(Feb 23, 2103,አዲስ አበባ)--በተጠናቀቀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮና የሆነችው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን አባል አሕመድ ሙሳ ዋሊያዎቹ ከየትኞቹም ተጋጣሚዎቻቸው የበለጠ ፈታኝ ሆነውባቸው እንደነበር ይገልጻል።
ተጫዋቹ ኤምቲኤንፉትቦል ዶት ኮም ከተባለ ድረ ገጽ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደገለጸው፤ ዋሊያዎቹ ከውድድሩ በፊት በደቡብ አፍሪካ የተዘጋጀውን 29ኛውን ሻምፒዮና የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸው ከነበሩት ከኮትዲቯርና የዋንጫ ተፋላሚ ከሆኑት ቡርኪና ፋሶ በበለጠ ለአረንጓዴ ንስሮቹ ፈታኝ ሆነውባቸው እንደነበር ተናግሯል።
ለሩሲያው ሲኤስኬ ሞስኮ በመጫወት ላይ የሚገኘው አህመድ ሙሳ ናይጄሪያዎች ከዋሊያዎቹ ጋር ባደረጉት የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ግብ ሳያስቆጥሩ ሰዓቱ እየገፋ ሲሄድ ምን እያሰበ እንደነበረ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ « ፈጽሞ
ምቾት የሚሰጥ ስሜት አልነበረኝም ። እንደምናሸነፍ ግን ተስፋ ነበረኝ ። በሻምፒዮናው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን
ጋር ያደረግነው ጨዋታ እጅግ ፈታኝ ነበር ። ያ ጨዋታ ከኮትዲቯርና ከቡርኪና ፋሶ ጨዋታዎች የበለጠ ከብዶን ነበር » በማለት መልሷል።
ተጫዋቹ በውድድሩ ምርጥ ብቃቱን እንዳላሳየ
ጠቁሞ፤ የዋንጫ ጨዋታውን በመሀል አርቢትርነት የመሩት ዳኛ የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረውን የፊሽካ ድምጽ ሲያሰሙ
የተሰማውደስታ ልዩ እንደነበረ ተናግሯል። በብራዚል በሚካሄደው በፊፋ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫና በዓለም ዋንጫ ውድድሮች
ላይ ምርጥ ብቃቱን እንደሚያሳይም አረጋግጧል።
በደቡብ አፍሪካ አረንጓዴ ንስሮቹ ዋንጫ ሊያነሱ የቻሉበትን ምክንያት ተጫዋቹ ተጠይቆ « ለአንድ ዓላማ እንደሚዋጋ ሠራዊት በኅብረት ጠንክረን መሥራታችን ነው» ሲል መልሷል። አብዛኛው የእግር ኳስ አፍቃሪ ሻምፒዮናው
ከመጀመሩ በፊት ኮትዲቯር እንደምታሸንፍ መገመቱንና አረንጓዴ ንስሮቹ እነርሱን ማሸነፋቸው ለስኬታቸው አስተዋጽዖ
ማበርከቱን ወይም አለማበርከቱን የተጠየቀው ተጫዋቹ በእዚህ ሐሳብ እንደማይስማማ ገልጿል።
አብዛኛው ተመልካች
ከኮትዲቯር ጋር ያደረግነው ጨዋታ በሻምፒዮናው የመጨረሻችን እንደሚሆን ገምቶ ነበር ብሏል። ነገር ግን እኛ እነርሱ ( ኮትዲቯሮች ) ከእኛ የተሻሉ ናቸው ብለን ፈጽሞ አምነን አናውቅም ሲልም አክሏል። ወደ ጨዋታው የገባነውም ለማሸነፍ ከፍተኛ ተስፋ ይዘን ነው በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።
በተያያዘ ዜና በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ለማውጣት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ( ካፍ ) ዝግጅት ጀምሯል። ሱፐርስፖርትዶት ኮም የተባለው ድረ ገጽ እንዳስነበበው ካፍ በመጪው ወር በሞሮኮ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ የምድብ ድልድል ዕጣ የሚያወጣ ሲሆን፤ ለዚሁ እንዲረዳ የኮንፌዴሬሽኑ አባል አገሮች በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በነበራቸው ተሳትፎና ባላቸው ውጤት መሠረት በሦስት ምድብ ደልድሏቸዋል ። ካለቅድመ ማጣሪያ በምድብ ድልድል ውስጥ ከገቡት አገሮች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንዱ ሆኗል።
በዚሁ መሠረት ዋሊያዎቹ ቤኒን ፣ አንጎላ፣ ኒጀር፣ ዚምባብዌ ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ሞዛምቢክ፣ ማላዊ ፣ ቡሩንዲ ፣ ላይቤሪያና ሱዳን በሚገኙበት በሦስተኛው ምድብ ውስጥ መካተታቸው ታውቋል።
ከአዲስ ዘመን
Related topics:
የናይጄሪያ ቡድን የክብር ኒሻን፣ የገንዘብና የመሬት ስጦታ ተበረከተለት
የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች የአፍሪካ ዋንጫው ድምቀት ነበሩ
የዋልያዎቹ ክራሞት
በአፍሪካ ዋንጫ ምን እንጠብቅ?
ዋሊያዎቹ የማይቻል ነገር የለም እያሉ ነው
የዋሊያዎቹ ደጋፊዎች የአፍሪካ ዋንጫው ድምቀት ነበሩ
የዋልያዎቹ ክራሞት
በአፍሪካ ዋንጫ ምን እንጠብቅ?
ዋሊያዎቹ የማይቻል ነገር የለም እያሉ ነው
No comments:
Post a Comment