቀጣጫ ይሆናል» በማለት ነው የወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ቄስ አብርሃም በርጋ የተናገሩት ።  በሙስና ምክንያት ለተሰቃዩትና እንግልት ለደረ ሰባቸው ደግሞ መፅናኛ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በኢፌዴሪ ሥነ - ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እየተሰጣቸው ያለው ትምህርት ከሚያስተምሩት ቅዱስ መጽሐፍ ጋር በይዘት እንደሚቀራረብ የጠቀሱት ቄስ አብርሃም፣ ስለሙስና አስከፊነት ለምዕመኑ በትኩረት ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውን ነው ያረጋገጡት። «ሰው ራሱን  ከብልሹ ሥነ - ምግባር ከጠበቀ፣ ቀጥሎ ቤተሰቡን፣ ኅብረተሰቡንና አገሩን ማዳን ይችላል» የሚል ፅኑ እምነት እንዳላቸውም ቄሱ ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያኑ አባ አበራ ገብረማርያምና የመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያኑ ወንጌላዊ ሰብራላህ ከድር ኢሳ በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በሙስና ወንጀል በተጠረጠሩ ላይ  በመንግሥት የተወሰደው እርምጃ በግላቸውም ሆነ በሚከተሉት ቤተክርስቲያን አወንታዊ በሆነ መልኩ ነው የታየው። «ሙስና አገርን የሚጎዳ ተግባር መሆኑን ያወቀ ማንኛውም ሰው በተዘዋዋሪ ራሱን የሚጎዳ እንደሆነ ሊያውቅ ይገባል» ብለዋል።

የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ - ሙስና ኮሚሽን በሥነ - ምግባር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የሥነ - ምግባር ትምህርት ከፍተኛ አማካሪ አቶ ፀጋዬ ጥሩነህ እንደገለጹት፤ የሥልጠናው ዓላማ ማስተማር፣ መከላከልና ሕግን ማስፈፀም ነው።

«ሙስናን ከምንጩ ዘላቂ በሆነ መልኩ ለማጥፋት ሙስናን የሚፀየፍ ማህበረሰብ መፍጠር የግድ ይላል» ያሉት አቶ ፀጋዬ፤ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ የሕዝብ ክንፎችን በማደራጀት መልዕክት ወደ ተፈለገው ስፍራ ማድረስ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ። «የእምነት አባቶችንና ወንጌል ሰባኪዎችን ግንዛቤ ማስጨበጡ ምዕመኑ ዘንድ በቀላሉ መልዕክት ለማስተላለፍ ያግዛል ነው» ያሉት።

«ጥንቱንም ቢሆን ቤተ እምነቶች አስተምህሮት መልካም ነው» የሚሉት ከፍተኛ አማካሪው፤ ምዕመናን የእምነት መሪዎቻቸውን ከሌላው በተሻለ እንደሚያምኑ ተናግረዋል። ይህም የሃይማኖት አባቶች ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ነው የገለጹት። ይህም የዘቀጠ ሥነ - ምግባርን በማስወገድ ሙስናን የሚፀየፍ ህብረተሰብ ለመፍጠር ምቹ እንደሚሆን ነው የተናገሩት።

የፌዴራል የሥነ - ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወዶ አጦ በበኩላቸው፤ «በሥነ - ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሚቻለው መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ህብረተሰቡና ሌሎችም ተባብረው ሲንቀሳቀሱ ነው» ብለዋል።

ሙስና ሲወገድ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል ሲንሠራፋ ደግሞ በእዚያው ልክ ተጎጂ እንደሚሆኑ የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ችግሩ በእምነት ነፃነት ላይም አሉታዊ ገፅታ እንዳለው ያመለክታሉ። ስለሆንም በሥነ - ምግባር የታነጸ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ያስገነዝባሉ።

የሃይማኖት አባቶች በተለይም ምዕመናን በሥነ - ምግባር እንዲታነጹ እና ሙስናን አጥብቀው እንዲታገሉ የማስተማርና የመምከር አባታዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው። ኮሚሽኑ የሃይማኖት ተቋማት በፀረ - ሙስና ትግሉ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በመገንዘቡ በ2001 ዓ.ም ከተቋማቱ ጋር ተባብሮ ለመሥራት የሚያስችለውን የሁለትዮሽ የትብብርና የምክክር መድረክ ማቋቋሙ ይታወሳል።

 በ2004 እና በ2005 ዓ.ም ኮሚሽኑ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ከ18 ሚሊዮን ለሚበልጡ ምዕመናን የግንዛቤ ማስጠበጫ ትምህርት ሰጥቷል። 
ምንጭ: አዲስ ዘመን ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment