Thursday, March 14, 2013

ሴቶች ሁሉ ሊፈጽሙት የሚገባ የማህፀን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ

(መጋቢት 04/2005, መታሰቢያ ካሣዬ, (አዲሰ አበባ))--ማንኛውም ግብረ ስጋ ፈፅማ የምታውቅ ሴት ለማህፀን በር የቅድመ ካንሰር መንስዔ ለሆነው በሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ኢንፌኪሽን የመጋለጥ ዕድል አላት፡፡ ከ30-45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል የሚለው ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ነው፡፡ የማህፀን ካንሰር በአብዛኛው የ “ሂውማን ፓፒሎማቫይረስ ኢንፌክሽን” ለረጅም ጊዜ በሰውነት ውስጥ በመቆየት በሚያደርገው ሂደት የሚከሰት ነው፡፡

ምናልባት አንዲት ሴት በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ቫይረሱን ብታገኘው እስከ ቅድመ ካንሰር ምልክት ለመድረስ ቢያንስ በአማካኝ ከ10-15 ዓመታት ይፈጃል፡፡ በ15 ዓመቷ የግብረ ስጋ ግንኙነት ብትጀምር እስከ 30 እና 35 ዕድሜዋ ድረስ ላይታወቅ ይችላል፡፡

የቅድመ ካንሰር ምልክት በሰውነቷ አንድ ጊዜ ከታየ በማህፀን በር ላይ ከተከሰተ በኋላ ቅድመ ካንሰሩ ወደ ካንሰር ለመለወጥ ከ10-15 ዓመት ይፈጃል፡፡ ስለዚህ የካንሰርን ሁኔታ በምናይበት ጊዜ በቫይረሱ አማካኝነት ተለውጦ በማህፀን ውስጥ የማህፀን ክፍሎች ላይ ለውጥ አምጥቶ፣ ቫይረሱ የማህፀን ግድግዳ ክፍሎችን በመበከል ወደ ቁስለት፤ ያ ቁስል ደግሞ ከማህፀን ባሻገር ወደ ደም በመግባት ወደ ሰውነት ውስጥ መተላለፍ የሚችልበት ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ገዳይ ከሆኑት የሴቶች በሽታዎች ውስጥ የማህፀንና ጡት ካንሰር የመጀመሪያዎቹን ደረጃዎች ይይዛሉ፡፡ ቀደም ሲል የማህፀን ካንሰር የሀብታሞችና በኢኮኖሚ የዳበሩ አገሮች ብቻ ችግር ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ ትልቁ ችግር የነበረው ይሄንን በሽታ ለማወቅ የሚቻልበት መንገድ ውስን ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች እየታመሙ ይሞቱ ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአሜሪካ መንግስት በሽታ መከላከልና መቆጣጠሪያ(CDC) በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የማህፀን ካንሰር መከላከል ፕሮግራም የጀመረ ሲሆን ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከሌሎች ድርጅቶችና ክልሎች ጋር በመሆን ይሄንን ፕሮግራም ጀምረዋል፡፡ ፕሮግራሙ በመጀመሪያ ደረጃ በተመረጡ 14 ሆስፒታሎች ላይ በተለይም ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሴቶችን ከካንሰር ለመጠበቅ የመከላከል ሥራ የሚሰራ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ማንኛውም ሴት ይህንኑ ምርመራ ለማድረግ እንድትችል ያደርጋታል፡፡ ዶ/ር መንግስቱ አስናቀ የፓዝፋይንደር ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ፕሮግራም ተጠሪ እና የተቀናጀ የቤተሰብ የጤና ፕሮግራም ዳይሬክተር ስለጉዳዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ህክምናው እንዴት ይሰጣል? በማህፀን በር ላይ የአሲቲክ አሲድ የተባለ ፈሳሽ በመቀባት የቅድመ ካንሰር ምልክቱን ማየት ይቻላል፡፡ ምልክቱ ካለ በቀዘቀዘ ካርቦንዳኦክሳይድ ይጠረጋል፡፡ በሚጠረግበት ጊዜ ችግሩ ወደ ካንሰርነት እንዳይለወጥ ያደርገዋል፡፡ አንዳንድ የቅድመ ካንሰር ምልክቶችን ጥንካሬ ስላላቸው በቀዘቀዘ ክራዮቴራፒ (Cryo ማሽን ይባላል) የህክምና ዘዴ ለመጥረግ ያስቸግራል፡፡ እነዚህን ምልክቶች ከመጀመሪያው ቴክኖሎጂ በተለየና (LEEP፤ በተባለ ቴክኖሎጂ አቃጥሎ እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል፡፡

ቅድመ ካንሰር ወደ ካንሰርነት ሲለወጥ እንዴት ይታወቃል? በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ኢንፌክሽን ያለባቸው በቀጥታ ወደ ቅድመ ካንሰር ፤ ቅድመ ካንሰር ያላቸው ሁሉ ወደ ካንሰር ይለወጣል ማለት አይደለም፡፡ በተወሰነ ደረጃ በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ኢንፌክሽን ያለባቸው ሰዎች (በኢንፌክሽኑ የተያዙ ሰዎች) ችግሩ ወደ ቅድመ ካንሰርነት ይቀየራል፡፡ ይሄም ለመታየት ከ10-15 ዓመት ይፈጃል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም፡፡ ቫይረሱን ለማከምም ሆነ ሌላ ህክምና ለማድረግ ጊዜው አይደለም፡፡ የቅድመ ካንሰር ምልክቱ ከታየ ግን ማከም ይቻላል፡፡ ከቅድመ ካንሰር ወደ ካንሰር ለመለወጥ አሁንም ከ10-15 ዓመት ጊዜ ይወስዳል፡፡ ቅድመ ካንሰሩን ማከም ከቻልን ግን ወደ ካንሰር እንዳይሄድ አቆምነው ማለት ነው፡፡ ከቅድመ ካንሰር፤ ወደ ካንሰር ከተቀየረ ደግሞ ለካንሰር የሚደረጉ ህክምናዎች አሉ፡፡ ምናልባት ካንሰሩ በማህፀን የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ብቻ የሚታይ ከሆነ ችግሩ የታየበት የማህፀኑን ክፍል ብቻ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡

በአካባቢው ባሉ ቦታዎች ተራብቶም እንደሆነ እነዛ እጢዎች አብረው የሚወጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ወደ ደም ውስጥ ከገባ በኋላ የሚሰጠው ህክምና የመድሃኒት የቀዶ ጥገና ወይንም የጨረር ህክምና ነው፡፡ ይሄ የሚሆነው አሁን በምንላቸውን ቴክኖሎጂዎች ሳንጠቀም ከቀረን ነው፡፡ አሁን የምንላቸውን ቴክኖሎጂዎች ቅድመ ካንሰር ህክምናና ምርመራ ካደረግን ግን እዛ ደረጃ ላይም ሳይደርሱ ካንሰሩን ለመከላከል ይቻላል፡፡

ዕድሜያቸው ከ30-40 ላሉ ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምርመራ ካደረጉ እና ችግር እንዳለባቸው ካወቁ በነዚህ ህክምናዎች በሽታው ወደ ካንሰርነት እንዳይቀየር መከላከል ይቻላል የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ቢቻልና አመቺ ቢሆን የግብረ ስጋ ግንኙነት ከመጀመሩ በፊት ክትባት መውሰድ ቫይረሱን ለመከላከል ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሆኖም ክትባቱ ከአቅም አንፃር አስቸጋሪ ነው፤ ለምሳሌ በአሜሪካ ክትባቱን አንዴ ለመውሰድ እስከ 250 ዶላር ያስከፍላል፡፡

