(Feb 13, 2103, አዲስ አበባ)--በሃያ ዘጠነኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሰላሳ
አንድ ዓመት በኋላ ተሳትፈው በምድብ ጨዋታ ከውድድሩ የተሰናበቱት ዋልያዎቹ ውጤት ባይቀናቸውም መልካም ጨዋታ
እንዳሳዩ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች መስክረዋል።
ቡድኑ በውጤት ረገድ ላስመዘገበው ዝቅተኛ አፈፃፀም በተለያዩ
አካላት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ቆይተዋል።የቡድኑ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫው ስለ
ነበራቸው ዝግጅትና በውድድሩ ጠቅላላ ሁኔታ ላይ ለቡድኑ ሽንፈት ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
አሠልጣኝ ሰውነት ትናንት በዋቢሸበሌ ሆቴል
በተዘጋጀው ቴክኒካዊ የምክክር መድረክ ላይ ቡድኑ ለውድድሩ ያደረገውን ዝግጅትና በውድድሩ ስላጋጠሙት የተለያዩ
ጉዳዮች የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች፤የስፖርት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችና ባለ ድርሻ አካላት በተገኙበት ሪፖርት
አቅርበዋል።
አሠልጣኙ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው ጥሩ
የሚባል ቡድን እንደነበረና ማራኪ የሆነ ጨዋታ እንዳሳየ በማስታወስ በምድብ ጨዋታው በጥቃቅን ስህተቶች ውጤት ማምጣት
ያለመቻሉ በተለይም በቡርኪና ፋሶው ጨዋታ ስለተፈጠረው ስህተት ራሳቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ
ከቤኒን ጋር ካደረገው የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ አንስቶ በአፍሪካ ዋንጫው የምድቡን የመጨረሻ ጨዋታ ሲያደርግ
ፌዴሬሽኑና ስፖርት ኮሚሽን በቅርበት በመከታተል ትልቅ ድጋፍ ሲያደርጉለት እንደነበረ አሠልጣኝ ሰውነት አስረድተዋል።
ዋልያዎቹ ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያው ጀምሮ
ወደ ፊት የሚያደርጉትን ጨዋታ አስመልክቶ ጠንካራ ግቦችን አስቀምጠው ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ አሠልጣኙ አስረድተው
ግቡም በአህጉሪቱ ዋንጫ መሳተፍ መሆኑንና ይህም መሳካቱን አሠልጣኝ ሰውነት አስታወቀዋል።
እንደ አሠልጣኝ ሰውነት ገለፃ ለአፍሪካ
ዋንጫው ወደ ዝግጅት ከመግባታቸው በፊት ተጫዋቾቹ ምን እንደሚጎድላቸውና ምን እንዳሟሉ በባለሞያ በመለየት ቡድኑን
የማጠናከር ተግባር ተከናውኗል።ይህንንም ተከትሎ ከፍጥነትና የጡንቻ ጥንካሬ ጋር በተያያዘ በርካታ ተጫዋቾች ክፍተት
እንደነበረባቸው በመረጋገጡም በልምምድ ክፍተቱን በመሙላት ለውጥ ያሳዩ ተጫዋቾች ተመርጠዋል። ይህንን ማድረግ
ያልቻሉት ደግሞ ከቡድኑ ተቀንሰዋል።
በአፍሪካ ዋንጫው የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታ
ዋልያዎቹ ዛምቢያን በጨዋታ በልጠው ነጥብ መጋራት ቢችሉም በሁለተኛው የምድብ ጨዋታ በቡረኪናፋሶ ትልቅ ሽንፈት
ደርሶባቸዋል። ለሽንፈቱ ዋና መንስኤ የሆነውም ዋልያዎቹ ቡርኪናፋሶን አሳንሰው መመልከታቸው መሆኑን አሠልጣኝ ሰውነት
አስረድተዋል።
«ቡርኪናፋ ሶን በተመለከተ ከጨዋታው በፊት ምንም አይነት መረጃ አልነበረንም»ያሉት አሠልጣኝ ሰውነት ተጋጣሚያቸውን እንደ ሚያሸንፉ እርግጠኛ ሆነው መግባታቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ነው ያብራሩት።
እንደ አሠልጣኝ ሰውነት ገለጻ፤ ቡርኪና
ፋሶን በገጠሙበት ጨዋታ የመረጡት አሰላለፍና ያቀዱት ታክቲክ አልሰራም። በተከላካይ መስመር ላይ የታዩት ከፍተቶችና
ተጫዋቾቻቸው በዛምቢያ ጨዋታ መድከማቸው ተዳምሮ አራት ግብ እንዲቆጠር ምክንያት ሆነዋል።
አሠልጣኝ ሰውነት ከናይጄሪያ ጋር ያደረጉትን
የመጨረሻውን የምድብ ጨዋታ እንደሚያሸንፉ እምነት አሳድረው መግባታቸውን በማስታወስ፤ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ያህል
ደቂቃ እስኪቀረው ድርስ ጥሩ ጨዋታ እንዳሳዩና እድል እንዳልቀናቸው ገልፀዋል።
ተጫዋቾቹ ከዳኛ ጋር የገጠሙት አላስፈላጊ
እሰጥ አገባ በናይጄሪያው ጨዋታ ላይ እንደጎዳቸው የገለጹት አሠልጣኙ፤ ተጫዋቾች ከዳኛ ጋር የማይሆን ነገር ውስጥ
እንዳይገቡ ቀደም ብለን ማሠልጠን ይገባን ነበር ብለዋል።
እንደ አሠልጣኙ አገላለጽ የተከላካዮች
መዘናጋት፤በኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለመውሰድ የአማካይ ክፍሉ ከግላዊ ጨዋታ ተላቅቆ በቡድን ላይ
አለመመስረት፤በማጥቃት ሂደት በመሃል ክፍሉና በፊት መስመሩ መካከል ክፍተት መፈጠሩ በብሔራዊ ቡድኑ የታዩ ዋና ዋና
ደካማ ጎኖች እንደነበሩ አሠልጣኙ ጠቅሰዋል።
ከረጅም ዓመታት በኋላ በውድድሩ ተሳትፎ
በሚገባ ልምድ ያካበተው ብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት መቻሉ ለቡድኑ አንድ ጠንካራ ጎን ተደርጎ
እንደሚወሰድም ተገልጿል። የቴክኒክ ምክክር መድረኩ ዛሬም የሚቀጥል ሲሆን፤ ባለ ድርሻ አካላት በሚያነሱት ጥያቄ ላይ
የተለያዩ ውይይቶች ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment