Monday, September 26, 2011

የግብፅ አዲሱ አመራር የአባይ ወንዝን ለጋራ ጥቅም ለማዋል ዝግጁነቱን እያሳየ መሆኑን ታዋቂው ጋዜጣ ዘገበ

(መስከረም 14 ቀን 2004 (አዲስ አበባ) --የግብፅ አዲሱ አመራር ከኢትዮጵያ ጋር የአባይ ወንዝን ለጋራ ጥቅም ለማዋል ዝግጁነቱን እያረጋገጠ መሆኑን ታዋቂው የአሜሪካ ጋዜጣ ዘገበ።

ኢዜአ ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር የተባለውን ጋዜጣ የሰሞኑን ዕትም ጠቅሶ እንዳስታወቀው ግብፅን እያስተዳደረ ላይ ያለው አመራር ከቀድሞው መሪ በተሻለ አባይን ለጋራ ጥቅም ላይ ለማዋል ተባባሪነቱን እያሳየ መጥቷል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝትም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስና ወንዙን በጋራ ለመጠቀም የበለጠ መግባባት ላይ ለመድረስ እንዳስቻለም ገልጿል።

ኢትዮጵያ በወንዙ ከፍተኛ ኃይል የሚያመነጭ ግድብ መገንባት መጀመሯ ግብፅ ለዘመናት በወንዙ አጠቃቀም ያላትን አመለካከት ላትቀየር ትችላለች የሚል ግምት አሳድሮ እንደነበር አስታውሶ፣ከፕሬዚዳንት ሁሴን ሙባረክ ከሥልጣን መውረድ በኋላ የተተካው አስተዳደር በጋራ ተጠቃሚነት እንደሚያምን ጋዜጣው አስረድቷል።

አመራሩ አገሮቹ ካለፈው ዓመት ወዲህ የጀመሩትን በመግባባት ላይ የተመሰረተ ውይይት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር እንዳስቻለም ኢዜአ ምንጩን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በካይሮ ቆይታቸው ወንዙን የአባይ ተፋሰስ አገሮች የጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑበት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ጋዜጣው አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት   


No comments:

Post a Comment