ይሄ በእኛ አቅም የሚቻል አይደለም፡፡ ክትባቱ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ አገልግሎት ላይ ይዋል ቢባል መሰጠት ያለበት የግብረ ስጋ ግንኙነት ላልጀመሩ ሰዎች እንጂ ለጀመሩ ሰዎች አይደለም፡፡ ምክንያቱም የግብረሥጋ ግንኙነት የጀመሩ ሴቶች ቫይረሱ በሰውነታቸው ውስጥ ሊኖር ስለሚችል ነው፡፡ ከክትባቱ ውድነት አንፃርና በአሁኑ ሰዓት በሽታው ካንሰር ደረጃ ሳይደርስ መከላከል የሚቻልበት ቴክኖሎጂዎች ስላሉ እነዚህን መጠቀም ይመረጣል፡፡

የቅድመ ካንሰር መከላከያው አዲስ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቁ ረገድ በህክምና ተቋማት ውስጥ ምን እየተሰራ ነው? በአዲሱ ቴክኖሎጂ አንድ ሴት ምርመራውን አግኝታ ‹‹ምንም ነገር የለብሽም›› ወይንም ‹‹ምልክት ያሳያል›› ተብላ ቀጠሮ ተሰጥቷት ‹‹ሌላ ጊዜ ነይ›› የምትባልበት አይደለም፡፡

ምርመራውን ምልክት ከታየ እዛው ቦታ ላይ ህክምናውን ታገኛለች - ዋን ስቶፕ ዲያግኖሲስ ትሪትመንት (በአንድ ቦታ የሚፈልጉትን አግኝቶ መውጣት እንደማለት ነው) ከዚህ በፊት የነበሩት ምርመራዎች የማህፀን ካንሰር በአብዛኛው ይሰራ የነበረው ከማህፀን በር ላይ ፈሳሽ ተጠርጎ ተወስዶ (ቁስለቱ ካለ ከቁስለቱ ላይ) ተወስዶ በፓቶሎጂ(ከተጠረገው ቁስል ላይ ያለውን ሴል) በመመርመር የካንሰር ምልክት አለ የለም የሚለውን ለማወቅ የሚካሄድ የምርመራ ዘዴ ነበር፡፡

ለዚህ ምርመራ በመጀመሪያ በሙያው ክህሎት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የምርመራ ውጤቱንም ወዲያው ማወቅ አይቻልም፡፡ ከ10-15 ቀን ወይም ከዛም በላይ ቆይቶ በቀጠሮ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ ውድና ጊዜ የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ አዲስ ቴክኖሎጂ ግን አሲቲክ አሲድ በሚቀባበት ጊዜ የቀለምና የማህፀን በር ላይ ለውጥ ያመጣል፡፡ ያ ለውጥ ከቅድመ ማህፀን ካንሰር ጋር ከተመሳሰለ፣ ህክምናው ወዲያውኑ እዛው ይሰጣል፡፡ በነገራችን ላይ አሲቲክ አሲድ ስንል በየመንደሩ የሚሸጠው አቸቶ አይደለም ለራሱ ተብሎ የሚዘጋጅ አለ፡፡ ህክምናው በሰለጠነ ባለሞያ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በአዋላጅ ነርሶችና በነርሶች እየተሰጠ ነው፡፡ በክራዮቴራፒ(Cryo) የሚጠረገውን የፅንስና የማህፀን ሀኪሞች እና ሌሎች ሀኪሞች ይሰሩታል፡፡ ቴክኖሎጂው እየተሻሻለ መምጣቱ ረጅም ጊዜ የመጠበቅን ነገር እና ሌሎችንም ተጓዳኝ ችግሮችን ይፈታል፡፡

ይህንን ሕክምና ለማግኘት የህብረተሰቡ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው፡፡ ሴቶች ተራ ጠብቀው አገልግሎቱን ለማግኝት ይፈልጋሉ፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተሰጠው ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ላለባቸው ሴቶች በመሆኑ ህክምናውን መስጠት በተጀመረባቸው ሆስፒታሎች በአብዛኛው ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሴቶችን ለማዳረስ ተሞክሯል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ሁሉም ሴቶችም ምርመራውን ለማግኘት የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ነው፡፡  ህክምናው ከኤችአይቪ ጋር በሚኖሩ ሴቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር የተደረገበት ምክንያት ምንድነው?

የቅድመ ካንሰር ኤችአይቪ በደማቸው ያለ ሴቶች ላይ ከታየ ወደ ካንሰርነት የመለወጡ ሁኔታ በጣም አጭር ጊዜ ስለሆነ እና ኤችአይቪ በደማቸው ያሉ ሴቶችን በፍጥነት ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች የማህፀን ካንሰር አንዱ በመሆኑ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ ኬር ከምንለው አንዱ ለሴቶች በተለይ ሰርቫይካል ካንሰር (የማህፀን በር) ካንሰርን መከላከል አንዱና ትልቁ ነው፡፡ መታመምንና ሞትን የመቀነስ አቅሙከፍተኛ ነው፡፡ HIV በደማቸው ውስጥ ያሉ ሴቶች የሰውነታቸው የመከላከል ሃይል በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ ኤችአይቪ በደሙ ያለበት ሰው ሁሉ ቅድመ ካንሰር አለበት ማለት አይደለም፡፡ ቅድመ ካንሰር ያለው በሙሉም ካንሰር አለበት ማለትም አይደለም፡፡

የቅድመ ካንሰር ህክምና ለመስጠት የተለየ ሞያ ወይም ሥልጠና ያስፈልጋል?  እ.ኤ.አ በ2010 ሚያዚያ ወር ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ጋር በተፈጠረ ትብብር የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ከአምስት ሆስፒታሎች ተመርጠው ሰለጠኑ ወደየመጡበት ሄደው ለስድስት ወራት ሰለጠኑ፡፡ ከዚያም ተመልሰው መጥተው የአሰልጣኝነት ስልጠና እንዲሰለጥኑ ተደረገ፡፡ እነዚህኛዎቹ ደግሞ በዘጠኙም ክልል ባሉ ሆስፒታሎች እየሄዱ ስልጠና እንዲሰጡ ተደርጐ ወደ ሥራው ተገባ፡፡ ጉዳዩ በፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደ አንድ ጉዳይ ታይቶ በመንግስት ዕቅድ ውስጥ ገብቷል፡፡ ቅድመ ምርመር ማድረጉ ወደ ጤና ጣቢያዎች ቢወርድ ውጤታማ ሊሆንና ብዙዎች ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡

ፕሮግራሙ ከተጀመረ ወዲህ ምን ያህል ሴቶች ምርመራውን አገኙ ምን ያህሉስ የቅድመ ካንሰር ምልክት ተገኘባቸው? በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 ሺህ ሴቶች ተመርምረው ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ሴቶች የቅድመ ካንሰር ምልክቱ ተገኝቶባቸው ወደ 98ፐርሰንት ትሪትመንት አግኝተዋል፡፡ ሌሎቹ ከቅድመ ካንሰር ያለፈ በመሆኑ በኦፕሬሽንና በመሳሰሉት ህክምና ማግኘት ነበረባቸው፡፡

ከተመረመሩት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምልክቱ ጠፍቶአል፡፡ ‹‹አንዲት ሴት ለምርመራ መጥታና ቅድመ ካንሰር ምርመራው ተደርጎላትና ታክማ፤ ከአንድ ወር በኋላ መጥታ አሁን ምንም ምልክት የለሽም ተብላ ፊቷ ላይ የሚታየውን ደስታ ከማየት የበለጠ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም›› የቅድመ ካንሰር የነበረባቸው ሴቶች ህክምናውን ሳያገኙ ቢቀሩ ኖሮ ወደ ካንሰር ሊያድግ ይችል ነበር፡፡

ከምርመራው በፊት ካውንስሊንግ ይሰጣል፤ በአዲስ አበባና በክልሎች ህክምናው የት የት ቦታ ይሰጣል?  ምርመራውን ለማድረግ መጀመሪያ ካውንስሊንግ አለው፡፡ ከ30 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ባለው ጊዜ ድረሰወ ካውንስሊንጉ ሊፈጅ ይችላል፡፡ ምልክቶቹ ከተገኙ ሊሰጥ የሚችለውን መፍትሄ ምንድን ነው የሚለውን ጭምር የሚያካትት ነው፤

በአዲስ አበባ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ ሚሊኒየም ህክምና ትምህርት ቤትና ዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ይሰጣል፡፡ በክልሎች ደግሞ ይርጋለም፣ ወላይታ ሶዶ ሪፈራል ሆስፒታሎች አዋሳ፣ ባህርዳር ፈለገ ህይወት፣ ጎንደር፣ ደብረ ማርቆስና ደሴ ሪፈራል ሆስፒታሎች፤ መቀሌ፣ አድዋ፣ አክሱም፣ ማይጨው ለምለም ካርል ሆስፒታሎች፤ ነቀምት፣ አሰላ፣ ቢሾፍቱ ሆስፒታሎች ውስጥም ይሰጣል፡፡ አራት ክሊኒኮች ከኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ጋር በመተባበር ህክምናውን እንዲጀመሩ ድጋፍ ተደርጐላቸዋል፡፡ ጦር ሃይሎች ሆስፒታልም እንዲጀመር ድጋፍ ተደርጓል፡፡ አንድ ክራዮቴራፒ(Cryo) ማሽን ዋጋው 40 ሺ ብር ነው፡፡

የቅድመ ካንሰር ምርመራውን አድርጋ ህክምናውን ያገኘች ሴት በሽታው ድጋሚ እንደማይከሰት ምን ያህል እርግጠኛ ትሆናለች? ቅድመ ካንሰርን ማከም ከተቻለ ካንሰርን መከላከል ይቻላል፡፡ ወደ ካንሰር ከተለወጠ በኋላ ግን ያለው አማራጭ ከፍተኛ ህክምና ነው ይህ ደግሞ የሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ነው፡፡ ከህሙማኑ መብዛት የተነሣ የሚሰጠው የዓመት ወይም የስምንት ወር ቀጠሮ ነው፡፡ አንዳንዶች ቀጠሮአቸውን እየጠበቁ ሳይደርስ ይሞታሉ፡፡ ቅድመምርመራው ይሄን ቁጥር ለመቀነስ ያረዳል፡፡

ቅድመ ካንሰር ህክምና ያደረገች ሴት ከዓመት በኋላ መጥታ ምርመራ በማድረግ ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ሆና ትሄዳለች፡፡ አብዛኞቹ ማለትም ከ90 ፐርሰንት በላይ ያህሉ ኔጌቲቭ ይሆናሉ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ መጥታ አሁን ምልክቱ ካላትና እንደገና ለመጥረግ ጠንካራ ከሆነ ሊፕ የሚባለው ህክምና ይሰራላታል፡፡  አንዲት ሴት ቢያንስ አንድ ጊዜ የቅድመ ካንሰር ምርምራ ካደረገች ከካንሰር ለመጠበቅ ዋስትና ይሆናታል፡፡

አብዛኛዎቻችን የበሽታ ምልክት ከታየብን በኋላ ነው ወደ ጤና ተቋማት መሄድ የምናዘወትረው ይህ ግን አግባብ አይደለም፡፡ በተለይ ካንሰር ምልክት የለውም፡፡ ከ30-35 ባለው ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች ምርመራ ማድረጉ ምልክት የሌለውን ነገር በማወቅ ከችግሩ ራስን ለመጠበቅ እንዳችሉ ያደርጋቸዋል፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ
 Home

1 comment:

nima said...

ቅድመ ካንስር የህመም ምልክቶች ምንድናቸው ስላልተገለጹ ነው፡፡

Post a Comment